ቅ/ፓትርያርኩ የጠ/ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅን አነሡ


  • የሰበካ ጉባዔ መምሪያ ኃላፊም ተነሥተዋል

(ደጀ ሰላም፤ ኦክቶበር 8/2010፤ መስከረም 28/2003 ዓ.ም):- የጠቅላይ ቤተ ክህነት ም/ዋና ሥራ አስኪያጅ የነበሩት ንቡረ ዕድ ኤልያስ አብርሃ ከዛሬ አርብ መስከረም 28/2003 ዓ.ም ጀምሮ ከሥልጣናቸው መነሣታቸው ታወቀ። በቤተ ክህነቱ ውስጥ ባላቸው ተሰሚነት እና የሥልጣን ቅደም ተከተል ከወንበራቸው በላይ ጉልበት የነበራቸው ንቡረ ዕድ ኤልያስ ሥልጣናቸውን ያጡት ከፓትርያርኩ ጋር ባለመግባባታቸው ወይም በሌላ ምክንያት ሳይሆን ቤተ ክህነቱ ራሱን እንዲያሻሽል ከተለያዩ አካላት በሚደረግበት ጫና ምክንያት ሳይሆን እንዳልቀረ ምንጮቻችን ጠቁመዋል።

በተያያዘ ዜና የሰበካ ጉባዔ መምሪያ ኃላፊ የነበሩት ሊቀ ኅሩያን ያሬድ ከበደውም ከሥልጣናቸው ተነሥተው ወደ ጎፋ ገብርኤል መዛወራቸው ታውቋል።  “ሊቀ ኅሩያን” የሚል የማዕረግ ስም ተሰጥቷቸው ታላቁን የቤተ ክርስቲያኒቱን የሰበካ ጉባዔ ማደራጃ መምሪያ ኃላፊነት ሲመሩ የቆዩት የፓትርያርኩ እህት ልጅ ያሬድ ከበደው ከዓመታት በፊት በቅዱስ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ታቦተ ሕጉ በቆመበት የአንድ ባህታዊ ነፍስ በጠፋባት ዕለት “ጥይቲቱን ያስወነጨፈው እርሱ ነው” እየተባሉ ይታማሉ። ሊቀ ኅሩያን ያሬድ የቤተ ክህነቱ ቁጥጥር ክፍል ኃላፊ እንዲሁም የቤተ ክርስቲያኒቱ የጀርባ አጥንት የሆነው የሰበካ ጉባዔ መምሪያ የበላይ ሆነው ቆይተዋል። ይህ መምሪያ በተወዳጁ መንፈሳዊ አባት በሊቀ ጉባዔ አባ አበራ በቀለ መሪነት ለአስርት ዓመታት ሲተዳደር የነበረ ሲሆን አባ አበራ ከፓትርያርኩ በደረሰባቸው መገፋት የሕክምና ርዳታ ሳያገኙ፣ በአንዲት ቆርቆሮ በቆርቆሮ ቤት ውስጥ ኖረው በቅርቡ ከዚህ ዓለም በሞት ሊለዩ በቅተዋል።
በቤተ ክህነቱ ውስጥ ስላለው ስለዚሁ የሥልጣን ሽግሽግ እና ምንጩ የምናዘጋጀው ሪፖርታዥ እንደረሰልን የምናቀርብ መሆናችንን እየገለጽን እንድትከታተሉ ከወዲሁ እናስታውሳለን።