የህወሃት ከሃዲ መሪዎች አፍራሽና ያልሞተ ስዉር አላማቸዉ ከንጉሤ ጋማ

በመለስ ዜናዊ፤ ስብሃት ነጋ፤ አባይ ፀሃዬ እና በሌሎች ጥቂት የህወሃት ከሃዲ መሪዎች አማካይነት በ” ነፃ አዉጪ” እና በ” መንግስት” ስም የተወሰዱትና በመወሰድ ላይ ያሉት ፖለቲካዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ተግባራት ለተለያየን ሰዎች የተለያየ ትርጉም ሊሰጡን ይችላሉ። የምንሰጠዉ ትርጉም ልዩነት ከድርጅታዊ ቅርበታችንና ወገናዊነት፤ ጎሳዊ አመለካከታችን፡ ፖለቲካዊ ግንዛቤያችን፤ የስርኣቱ ተጠቃሚነታችንና፤ ከኢትዮጵያዊነት እምነታችን ይመነጫል። ከሁሉ በላይ ደግሞ የተነጣጠሉት ተግባራት ለሚኖራቸዉ ድምር ዉጤት የምንሰጠዉ አትኩሮት ነዉ። ነገሮችን በቅንነት እንደተራ መመልከት በሌላ በኩል በተቃራኒዉ በጥርጣሬ ዓይን ማየት ለምንደርስበት አጠቃላይ ድምዳሜ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ላለፉት 36 አመታት ቁልፍ የሆኑ የአመራር ቦታዎችን የያዙት የህወሀት ከሃዲ መሪዎች በድርጅቱና በትግራይ ተወላጆች ስም የሚፈፅሟቸዉ ተግባራትና የተከተሏቸዉ አካሄዶች ምን ያመላክታሉ?ብለን እንድንጠይቅ እንገደዳለን።

የህወሃት ከሃዲ መሪዎች አሃዝ ጠቅሰዉ ” ዕድገት አሳይተናል” በማለት እንደሞኝ ክርክር ስላደነቆሩንና በተወሰኑ ክልሎችና ከተሞች የሚታዩ የመንገድና የህንፃ ግንባታዎችን የተመለከቱ አንዳንዶች በማወቅም ሆነ ባለማወቅ ምስክርነታቸዉን ስለሰጡ ሳይሆን በርግጥ አገራችንንና ህዝባችንን በዘላቂነት ከድህነት ሊያወጡ የሚችሉ የኢኮኖሚ ዕድገቶች ይታያሉ? የኢኮኖሚ ዕድገት በምን ይገለጻል?

በሌላ በኩል ዜጎች የሰብኣዊ መብታቸዉ ተጠብቆ፤ ፍትህ፤ እኩልነትና የህግ የበላይነት በሰፈኑበት ስርኣት ዉስጥ በዘላቂነት እንዲኖሩ የሚያስችላቸዉ የዲሞክራሲያዊ ስርኣት መሰረቶች እየተጣሉና እየጎለበቱ ናቸዉ? እዉን በአገሪቱ ዉስጥ ዜጎች ያለአንዳች ስጋት በእኩልነት እየኖሩ ነዉ? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት ነገሮችን መፈተሽ ተገቢ ነዉ።

ኢትዮጵያ ዛሬ በታሪክ የነበራት ስምና ዝና እንዲጎድፍ ፤ አገራዊ አንድነቷና ሉዓላዊነቷ እየተሸረሸረ እንዲሄድ በህወሃት መሪዎች በጎ ፈቃድ ለባእዳን በክፍያም ሆነ በገፀ በረከትነት ስትሰጥ፡ ታሪካዊ ቅርሶቿ ሲመዘበሩ፡ በሰላም ለዘመናት የኖረዉ ህዝቧ በየጥቃቅኑ ምክንያት እንዲጋጭ፤ በመካከሉ ልዩነት እንዲፈጠር፤ የግልና የማህበራዊ ህይወቱ ዋስትና እንዲያጣ ፤ ኑሮዉ ችግርና ጭንቀት እንዲወርሰዉ ሲደረግ፤ ከጊዜ ወደጊዜ እየወደቀና መቋቋም እንዲሳነዉ ሲፈረድበት፤ በአገራችን ላይ እንደሁለተኛ ዜጋ መቆጠራችንን በፀጋና በዝምታ እንድንቀበል በመደረግ ላይ ነን።

የህወሃት ጥቂት ከሃዲ መሪዎች ሃሳባቸዉን የተቃወመዉን ሁሉ በየደረጃዉ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ በማስወገድ የድርጅቱን አመራር ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥረዉ እዚህ እንደደረሱና ዛሬም በአንድ ጎሳ የበላይነት የግል ፍላጎታቸዉ ማስፈፀሚያ ሲያደርጉት እየተመለከትን ነዉ።

እንደ አጋሰስ ተጭነዉ የሚጋለብባቸዉ የኦህዴድ፤ የብኣዴንና የነሃይለማርያም የደቡብ ድርጅቶች ” እንወክለዋለን” የሚሉትን ሕዝብና ከልል ለጊዜያዊ ስልጣንና ሆዳቸዉ አሳልፈዉ በመሸጥ የህወሃት ከሃዲ መሪዎችን አፍራሽና ስዉር አላማ በማስፈፀም ላይ እንዳሉ እኛም እናዉቃለን፤ እነሱም አያጡትም።

ዛሬ ጥያቄዉ የነገ የከዚያ ወዲያ ተጠያቂ የመሆን የአለመሆን ጉዳይ ሳይሆን የህወሃት ከሃዲ መሪዎች ሰብኣዊና ዲሞክራሲያዊ መብቶቻችንን በየደረጃዉ በመግፈፍ፤ በጠመንጃ አፈሙዝ አስገድደዉ ይዘዉ፤ በፍርሃትና በሸብር ተብትበዉ፤ አገራችንን እንደግል የሸቀጥ ዕቃቸዉ ባሻቸዉ ቸርችረዉ፤ ሽጠዉና ለዉጠዉ በሃይል ለመኖር ጥርሳቸዉን ነክሰዉ በእልህ የሚቆሙት እስከመቼ ነዉ? የሚል ነዉ። እያንዳንዳችን እራሳችንን መጠየቅ ይኖርብናል እላለሁ።

ህወሃት አጋሰሶቹን አስከትሎ በመንግስትነት አዲስ አበባን ከተቆጣጠረበት ካለፉት 20 አመታት የስልጣን ላይ ቆይታዉ ስሙንም ሆነ አላማዉን እንዴት ሊለዉጥ አልቻለም? በማለት መጠየቅ አግባብ ይመስለኛል።

ለዚህ ጥያቄ ዉስጤ ጥርጣሬ ላይ የተመሰረተ መልስ ይነግረኛል። የትግራይን ሪፑብሊክ የመመስረቱ አላማ በእነዚህ የህወሃት ከሃዲ መሪዎች አእምሮ ዉስጥ አለመለወጡን፤ አድብተዉ አመቺ ጊዜና አጋጣሚ እየጠበቁ እንደሆነ…

እነዚህ ጥቂት የህወሃት ከሃዲ መሪዎች በምስጢር ያረቀቁትን ፀረ ኢትዮጵያ አንድነት አጀንዳ በህወሃት ዉስጥ ተቀባይነት እንዲኖረዉ በድርጅቱ ዉስጥ ሲፈፅሟቸዉ የነበሩ ወንጀሎችን በተለያዩ አጋጣሚዎች ተገንዝበናል።

ለኢትዮጵያ ብሄራዊ ጥቅምና አንድነት የሚቆረቆሩ ሃይሎች በድርጅትም ሆነ በግለሰብ ደረጃ በስልታዊ መንገድ እየተለቀሙ እንዴት ደብዛቸዉ እንዲጠፋ ሲደረግ እንደነበር፤ ለነፃነት በሚደረገዉ ትግል አምነዉ በቅንነት ከእነዚህ የህወሃት መሪዎች ጋር በረሃ ለበረሃ መስዋዕት የከፈሉና በአላማና በአመለካከት ልዩነት፤በግል ጥላቻና ቂም በሂደት የተገደሉ፤ የተገለሉ፤ ከሞት ተርፈዉ በመካከላችን የሚገኙ ኢትዮጵያዊነት ያስገደዳቸዉ ወገኖች መስክረዋል።

መለስና አብረዋቸዉ የተሰለፉት የህወሃት አመራሮች ከ1975 እስከ 1991 (ጫካ ከገቡበትና እና ወደ ስልጣን እስከመጡበት ጊዜ ድረስ) የኤርትራን የመገንጠል አላማ ተግባራዊ ለማድረግ በአስገንጣይነት የተሰለፉ፤ አገራችንን የባህር አልባ ለማድረግ በቅጥረኝነት የተሟገቱ፤ የተዋጉ ከሃዲዎች መሆናቸዉ ይታወቃል።

በ1991 የመንግስት ስልጣን ከጨበጡበት ማግስት ጀምረዉ እስከ አሁን ባለዉ ጊዜ ዉስጥ የተነሱለት አላማ ህጋዊ መሰረት እንዲያገኝ፤ የትግራይን ሪፑብሊክ ለመመስረት ያለአንዳች ህዝባዊ ይሁንታ ደፋ ቀና የሚሉ በአንፃሩ ሌላዉ የአገሪቱ ግዛትና ህዝብ ባዘጋጁለት የጎሳ ግጭትና ጦርነት እርስ በርሱ እንዲናቆር እያደረጉት ነዉ። ደካማዋ ኢትዮጵያ ብቻዋን እንድትቀር የመገንጠል አጀንዳ ይዘዉ የሚንቀሳቀሱ ሀይሎችን በያዙት እሳት ላይ ነዳጅ እየጨመሩ፤ ይብሱኑ በሚደርስባቸዉ ግፍና በደል በኢትዮጵያዊነታቸዉ ተማረዉ በትግላቸዉ እንዲገፉበት ለሌላ ግንጠላ ሁኔታዎችን በማመቻቸት ላይ የሚገኙ የዉስጥ አርበኞች መሆናቸዉ በግልፅ ይታያል።

መለስና አብረዋቸዉ በክህደት የተሰለፉት ኢትዮጵያ እንደአገር እንዳትኖር ታጥቀዉ በመስራት ላይ እንዳሉ ከሚያመላክቱን ዉስጥ የተናገሯቸዉንና የፈፀሟቸዉን በቅርበት መመርመር አስፈላጊ ይሆናል።

እንደሚኒልክ ያሉትን መሪዎች ለማንኳሰስና ኢትዮጵያ በአፄ ቴዎድሮስ አማካይነት ከፊዉዳል ስርአት ወደ አንድ የተማከለ ስርአት የተሸጋገረችበትን ወቅት ብቻ ግምት ዉስጥ በማስገባት ጥንታዊ ታሪኳን በመካድ በ100 አመት ሊገድቧት የዳዱ በታሪክ ተወቃሽ ሰዉ እንደሆኑ ይታወቃል።
ሎሬት ፀጋዬ ገብረመድህን ” እሣት ወይ አበባ” በሚል የግጥም መድበላቸዉ ዉስጥ ” የቴዎድሮስ ስንብት ከመቅደላ” የሚለዉን ግጥም ህወሃቶች ” ሦረኔ ” በሚል ርዕስ ባዘጋጁት የግጥም መፅሃፍ ዉስጥ ” ለአንተ ይለቀስልህ!” በማለት የመሳፍነቱን ዘመን አስወግደዉ ለኢትዮጵያ አንድነት የወደቁትን ታላቅ መሪ በድፍረት የሰደቧቸዉ ከሃዲዎች ” ያ ቴዎድሮስ በጀግንነት የወደቁለትን አንድነት ሊያፈርሱ የሚችሉ ጀግኖች እንዳሏት” አፍራሽነታቸዉን እራሳቸዉ መስክረዋል።

የህወሃት መሪዎች ታሪክን በመካድ በኤርትራና በትግራይ ህዝቦች ላይ የአማራዉ ህዝብ ወንጀል እንደፈፀመ የዉሸት ታሪክ የሚፅፉ፡ ሰንደቅ አላማዋን ያዋረዱ፤ የትግራይን ህዝብ በወርቅ በመፈረጅ ለሌላዉ የኢትዮጵያ ህዝብ ያላቸዉን ንቀት እንደመሪ ሳይሆን በተራ የባለጌ ቋንቋ የገለፁ ናቸዉ።
የአገሪቱን ጠንካራ የመከላከያ ሃይል ያፈረሱ፤ የጦር ተቋሞቿን ለኤርትራና ለትግራይ በዘላቂ መከላከያነት ላላቸዉ ስዉር ዓላማ እንዲያገለግል በደካማ አስተሳሰብ ለይተዉ ያስቀመጡና የሰጡ ፡የኢኮኖሚ ሀብቶቿንና ኢንዱስትሪዎቿን በኢንቬስትሜንት ስም ለጥቂቶች መጠቀሚያ ግልፅነት በጎደለዉ መንገድ በማን አለብኝነት ያቀራመጡ፤ የሸጡና የለወጡ፤ የሌሎች የትግራይ አዋሳኝ ከፍለ ሀገሮችን መሬትና ግዛት እየቆረሱ ወደ ትግራይ ያለህዝብ ፈቃድ እንዲካለል ያደረጉ፡ ዘረኞች ናቸዉ።

የአገሪቱን ለም መሬቶች ድሃዉን ገበሬ እያፈናቀሉ ለባእዳን ባለሃብቶች በአመታት ለሚቆጠር ጊዜ እጅግ ርካሽ በሆነ የኪራይ ዋጋ የቸበቸቡ፤ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገዉ ጦርነት ከሁለቱም ወገን በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች የህይወት መስዋእትነት የከፈሉበትን ድል አልጄርስ በጠረጴዛ ዙሪያ በድርድር የሰጡና የተቃወሟቸዉን ሀቀኛ የህወሃት ከፍተኛ አመራር አካላት ለእስራትና ለእንግልት ያደረሱ ከሃዲዎች ናቸዉ።
ለመንግስታቱ ድርጅት ደብዳቤ በመፃፍ፤ በዳኝነት በሄግ ለተሰየመዉ የድንበር ኮሚሽን ከኢትዮጵያዊያን ይልቅ ባዕዳንን በህግ አማካሪነት በመመደብ፡ ተቀባይት የሌለዉን የቅኝ ገዢዎች ካርታ በማስረጃነት አቅርበዉ የባድመንና የኢሮብን ህዝብ ከአያት ቅድመ አያት ርስቱ ጋር አሳልፈዉ ወደ ኤርትራ እንዲካለል የሰጡ የታሪክ ከሃዲ ናቸዉ።

በየክልሉ ዜጎችን በጅምላና የትግራይ ተወላጆችን በግለሰብ ደረጃ ፤ የገደሉ፤ በተለያየ ምክንያት፤ በማሰርና ፤ በማሰቃየት ህይወታቸዉና ኑሯቸዉ በየደረጃዉ ዋስትና እንዲያጣና፤ ተስፋቸዉ እንዲጨልም በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

ህዝቡን ከዳር እዳር ትጥቅ በማስፈታት ግልፅ ባልሆነ መንገድ የትግራይ ተወላጆች በአብዛኛዉ ማለት ይቻላል እንዲታጠቁና እራሳቸዉን እንዲጠብቁ በማድረግ ሌላዉ ኢትዮጵያዊ በራሱ እንዳይተማመንና እራሱን እንዳይከላከል አድርገዉታል።

“አማራዉ በሽግግር መንግስቱ ዉስጥ ዉክልና ተነፈገዉ” በማለት ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስን የመሳሰሉ አገር ወዳዶች አማራዉን ወክለዉ በመናገራቸዉ ብቻ በሃሰት ክስ በእስር እንዲሰቃዩና ህይወታቸዉ እንዲያልፍ መደረጉ አይዘነጋም።

እነዚህ የህወሃት ከሃዲ መሪዎች በመንግስት ላይ የሚነሱ አመጾችን ለመቀልበስ እንደአጋዚ ያሉ ከአንድ ጎሳ የተመለመሉ አልሞ ተኳሽ ወታደሮችን መሳሪያ ደግነዉ በተጠንቀቅ እንዲቆሙ ከማድረግ ባሻገር በአገሪቱ ባሉ በሁሉም መንግስታዊና ድርጅታዊ ተቋሞች ዉስጥ የትግራይ ተወላጆች ቁልፍ በሆኑ የስልጣን ቦታዎች ላይ በዉሳኔ ሰጪነት እንዲቀመጡ አድርገዋል።

የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የልማት ፕሮግራም ለአገሪቱ በመደበዉ የአቅም ግንባታ ወጪና በሌሎችም የትምህርትና የስልጠና መንግስታዊ ወጪዎችና እድሎች አማካይነት የትግራይ ተወላጆች በአገር ዉስጥና በዉጭ አገር በአድልዎ ትምህርታቸዉን እንዲከታተሉ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።

በህዝብ ላይ የሚያደርሱት የሰብኣዊ መብት ረገጣና በደል የጌቶቻቸዉን የምዕራባዊያን ተቃዉሞ እንዳያስከትልባቸዉና ድጋፍ እንዳያሳጣቸዉ አልፎ ተርፎ የአገራዊ አንድነት ራዕይ ያላቸዉንና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾችን ማጥቃት እንዲያስችላቸዉ ” በፀረ ሽብር አጋርነት ” ተላላኪ በመሆን፡ የአገሪቱ አሻንጉሊት ፓርላማ እንኳ ሳያዉቀዉ በጎረቤት አገር የዉስጥ ጉዳይ ጣልቃ በመግባት በሶማሊያ ወረራ መፈፀሙ ይታወቃል።

የፍትህ አካላቱ ዳኞች፤ አቃብያን ህግ፤ ወህኒ ቤት ፤ ፖሊስ የደህንነትና የፀጥታ ሃይሎች፤ ለሙያ ክብርና ለህሊና ነፃነት ከመቆም ይልቅ የድርጅቱ ጉዳይ አስፈፃሚዎች እንዲሆኑ በማስገደድ በአገራችን ፍትህ እንዲረገጥና እንዲዋረድ አድርገዋል።

የአገሪቱ ሠራዊትና በተለይም በመከላከያዉ ቁልፍ የስልጣን እርከኖችና የዕዝ ሰንሰለቶች ላይ የአንድ ጎሳ የበላይነትና ቁጥጥር እንዲሰፍን በማድረግ ከዘረኛዉ የአፓርታይድ ስርኣት ባልተለየ መንገድ የገዢዉ ፓርቲ ህወሃት አጀንዳ የማስፈፀሚያ መሳሪያዎች እንዲሆኑ ከማድረጉም በላይ ለአገርና ለወገኑ የመቆም ታሪካዊ ሚና ያለበት ሰራዊት በባዕድ አገራት ተሰማርቶ ደሙን እየፈሰሰ፡ እንደዉሻ አስከሬኑ በየጢሻዉ እየወደቀና በየጎዳናዉ ላይ እየተጎተተ ለነዚህ ጥቂት ከሃዲ የህወሃት መሪዎች የስልጣን ዕድሜ ማራዘሚያና ከመንግስታቱ ድርጅት የዉጭ ምንዛሬ መሰብሰቢያ ዕቃ አድርጓቸዋል።

መለስና ስብሃት ህወሃት ከስልጣን ከተወገደ ህዝብ እርስ በርሱ የጎሳ ግጭት ዉስጥ እንደሚወድቅ፤ አገራችን በሁትሲና በቱትሲ መካከል በሩዋንዳ እንደታየዉ ሁሉ በደም እንደምትታጠብ፡ ኢትዮጵያ እንደ አገር ልትኖር እንደማትችል በድፍረትና በንቀት ደጋግመዉ በመናገር ዜጎች በፍርሃትና በመሸማቀቅ ወደድንም ጠላን የህወሃትን የበላይነት ተቀብለን ተሸማቀን እንድንኖር ለማድረግ ጥረት ከማድረግ አልተቆጠቡም።

የጫካ እምነታቸዉና ስዉር አጀንዳቸዉ ዛሬም እንደተዳፈነ እሳት በዉስጣቸዉ የሚንቀለቀለዉ እነመለስ የአገሪቱንና የህዝቦቿን ድምር የጥንታዊ ታሪክ፤ ድልና ገድል ዉጤቶች በጠባብ የጎሰኝነት ስሜት ለማዛባት ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ ይነግሩናል።

መለስ በ1992 ከፕሮፌሰር ዶናልድ ሌቪን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ትግራዮች አክሱም አላቸዉ፤ ያ ለጉራጌ ምኑ ነዉ? አገዎች ላሊበላ አላቸዉ፡ ያ ለኦሮሞዉ ምኑ ነዉ? ጎንደሮች የቤተ መንግስት ግንቦች/ካስሎች/ አሏቸዉ፡ ያ ለወላይታዉ ምኑ ነዉ? ” በማለት ያለሃፍረት ተናግረዋል።

አክሱም ሆነ ላሊበላ፤ የጎንደር ቤተ መንግሰቶችም ሆኑ የጅማ አባጅፋር ግቢ፤ የሃረር ግንብ፤ የሶፎሞር ዋሻ፤ አይጠየፍ አዳራሽ ….የእገሌ ያያ እገሌ ሳይባል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ታሪካዊ ቅርሶች ናቸዉ። የአንድ ታሪካዊ ቅርስ ባለሃብቶች የአገሪቱ ህዝቦች በጠቅላላዉ እንጂ ቅርሱ ለመታሰቢያነት ያረፈበት ስፍራ ነዋሪ የሆኑ ጎሳዎች ብቻ አይደለም።
አዲስ አበባ ላይ የተሰራዉ የአሉላ አባነጋ መታሰቢያ ወይንም የአፄ ቴዎድሮስ መድፍ መታሰቢያነት የሁሉም ኢትዮጵያዊ እንጂ ለአዲስ አበቤዎች በባለቤትነት የተሰጠ የታሪክ ሀብት አይደለም። የስልጣን አጋጣሚ በፈጠረላቸዉ ዕድል ተጠቅመዉ “ሁሉን ነገር አዉቃለሁ” የሚሉት መለስ እዉነቱን አጥተዉት እንደሁ እንጂ በአንድ አገር ዉስጥ የሚገኝ ታሪካዊ ቅርስ እዉቅና ተሰጥቶት በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የትምህርትና የሳይንስ ኮሚሽን/ ዩኔስኮ/ ስር ከተመዘገበ የተወሰነ አገር ቅርስ ከመሆን አልፎ አለምአቀፋዊ ቅርስ ይሆናል። ከጎሰኝነትና ከጠባብ አዕምሮ የሚመነጩ ደካማ አስተሳሰቦች ሁሌም ግለኝነትን ሊያንፀባርቁ መቻላቸዉ ግን አይቀሬ ነዉ።

የትግራይ ሪፑብሊክን ለመመስረት ስዉር አጀንዳ ይዞ የተንቀሳቀሰዉ የህወሃት ከሃዲ ቡድን የኮሎኔል መንግስቱ ሃይለ ማርያም ጨካኝ ወታደራዊ አምባገነን መንግስት በፈጠረለት አጋጣሚና የአገር ዉስጥና የዉጭ ፖለቲካዊ ሁኔታዎች ባመቻቹለት መንገድ ለስልጣን መብቃቱን ሲዘነጋዉ ይስተዋላል። በሰልጣን የመቆናጠጡ ሚስጢር ወታደራዊ የዉጊያ ብቃቱ ብቻ መሆኑን ለመስበክ ይቃጣዋል።

መላዋን ኢትዮጵያ እንደቅኝ ግዛት መቆጣጠሩ ትምክህትና ንቀት ከማሳደር አልፎ ለእነዚህ ጥቂት የህወሃት ከሃዲ መሪዎች ባለፉት 20 አመታት ዉስጥ በተለያየ ምክንያት በራሳቸዉ ዙሪያ ያሰባበሱትና ያማከሉት የመከላከያ ትጥቅ ለስዉር አላማቸዉ ስኬት ሊያገለግላቸዉ እንደሚችል የሚያምኑ መሆናቸዉን መጠራጠር አይቻልም።

የአንድ ጎሳን የበላይነት በአገሪቱና በሌሎች ህዝቦቿ ላይ ለመጫን እኒህ ከሃዲዎች ለጊዜዉ ግልፅ ባልሆነ መንገድ ዉስጥ ዉስጡን እንደፍልፈል የሚፈፅሙት በደል፤ አገሪቱን ለማፍረስና ታሪኳን ለመናድ የሚያደርጉት ቡርቦራ አካል መሆኑ በግልፅ የሚታይ ነዉ።

ዛሬ ከሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶች ይልቅ ትግራይ ነፃ ግዛት እንደሆነች ብዙዎች ይገምታሉ። በስሙ ለትግራይ ሕዝብም ሆነ ለጥቂት የህወሃት መሪዎች የግል ብልፅግና የተደራጁት የኤፈርት ድርጅቶች የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ በመጠቀምና የኢትዮጵያን ሀብት በመዝረፍ በስፋት እንዲስፋፉ በመደረግ ላይ ያሉት በአብዛኛዉ በትግራይ ክልል ዉስጥ ተገድበዉ ነዉ።

በመለስና፤ በስብሃት እንዲሁም በአንዳንድ የህወሃት ከሃዲ አመራሮች ዉስጥ አንዳችም የኢትዮጵያዊነት ስሜት እንደሌለ ብዙ ሰዎች መስክረዋል፡ በርካታ ማስረጃዎች ቀርበዋል፡ ስራዎቻቸዉ በተጨባጭ አረጋግጠዋል።
ጫካ የገቡበትንና መሳሪያ ያነሱበትን አላማ ጠንቅቆ ለሚያዉቅ፡ የትግል አጋሮቻቸዉ በሆኑ በራሳቸዉ አባላት ላይ የፈፀሟቸዉን ዘግናኝ ሁኔታዎች በሚገባ ለሚረዳ፡ ለአላማቸዉ ስኬት እንዲረዳቸዉ የጦር መሳሪያ ለመግዛትም ሆነ፤ ተዋጊ የሰዉ ሃይላቸዉን ለማጠናከር በትግራይ ወገኖቻቸዉ ላይ በሃዉዜን የፈፀሙዋቸዉን ዘግናኝ ተግባራት በዉል የተረዳ ሁሉ የነዚህን የታሪክ ከሃዲዎች ማንነት ለማወቅ ሌላ ማስረጃ አያስፈልገዉም።

ፍትህና ዲሞክራሲን በማለት እንደ እነሱ ፕሮግራም ነድፈዉ በተንቀሳቀሱ የፖለቲካ ድርጅቶች ላይ የፈፀሟቸዉ ክህደቶች፡ የአገሪቱን የመንግስት ስልጣን በወራሪነት በተቆጣጠሩ ማግሰት ኤርትራንና የባህር በሯን አሳልፎ በመስጠት በየደረጃዉ አገሪቱ በጎሳ እንድትከፋፈልና ህዝብ በማያቋርጥ ግጭት ዉስጥ እንዲወድቅ የተጫወቱት አፍራሽ ሚና የከሃዲዎቹን ማንነት በግልፅ ይመሰክራል።

በጣሊያን ወረራዎች ወቅት ከወራሪዉ የጠላት ሃይል ጎን በድብቅ ተሰልፈዉ፤ በጥቅምና በስልጣን ተገዝተዉ በወገኖቻቸዉና በአገራቸዉ ላይ የክህደት ወንጀል የሚፈፅሙ፡ ባንዳዎች፤ አሽከሮችና፤ ቅጥረኞች እንደነበሩ የማይካድ ሲሆን የአገራቸዉን ህልዉና በማጥፋት ላይ የሚገኙት መለስና ጥቂት የህወሃት አመራር አካላት ቤተሰባዊ ጀርባቸዉ ከዚህ ክህደት ጋር የተያያዘ መሆኑ በሰፊዉ ይነገራል።

ከኢትዮጵያ በመገንጠል የኤርትራን ነፃ አገርነት ለማረጋገጥ ባነሳዉ ነፍጥ ሻዕቢያ ያዋለደዉና ያሳደገዉ ድርጅት ስልጣን እንደጨበጠ የተሰጠዉን ተልእኮ መፈፀሙ፡ ከዚያም ወዲህ አገራችን ካላት ጥንታዊ ታሪክና ያልተነካ የተፈጥሮ ሀብት ክምችት፤ እንዲሁም ከምትገኝበት መልክአ ምድራዊ አቀማመጥ በመነሳት ለዘመናት አንድነቷና ሉዓላዊነቷ ከሚያሳስባቸዉ የዉጭ ሃይሎች ጋር በአሽከርነት አደግድጎ መቆሙ ጠላትነቱን በግልፅ ያሳያል።
ህወሃትን ለአመፅ ምን እንዳነሳሳዉ በገለፁበት ስራ ፕሮፌሰር ክንፈ አብርሃም “ትግራይ ህመምና ገድል” በሚል ርእስ ባዘጋጁት አጭር ፅሁፍ የአድዋ ጦርነትን በምክንያትነት ጠቅሰዋል። የአድዋ ጦርነት ዉጤት የህወሃት የጥንካሬና የድክመቱ ምንጭ መሆኑን ተናግረዋል።

ለትግራይ ተወላጆች የአድዋ ድል እንደሌሎች ኢትዮጵያዊያን የሚኮሩበት እንደሆነ የጠቀሱት ፀሃፊ ጦርነቱ በትግራይ ላይ ከፍተኛ ጫና የፈጠረ፤ በሺዎች የሚቆጠሩት የህይወት መስዋትነት በመክፈላቸዉ ብቻ ሳይሆን ከመላ አገሪቱ የተመመዉን ጦር በመቀለብ እንደተጎዳች ገልፀዋል።

በድል የተጠናቀቀዉ ጦርነት የትግራይ ድቀት የጀመረበት ወቅት እንደሆነ በመጥቀስ ከአድዋ ጦርነት በሁዋላ አፄ ምንልክ ግዛታቸዉን በደቡብና በምዕራብ ሲያስፋፉ እንደነበርና የትግራይ ተወላጆች ከአረቦች፤ ከግብፆች፤ ከቱርኮች፤ ከጣሊያኖችና ከማህዲስቶች ጋር በተደረጉ ጦርነቶች የመጀመሪያዎቹ ገፈት ቀማሽ የመሆናቸዉን ያህል ተጠቃሚ እንዳልሆኑ፤ እኩልነታቸዉ እንዳልተጠበቀ፤ የተሻለ የወደፊት ህይወት የመገንባታቸዉ ፍላጎት ከአፄ ዮሃንስ በሁዋላ የተገደበ መሆኑን ፕሮፌሰር ክንፈ ገልፀዋል።

የአፄ ዮሃንስ ሞትና በሰሜን የአገሪቱ ክፍል በኤርትራ መፈጠር ምክንያት የትግርኛ ተናጋሪዉ ህዝብ ለሁለት መከፈል የኢትዮጵያን ታሪክ እንደለወጠዉ ፕሮፌሰር ክንፈ ያነሱትን መላ ምት መነሻ በማድረግ “ፍኖተ ገድል” የሕዝባዊ ወያኔ ሐርነት ትግራይ ታሪካዊ አነሳስና ጉዞ በሚል ርእስ በቅርቡ ብስራት አማረ የተባሉ ሰዉ በሌላ ስራ ሃሳቡን ለማጠናከር ሞክረዋል።

እኒህ የቀድሞ የህወሃት የደህንነት ሹም ከሃዲ ግለሰብ ለብዙ ንፁሃን ዜጎች ሞት፤ እስራትና ግርፋት ተጠያቂ ሊሆኑ ሲገባ በአሁኑ ወቅት በስለላ ተግባር ተሰማርተዉ በዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ ናቸዉ። ግለሰቡ ባሳተሙት በዚህ መፅሃፍ የዳግማዊ ምኒልክ ወደ ሥልጣን መምጣት ኢትዮጵያ አሁን ድረስ የገጠሟትን ሰፊና ውስብስብ ችግሮች ያስከተለ ክስተት እንደሆነ ለመግለፅ ሞክረዋል።

በማያዳግም ሁኔታ የተመታዉን ዘመነ መሳፍንት ተከትሎ በተለይም ከአፄ ምኒልክ በሁዋላ የንጉሰ ነገስቱ መንግስት ስልጣን ሸዋ ላይ ማክተሙ ኢትዮጵያ የ100 አመት ታሪክ ያላት አገር አድርገዉ አፍራሽ ተልእኮ ያላቸዉ መለስና ደጋፊዎቻቸዉ የህወሃትን አላማ ለማራመድ ይረዳል የሚሏቸዉን አዲስ የፈጠራ ታሪክ ለመፃፍ መነሳታቸዉ ከታሪክ ከሃዲነት ዉጭ ሌላ ሊሆን አይችልም።

የአድዋ ድል ውጤት ለኢትዮጵያ መከፋፈልና አገሪቱን የባህር ወደብ አልባ እንድትሆን ያደረገ እንደሆነና የአክሱም ሥልጣኔ ባለቤት የትግራይ ሕዝብና ትግርኛ ተናጋሪው የኤርትራ ሕዝብ ብቻ እንደሆነ በመግለፅ መለስና ቢጤዎቻቸዉ በኢትዮጵያ ህዝብና ጥንታዊ ታሪክ ላይ ወንጀል በመፈፀም ላይ እንዳሉ አያጡትም። የሚወስዱት እርምጃና የሚፈፅሙት ክህደት ግን ያለ ምክንያት እንደሚፈፀም መቁጠር የለብንም።

መለስ፤ ስብሃት ነጋ፤ አባይ ፀሃዬ የመሳሰሉት የህወሃት ከሃዲ መሪዎች አፍራሽና ስዉር አላማ እንዳላቸዉ የሚያመላክቱ በርካታ አካሄዶች እንዳሉ ለአፍታም ቢሆን መዘንጋት የለብንም።
አድብተዉ ጊዜ፤ አጋጣሚና ምቹ ሁኔታ ከመጠበቅ ዉጭ በኢትዮጵያና በኢትዮጵያዊነት አምነዉ አብረዉን እንዳልቆሙ በርግጠኝነት መናገር የሚያስችሉ አሳማኝ ነገሮች አሉ። በኢትዮጵያዊነቱ የሚያምነዉ ህዝብ በስተመጨረሻ የሚገልፁለትን አፍራሽና ስዉር አላማ እንደማይቀበል ልቦናቸዉ ቢያዉቀዉም፤ የሚገድሉትን እየገደሉ፤ የሚያጋጩትን እያጋጩ “በሽብርተኝነት” “ህገ መንግስቱን በሃይል ለመናድ” “በአገር ክህደት” እና በመሳሰሉት የሃሰት ክሶች ሽመልስ ከማልን የመሳሰሉ ለሆዳቸዉ የተንበረከኩ ከሃዲዎች እስካሉ ድረስ በሚያስቀምጧቸዉ አስገዳጅ ሁኔታዎች ሁሉ ሞክረዉ ካልተሳካላቸዉ ትተዉ ወደ ቻይና እንደሚኮበልሉ ለብዙዎች ግልፅ እየሆነ ያለ ሃቅ ነዉ።
እነዚህ ጥቂት የህወሃት ከሃዲዎች ጥለዉ በሚያልፉት ሴራ ሊቀጣጠል የሚችለዉን እሳት እየተቃጠሉ ማጥፋት በኢትዮጵያዊነታቸዉ የሚያምኑ ሃይሎች ሁሉ ታሪካዊ ግዴታ ይሆናል።
የትግራይ ህዝብ ለኢትዮጵያ አንድነት ያለዉን የማይናወጥ አቋም፡ ኢትዮጵያዊነቱንና ለሃይማኖቱ ያለዉን ፍፁም እምነት ማንም የሚክደዉ አይደለም።

ዳግማዊ አፄ ምኒልክ የተከተሉት የተዛባ የአማራነትና የኢትዮጵያዊነት ፍልስፍና አገሪቱን ለውድቀትና ለመበታተን አሳልፎ እንደሰጠ ብስራት አማረን የመሳሰሉት የመለስንና የቢጤዎቻቸዉን ስዉር የክህደት አላማ ለማስፈፀም በንፁሃን ህዝብ ደም የተጨማለቁ ገዳዮች አዲስ ታሪክ ለመፃፍ መዳዳታቸዉ ያለ ምክንያት እንዳልሆነ ለሁላችንም ግልፅ እየሆነ ነዉ።

እነዚህን የትግራይ ሪፑብሊክ ምስረታን ለማገዝ ከወዲሁ በህወሃት ስም በመዘጋጀት ላይ ያሉትን የታሪክ ቅጥፈቶች ከሚያራምዱት መካከል የኢትዮጵያን አንድነትና ሉኣላዊነት ለማፍረስ በየወቅቱ በንቀትና በትምክህት የሚናገሩት ስብሃት ነጋ ከህወሃት ዉጭ ያለዉን የኢትዮጵያ ህዝብ “በውሸት ታሪክ የሚነዳ፡ እጅግ ከፍተኛ አቅም ያለው ኃይል” ብለዉ ሲጠሩ እራሳቸዉንና ብጤ ከሃዲዎችን ደግሞ “እውነት ፈላጊ ጥቂትና አቅመ ደካማ ” በማለት ገልፀዋል።

በጠመንጃ ወደ ስልጣን ስለመጡ ዛሬ ” ሁሉ በእጄ ሁሉ በደጄ” በሚል ትምክህትና ንቀት ሰፊዉን ህዝብ “በዉሸት ታሪክ የሚነዳ” በማለት እኒህ የሞራል ብቃት የጎደላቸዉ ግለሰብና አብረዋቸዉ የቆሙት ከሃዲዎች ያለአንዳች የጠለቀ እዉቀት የታሪክ ተመራማሪዎች ያረጋገጡትን ሃቅ በማዛባት አዲስ ተረት በመፃፍ የህወሃትን አገር የማፍረስ ክህደትና የትግራይ ሪፑብሊክ ምስረታን እዉን ሊያደርጉት እንደማይቻላቸዉ ግን ሊረዱት ይገባል። የአንድ አገር ህዝቦች ድልም ሆነ ሽንፈት፡ ነፃነትም ሆነ ባርነት፤ ብልፅግናም ሆነ ዉድቀት የጋራ ቅርስና ዉርስ መሆኑን መገንዘብ ያሻል። በርግጥ ሁሉም እኩል አስተዋፅኦና ፅናት ላይኖራቸዉ ይችላል።

አስተያየታችሁን በሚቀጥለዉ አድራሻ ግለፁልኝ። [email protected]