“አነስተኛ ጊዜ” ብሎ ነገር የለም
ከዝግጂት ክፍላችን
“ዋን ዊክ” ወይም በአማርኛ “አንድ ሳምንት” የሚል ርእስ ያለው ፊልም ተራኪ ተመልካቾቹን እንዲህ ሲል ይጠይቃል፥ “ጥያቄው መሆን ያለበት…ከዚህ በኋላ መኖር የምትችሉት አንድ ሳምንት ወይም አንድ ወር ነው ተብሎ ቢነገራችሁ፤ በዛ ጊዜ ምን ትሰሩበት ነበር? ምን አይነት ሚስጥር ትገልጣላችሁ? የትኛውን የሙዚቃ ባንድ ታያላችሁ? ለየትኛው ሰው ፍቅራችሁን ታውጃላችሁ? የትኛውን ምኞታችሁን ለማሟላት ትሞክራላችሁ? ቆንጆ ቡና ለመጠጣት ስትሉ ወደየትኛው አገር ትሄዳላችሁ? ምን አይነት መጽሃፍስ ትጽፋላችሁ?”
ከዛ ቀደም ብሎ በነበረው የፊልሙ ታሪክ፥ ዋናው ገጸ ባህሪ ቤን ክፉ ደረጃ ላይ የደረሰ የነቀርሳ ወይም የካንሰር በሽታ እንዳለበት ተነግሮት ነበር። ምርመራውን ያካሄደው ዶክተር በሽተኛውን አስቀምጦ በፍጥነት ህክምና ሊያገኝ እንደሚገባው እና ህክምናውም ካላገኘ የመኖር እድሉ ዝቅተኛ እንደሆነ ይነግረዋል። ድንጋጤ ፊቱን የሸፈነው በሽተኛም መልሶ፥ ህክምናውን ቢያገኝ ምን ያህል መኖር እንደሚችል ይጠይቃል።
“ሁለት አመት” የሚል መልስ ይሰጠዋል። “ህክምናውን ባላገኝስ፥ ልኖር የምችልበት አነስተኛ ጊዜ ምን ያህል ነው?” ብሎ ይጠይቃል። ይህን ጊዜ ዶክተሩ መልሶ፥ “አነስተኛ ጊዜ ብሎ ነገር የለም” ይለዋል።
እንደ እምቡጥ አበባ በፈካ ወጣትነቱ ላይ እንዲህ ያለ ጨለማ ማንዣበቡ በድብልቅልቅ ስሜት የሞላው ቤን፤ ከዶክተሩ ቢሮ ወጥቶ ከሄደ በኋላ፣ በቀረችው የህይወት ዘመኑ ማድረግ ያለበትን ነገር ለማሰላሰል በሚል በአገሩ ዙሪያ የአንድ ሳምንት ጉዞ ለማድረግ ተነስቶ ይሄዳል። በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢም፣ ለጉዞው በገዛው አሮጌ ሞተርሳይክል ላይ ሆኖ እየነዳ ሳለ፤ የሞተ እንስሳ ገጭቶ ከመንገድ ተሽከርክሮ በመውጣት እራሱን ስቶ ይወድቃል። ከጥቂት ቆይታ በኋላ ሲነቃ አለመሞቱን በመረዳት በደስታ ተጥለቅልቆ መደነስ የሚጀምረው ወጣት ከዚህ ሁሉ የተማረውን ሲነግረን እንዲህ ይላል፥ “ሁላችንም የምንኖረው በተበደርነው ጊዜ ነው፤ ለኑሮ አነስተኛው ጊዜ ብሎ ነገር የለም።”
አዎን፥ ወጣቱ ቤን መልሶ የመጣው ቀድሞ ዶክተሩ ወደነገረው ቁምነገር ነው። በዚህ አለም ላይ ልኖር የምችልበት አነስተኛ ጊዜ ምን ያህል ነው ብሎ ጥያቄ የለም። ማንኛውም ሰው በማንኛውም ሰከንድ ሊሞት ይችላል። ጠቢብ ሆነ ቂል። ሃያል ሆነ ደካማ። ባለስልጣን ሆነ ተራ ዜጋ። ሁሉም ባልተጠበቀ ጊዜ ከመሞት እራሱ ሊያድን የማይችል አላፊ ፍጡር ነው።
እንደ ወጣቱ ቤን ሁለት አመት አለኝ ብሎ ነቀርሳው እስኪገድለው የሚዝናናውም ከነቀርሳው ወዲህ ያልተጠበቀ አደጋ፣ ትንታ፣ ወይም ጉንፋን እንዳለ ሊረዳ ይገባል።
ከተፈጠርንበት ጊዜ ጀምሮ ስንሞት የኖርን ፍጡራን ብንሆንም፤ ሰዎች ስንባል ለምን እንደሆነ በማናውቀው ምክንያት የሟችነታችንን እውነታ ሙሉ በሙሉ የተቀበልነው አንመስልም። እያንዳንዱ ሰው ሲሞት በድንጋጤ እንሞላለን፣ በሃዘን እንሰበራለን፣ እንባችንን እናፈሳለን፤ የምንታመምም አለን።
የአንዳንድ ሃይማኖት ተከታዮች ሟችነታችንን መቀበል የማንችለው ፈጣሪ መጀመሪያ ሲፈጥረን እንድንሞት አድርጎ ስላልቀረጸን ነው ይላሉ። ሰው በሃጢያቱ ምክንያት ባይወድቅና ሟች ባይሆን ኖሮ፤ ለዘላለም እንዲኖር ተደርጎ የተሰራ ነበርና፤ ያ ነገር አሁንም ቢሆን በውስጡ ተቀብሮ ያለ ነገር ስለሆነ፤ አጠገቡ ያለ ሰው በሞተ ቁጥር መደንገጡ ከዛ የመጣ እንደሆነ ይናገራሉ። ምናልባት የኢቮሉሺነሪ ሳይንቲስቶች ደግሞ፣ ሰው ጉልበቱን እና ያለውን ሁሉ የሚያፈሰው ለመኖር፣ ለመትረፍ እና እራሱን ለማባዛት ስለሆነ፤ አስተሳሰቡ የሞትን ነገር እንዲቀበል ሆኖ አልተገነባም ይሉን ይሆናል።
እንግዲህ ያም ሆነ ይህ፣ ሃቁ እያንዳንዷ ደቂቃ ስጦታ መሆኗ ነው። ማንም የመሞቻ ጊዜውን አያውቅም። ለኑሮ “አነስተኛ ጊዜ” ብሎ ነገር የለም።
ምናልባት አንዳንዶቻችን፥ እንዳው ፈጣሪ የሁላችንንም የመሞቻ ቀን ቢያሳውቀን ኖሮ ምናለበት የሚል የዋህ ጥያቄ ጠይቀን እናውቅ ይሆናል። ተዘጋጅቶ መጠበቁ ሃዘኑን እንደሚቀንስልን አስበን። ጉዳዩን በሌላ ጎን ስንመለከተው የምናየው ግን አዎንታዊ ነገር አይደለም።
ምናልባት የመሞቻ ቀናችንን የምናውቅ ቢሆን ኖሮ፣ ያለ የሌለ ሃጢያት ስንሰራ፣ ስንዋሽ፣ ስንሰርቅ፣ ስንቀና፣ ስንበድል፣ ስናጠፋ እንከርምና፤ ለመሞቻችን ቀጠሮ አንድ አስር ቀን ሲቀረን ንስሃ መግባት እንጀምር ይሆናል። የመሞቻችንን ቀን አለማወቃችን ትእቢትና ማን አለብኝነትን ወዲያ ብለን ትህትና እንዲኖረን እድል ይሰጠናል።
ሃይማኖት ላለን፥ በማንኛውም ጊዜ መሞት መቻላችን በወዲያኛው አለም አለ ወይም ሊኖር ይችላል ብለን ከምንፈራው ፍርድ ለመዳን መልካሞች በመሆን እንድንሰናዳ ያደርገናል። ሃይማኖት የሌላቸው ደግሞ ከአፈር ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት ስማቸውን ለማትረፍ የምታስችላቸውን መልካም ስራ ለመስራት እንዲጣደፉ ይረዳቸዋል።
እንግዲህ መልክቱ ይህ ነው፥ ውድ አድማጭ፣ ባልተገመተ ሁኔታ ከዚህ ቀጥሎ ባለው ሰከንድ ልትሞት ትችላለህ፤ ልትሞቺ ትችያለሽ። ሁላችንም የምንኖረው በተበደርነው ጊዜ ነው። ያንን መጽሃፍ የመፃፊያ ጊዜ ነገ ሳይሆን ዛሬ ነው። ስእሉም መሳል ያለበት አሁን ነው። ክራርህን ከሰቀልክበት ለማውረድ ቀጠሮ አትያዝ። አቧራውን አራግፈህ ቅኔን ለመቀኘትም አትስነፍ።
ሰው ላደረገህ እውነት ለመቆምም አትፍራ፤ አትዘግይም። ምክንያቱም ነገ መሞትህ የማይቀር፤ ሟችነትህ ያለቀለት፣ የተጠናቀቀ ጉዳይ ነውና።
ጥያቄው ሊሆን የሚገባው፥ “በዛሬ ምን ታደርግበታለህ?” የሚለው ነው።