የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ኦነግ አመራር የገጠመውን አለመግባባት በእርቀሰላም ማስወገዱን ይፋ አደረገ
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር እንደፈ ረንጆች አቆጣጠር ሴፕቴምበር 29፣ 2010 ባወጣው መግለጫ ፤ በአመራር አባላቶቹ መካከል ተከስቶ በነበረው አለመግባባት እና የሃሳብ ልዩነት ምክንያት ተከፋፍሎ የነበረው ግንባር መልሶ እንዲዋሃድ አንጋፋ የግንባሩ አባላትና መስራቾች ባደረጉት የሽምግልና ጥረት ከስምምነት መደረሱን አስታውቆአል። እንደግንባሩ መግለጫ፤ በመስራች አባላቱ ሽምግልና ከስምምነት የተደረሰባቸው እና ባለፈው ስብተምበር 27 የተፈረመው ይህ የእርቅ ሠነድ ከ5 ወራት ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚደረግ ይፋ ሆኖአል። ኦነግ ለህዝብ ይፋ ባደረገው በዚህ የእርቅ ስምምነት መግለጫ፤ መላው አባላቱ ያለፈውን ወደጎን ትተው በአንድነት በመቆም የነጻነት ትግሉን እንዲያግዙ ጥሪ አቅርቦአል።
ቃለ አቀባዩ አቶ ሌንጮ ባቲና ዶር ቢያን አሶባ በትናንትናው ዕለት ረቡዕ ከአሜሪካ ድምጽ ሬዲዮ የአማርኛው ክፍለ ጊዜ ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የኦነግ አመራር እንደማንኛውም የፖለቲካ ፓርቲ የራሱ የውስጥ ችግር የነበረበት ቢሆንም ለመከፋፈል ያበቃው ምክንያት ትግሉን ምን ያህል እንደጎዳ በቂ ግንዛቤ የተጨበጠ በመሆኑ ከአሁን ቦኋላ ያለፈውን ወደጎን ትቶ ወደፊት ሊያራምድ በሚችለው አብይ ጉዳይ ላይ ማተኮር ይገባናል ሲሉ ተደምጠዋል። በተጨማሪም በዛሬይቷ ኢትዮጵያ ሁሉም የአገሪቱ ህዝብ በወያኔ እኩይ አገዛዝ መብቱና ክብሩ ተረግጦ አኩል እየተሰቃየ ስለሚገኝ ለነጻነት፤ ለፍትህ፤ ለእኩልነት እና ለዲሞክራሲ ከሚታገሉ ድርጅቶች ጋር ግንባር በመፍጠር ትግሉን ለማፏፏም ድርጅታቸው ኦነግ ዝግጁ እንደሆኑ አረጋግጠዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጥምረት ለነጻነት፣ ለእኩልነትና ለፍትህ የተባለው አዲሱ ጥምረት የኦነግ አመራር አካላት በመካከላቸው ያለውን ችግር በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት ያደረጉትን ጥረት አወድሷል።
የአፋር ሕዝብ ፓርቲ ፣ ግንቦት 7 የፍትህ ፤የነጻነት እና የዲሞክራሲ ንቅናቄ ፣እንዲሁም የኢትዮጵያ ህዝብ የአንድነትና የፍትህ ንቅናቄ በጋራ የመሰረቱት ጥምረት ለነጻነት፤ ለፍትህና ለእኩልነት ባለፈው እሁድ ባወጣው መግለጫ እንዳስታወቀው “ የኦነግ ውስጠ ድርጅት ችግር መቃለሉና ኦነግ እንደ አንድ ወጥ ድርጅት ተጠናክሮ መውጣቱ፣ የኦነግን መዳከምና መበታተን ሲመኝ ለነበረው ዘረኛው ወያኔ ቅስም ሰባሪ ኩነት እንደሚሆንበት ገልጿል።
በኢትዮጵያ ውስጥ በዘረኛው የወያኔ አገዝዝ ምትክ ዴሞክራሲያዊ ስርአት ምስረታ እውን እንዲሆን ኦነግ ሊጫወት የሚችለውን ቁልፍ ሚና ለሚያውቀው ወያኔ፣ ኦነግ ውስጣዊ ችግሩን አቃልሎ ፊቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ዋናው የህዝብና የዴሞክራሲ ጸር ወደ ሆነው ወያኔ የሚያዞርበት ዋዜማ ላይ መገኘቱ ለወያኔ ትልቅ መርዶ ነው ሲል መግለጫው አትቷል።
ይህ ለዘረኛዎቹ ወያኔዎች መርዶ ለህዝብ ወገኖች ግን ተሰፋን ሰንቆ የመጣ የኦነግ የ እርቅ ተሃድሶ፣ ዘረኛው የወያኔን ገዥ ቡድን እያስለቀሰ ዲሞክራሲ ናፋቂ ወገኖችን እያስፈነደቀ እንዲቀጥል ኦነግ በውስጥ ችግሩ የተነሳ የባከኑበትን ውድ ጊዜዎች በሚያካክሱ አስቸኳይና አፋጣኘ ስራዎች ሊጠመድ እንደሚገባው የጥምረቱ ጽኑ እምነቱ ነው ብሎአል።
መግለጫው በማከልም ለዴሞክራሲ የሚታገሉ ሃይሎች ኦነግን ጨመሮ፣ ባንድነት ተባብረው የጸረ ወያኔን ትግሉን ይመራሉ ብሎ የኢትዮጵያ ህዝብ በትግስት መጠበቅ ከጀመር በመሰንበቱ፣ የኦነግ የውስጥ ችግር መፈታት በሃገርና ከሃገር ውጭ የሚኖሩትን በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ዜጎች ታላቅ ተስፋ ይዘራባቸዋል ብሎአል።
መግለጫው በመጨረሻም ” ኦነግ ይህን ታላቅ ታሪካዊና ህዝባዊ አደራ ለመሸከም መወሰድ የሚገባቸውን ማናቸውንም ውሳኔዎች በድፍረት በመውሰድ በአጭር ግዚ ውስጥ የሚጠበቅበትን ከፍተኛ ሃላፊነት እንደሚሸከም ጥምረት ትልቅ ተሰፋ በኦነግ ላይ ጥሎአል ሲል አጠቃሏል።