ስር እየሰደደ በመሄድ ላይ ስላለዉ የኢትዮጵያ የሰብኣዊ መብት ረገጣ የተነጋገረ ሕዝባዊ ስብሰባ በለንደን ተካሄደ
የፋሽስቱ መለስ ዜናዊ አገዛዝ ከጊዜ ወደ ጊዜ በህዝብ ላይ እየፈጸመ ስላለው የሰብኣዊ መብት ረገጣ በሰፊው የተነጋገረ አንድ ታላቅ ሀዝባዊ ስብሰባ ከትናንትና ወዲያ እሁድ (16/10/2011) በእንግሊዝ አገር በሎንደ ከተማ በፍሬንድ ሃዉስ አዳራሽ ውስጥ መካሄዱን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመለከተ።
ቁጥራቸው ወደ ሁለት መቶዎች የሚገመቱ ኢትዮጵያዊያን በተገኙበት በተካሄደው በዚህ ታላቅ ስብሰባ ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የ3ኛዉ አለም የሁሉም የፓርላማ ቡድኖች ህብረት ሊቀመንበር የሆኑት የተከበሩ ካዉንስለር ሙሽራክ ላሺር መሆናቸው ተያይዞ የደረሰን ዘገባ አመለከተ። ካዉንስለሩ በመክፈቻ ንግግራቸዉ በኢትዮጵያ ዉስጥ ያለዉ የሰብኣዊ መብት አያያዝ እጅግ አሳሳቢ እንደሆነ በመግለፅ ከዚህ በፊት በተመሳሳይ ምክንያት የሶስተኛዉ አለም ህብረት የፓርላማ ቡድን ከኢትዮጵያ የዲሞክራሲና የሰብኣዊ መብት ተሟጋቾች ጋር በመተባበር ሁለት የህዝብ ስብሰባዎች ማካሄዱን ገልጸው ፤ በኢትዮጵያ ዉስጥ ገንዘብና ስልጣን ከፍተኛ የሆነ ሙስናን ብሎም የሰብኣዊ መብት ረገጣን ሊያስከትሉ እንደቻለ አስረድተዋል።
“ሕዝብ በረሃብና በድህነት በሚሰቃይባት አገር ጠ/ሚኒስትሩና ደጋፊዎቹ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ በዉጭ አገር በማካበት ላይ ናቸው ያሉት ካውንስለር ሙሽራክ፤ የምእራቡም አለም “በፀረ ሽብር ተባባሪነት” ስም በህዝብ ላይ የሚደርሰዉን የመብት ጥሰት ችላ ብለውታል፤ ስለዚህ ኢትዮጵያዊያን ህብረት ፈጥረዉ በጋራ መንቀሳቀሳና በለንደን በሚገኙት በፓርላማ ተወካዮቻቸዉ አማካይነት በህዝብ ላይ የሚደርሰዉን ግፍና ስቃይ የብሪታኒያ መንግስት ይበልጥ እንዲረዳዉ ማድረግ እንደሚኖርባቸው በማሳሰብ በመጪዉ ነሃሴ ወር በእንግሊዝ ፓርላማ ውስጥ በኢትዮጵያ ስለሚካሄደው ምርጫ ውይይት እንደሚካሄድ ጠቁመዋል።
ማስ አድቮኬሲ ፎር ሂዩማን ራይት ኢን ኢትዮጵያ፤ የተባለዉ ቡድን ባዘጋጀዉ በዚህ አራት ሰዓታት በፈጀ ስብሰባ ላይ ንግግር ያደረጉት ሌላው ተጋባዥ እንግዳ በቅርቡ ኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ቢሮ ከቢቢሲ ኒዉስ ናይት ጋር በመተባበር በኢትዮጵያ ለድሃዉ ህብረተሰብ የሚሰጠዉ የዉጭ ርዳታ የገዢዉ ፓርቲ/ህወሃት/ የፖለቲካ መጨቆኛ መሳሪያ መሆኑን ያጋለጡት ጋዜጠኛ አንገስ ስቲክለር ነበሩ።
ጋዜጠኛ አንገስት ስቲክለር ባደረጉት ንግግር እሳቸዉና ባልደረቦቻቸዉ ያጠናቀሩትን መረጃ የኢትዮጵያው አገዛዝ አምኖ አለመቀበሉ የሚጠብቁት ነገር እንደነበረ ገልጸው ፤ በየገጠሩ ተዘዋዉረዉ ያገኙት ማስረጃ በእጃቸዉ እንዳለና በሰሩት ስራ ሙሉ እምነት እንዳላቸዉ ጠቅሰው ፤ በተዘዋወሩባቸዉ መንደሮችና ሰፈሮች ዉስጥ መረጃ የሰጧቸዉን ድሃ ገበሬዎች የመለስ መንግስት የፀጥታ ሃይሎችን በማሰማራት፤ በማሰስና በማፈላለግ በንፁሃን ዜጎቹ ላይ ያደረሰባቸዉ ወከባና እንግልት እጅግ አሳዛኝ እንደሆነ ገልጸዋል።
የመለስ አገዛዝ በኦጋዴን ሶማሌ ክልል በህዝብ ላይ የሚፈፅመዉን የሰብኣዊ መብት ጥሰት ለመከታተል በሚስጢር የገቡትን ሁለት የስዊድን ጋዜጠኞችና ሌሎችም ኢትዮጵያዊያን ጋዜጠኞችና የተቃዋሚ ድርጅት መሪዎችን በሽብርተኝነት እንዳሰራቸዉና ክስ እንደመሰረተባቸዉ አንገስ አስታዉሰዉ፣ በህግ ወንጀለኛነታቸዉ ሳይረጋገጥ ጠ/ሚር መለስ ሽብርተኞች ናቸዉ በማለት ፍርድ መስጠቱን በአገሪቱ ውስጥ እየተካሄደ ያለውን የፍትህ አሰራር ምንነት ያሳያል ብለዋል።
የኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ቢሮ፤ የብሪታኒያ መንግስት የሚሰጠዉ የርዳታ ገንዘብ ለተረጂዎች ላለመድረሱ አሳማኝ ማስረጃ እያለ የአለም አቀፍ የዉጭ ርዳታ የካቢኔ ሚኒስትር አንድሪዉ ሚቼል ስለጉዳዩ ለማሰተባበል ያደረጉት ጥረት ወይ ባለማወቅ ወይ ሆን ተብሎ የተፈፀመ ክህደት መሆኑን የጠቀሱት ጋዜጠኛ አንገስት፣ ግብር ከፋዩ የብሪታኒያ ህዝብ እዉነቱን ማወቅ መብቱ እንደሆነ በማመን ድርጅታቸዉ የሚኒስትሩን ማስተባበያ በቀላሉ እንደማይመለከተዉና ሌሎች ተጨማሪ ጥያቄዎች መነሳታቸዉን አስረድተዋል።
በማያያዝም በአገሪቱ በመካሄድ ላይ ያለዉ የሰብኣዊ መብት ረገጣ በገለልተኛ አካል እንዲጣራ ለተባበሩት መንግስታት ድርጅት ልዩ ራፖርተር ጥያቄ መቅረቡንና ራፖርተሩም እንዲጣራ አምኖ ጥያቄዉን መቀበሉን አስረድተዋል።
ጋዜጠኛ አንገስት ስቲክለር፤ መለስና እርሱ የሚመራው ፓርቲ በቢሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ ብሪታኒያን ጨምሮ ከምእራቡ አለም በገፍ እየተቀበሉ የኢህአዴግ ደጋፊ ያልሆኑትን ለማጥቃትና በረሃብ ለመቅጣት በፖለቲካ መሳሪያነት እየተጠቀሙበት እንዳለ ያጋለጡ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባለዉለታ በመሆናቸዉ ተሰብሳቢዉ ለጋዜጠኛ ስቲክለር ያለዉን አድናቆት በከፍተኛ ጭብጨባ እንደገለጸላቸው ታውቆአል።
የኢንቬስቲጌቲቭ ጆርናሊዝም ቢሮ በኢትዮጵያ ዉስጥ በድብቅ በመዘዋወር ከድሃዉ ገበሬና ህብረተሰብ ጋር በመነጋገር አገሪቱ ከዉጭ የምታገኘዉ ርዳታ የገዢዉን ፓርቲ /ህወሃት/ ለሚደግፉ ብቻ እንደሚዉል ያጋለጡበት የ22 ሰዓት የቪዲዮ ፊልም ቀረፃ በእጃቸዉ እንዳለና ከዚህ ዉስጥ የተጠቀሙት የ17 ደቂቃ ብቻ እንደሆነ ጋዜጠኛ አንገስ ለኢሳት በሰጡት አጭር ኢንቴርቪው መግለጣቸውን ኢሳት በትናንትናው እለት ዜናው ዘግቦአል።