በኢትዮጵያ የሚደረጉ ዓለም አቀፍ ስብሰባዎች መቀሌ ላይ እንዲካሄዱ መመሪያ ተላለፈ

ዘረኛውና አምባገነኑ የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የሚካሄዱ ዓለማቀፋዊ ስብሰባዎች በተቻለ መጠን በመቀሌ ከተማ እንዲደረግ የስብሰባ አዘጋጆችን ማባበል መጀመሩን የውስጥ አዋቂ ምንጮች ለግንቦት 7 መረጃ ክፍል በላኩት ጥቆማ አስታወቁ። እንደምንጮቻችን መረጃ የወያኔው ዘረኛና አምባገነን አገዛዝ ይህን የማግባባት ሥራ ለመጀመር የፈለገበት ምክንያት የህወሃት ንግድ ድርጅቶች እና የቅርብ ሸሪኮቻቸው በመቀለ ከተማ ያስገነቡት ዘመናዊ ሆቴሎች የፈሰሰባቸውን ያህል ገንዘብ በተገመተው የጊዜ ገደብ ስለማስመለሳቸው ምንም ፍንጭ ሊገኝ ባለመቻሉ እንደሆነና እስከዛሬ በአገራችን ዋና ከተማ በአድስ አበባ ሲስተናገዱ የቆዩትን አለም አቀፍ ስብሰባዎች በሙሉ ወደ መቀሌ በማዞር ከፍተኛ የሆነ ገቢ ለመሰብሰብ ካላቸው ፍላጎት አንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል።

ወያኔ በመቀሌ ከተማ እንዲደረጉ የሚፈልጋቸው ስብሰባዎች በተባበሩት መንግሥታት የአፍሪካው ቅርንጫፍ መሥሪያቤት እና በሥሩ የሚተዳደሩ እርዳታ ለጋሾች የሚያደርጉት የአህጉር ስብሰባዎች በሙሉ እንደሆነና እነደ ዩ ኤስ ኤይድ ፤ ዩኒሰፍ የመሳሰሉትን እንደሚጨምር ከነዚሁ የውስጥ አዋቂ ምንጮች የደረሰን መረጃ ያመለክታል።

የተቀረው የኢትዮጵያ ክልሎች የራሱ አገር ክፍል የማይመስለው ዘረኛው የህወሃት መሪዎች ቡድን ስልጣን ላይ ከወጣበት ዕለት ጀምሮ የአገሪቱን ሃብት እየዘረፈ አላስፈላጊ የሆኑትን የንግድ አገልግሎት መስጫ ድርጅቶችን በመቀለ ከተማ ሲገነባ እንደነበረና ይህም ውስጥ ውስጡን እየተቀጣጠለ ከፍተኛ የሆነ ህዝባዊ ተቃውሞ ሲያስነሳበት የነበረና በማስነሳት ላይ የሚገኝ መሆኑ ይታወቃል። ወደመሃል አገር የማጓጓዣ ወጪው ብቻ የምርቱን ዋጋ በእጥፍ እንደአናረው የሚነገርለት የትግራይ ስምንቶ ፋብሪካን ጨምሮ ትግራይ ውስጥ በዘመቻ የተሰሩ ግንባታዎች በሙሉ የታሰበላቸውን ትርፋማነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ሊያስገኙ ባለመቻላቸው ለራሱ ለወያኔ ቁንጮዋች ራስ ምታት እየሆኑ መምጣቱን ለአገዛዙ የፋይናንስ እንቅስቃሴ ቅርበት ያላቸው ምንጮች በመናገር ላይ ናቸው።