የቤነሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዝዳንት የነበረው የወያኔ ተለጣፊ ከሥራ ታገዶ በቁም እስር ላይ እንደሚገኝ ታወቀ
በተለያዩ አንስተኛ ጥቅማጥቅሞች በመደለል በአገራቸውና በወገናቸው ላይ ታሪክ ይቅር የማይል ወንጀል በመሥራት የዘረኛውን አምባገነን ስርአት አገዛዝ እድሜ ለማራዘም ከፍተኛ አስተዋጽኦ ሲያደርጉ ከነበሩ በርካታ የወያኔ ሆድ አደሮች መካከል አንዱ የሆነው ያረጋል አይሸሹም ከሰሞኑ ከሥራ እንደታገደና በቁም እስር ላይ እንደሚገኝ ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ አጋለጠ።
ያረጋል አይሸሹም ቀደም ሲል የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ፕሬዚዳንት ሆኖ ሲያገለግል ከቆየ ቦኋላ በፖለቲካ ታማኝነት ለወያኔው ቁንጮ መለስ ዜናዊ የሚሰጠው አገልግሎት እያነሰ በመምጣቱ ከክልል ፕሬዝዳንትነት ተነስቶ በአሁኑ ወቅት የተወካዮች ምክር ቤት አባልና የኅብረት ሥራ ማኅበራት ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ሆኖ እያገለገለ እንደሆነ ቢታወቅም በወያኔ ፓርላማ አባልነቱ ፤ የነበረው ያለመከሰስ መብቱን ጭምር እንደተገፈፈ የደረሰን መረጃ አክሎ ገልጾአል።
እንደ ምንጮቻችን ዘገባ መሰሪው የወያኔ አገዛዝ በያረጋል አይሸሹም ላይ ፊቱን ያዞረበት የሕግ፣ የፍትሕና የአስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በመባል በሚታወቀው የወያኔ ቡድን በሙስና ወንጀል እንደተጠረጠረ ከተገለጸለትና ያለመከሰስ መብቱ እንዲነሳ የቀረበለትን ጥያቄ መቀበሉን ይፋ ካደረገ ቦኋላ መሆኑ ታውቆአል።
ያረጋል አይሸሹም አሁን ለተዘፈቀበት ቅሌት የተጋለጠው የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበረበት ወቅት በክልሉ እንዲሠራ በጀት ከተያዘላቸው የሦስት ትምህርት ቤቶች ማሰሪያ ገንዘብ ላይ ከክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ጋር በመመሳጠር ከ83 ሚሊዮን ብር በላይ ለግል ጥቅሙ ማዋሉ በማስረጃ በመረጋገጡና በቂ አመላካች ነገሮች በመኖራቸው ነው ተብሎአል።
በአሁኑ ጊዜ በቁም እስር ላይ የሚገኘው ያረጋል አይሸሹም የያዘውን የመንግስት ንብረት ካስረከበ በሁዋላ ወደ እስር ቤት እንደሚወርድም ተያይዞ የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ገልሰቦች የወያኔን አጀንዳ ሙሉ በሙሉ እስካስፈጸሙና ስብዕናቸውን በቁሳዊ ችሮታ ለውጠው ታዛዥነታቸውንና ታማኝነታቸውን እስካረጋገጡ ድረስ ለተዘፈቁበት ሙስና ተጠያቂ እንደማይሆኑ በተረጋገጠበት የመለስ ዜናዊ አስተዳደር፤ የያረጋል አይሸሹምን በሙስና ወንጀል ከሥራ መታገድና ለክስ መቅረብ ፖለቲካዊ ይዘት ያለው ነው በማለት ለግለሰቡ ቅርበት ያላቸው ምንጮች ይናገራሉ። ለዚህም የሚሰጡት ምክንያት ግለሰቡ የክልሉ ፕሬዚዳንት በነበረበት ወቅት፤ ህወሀት በክልላቸው የሚያደርገውን ጣልቃ ገብነት አጥብቆ በመቃወሙ፣ በእነ አባይ ጸሀዬ የተመራ ቡድን ማስጠንቀቂያ ሰጥቶት እንደነበርና ማስጠንቀቂያውን ተከትሎም በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል የሚገኙ ተቃዋሚዎችን ትደግፋለህ የሚል ክስ ቀርቦበት ከፕሬዚዳንትነት እንዲነሳ እንደተደረገ ይገልጻሉ።
ያረጋል አይሸሹም ከወያኔ አመራር ጋር እልህ እንደተጋባ “ለደህንነቴ እሰጋለሁ” በማለት በህክምና ሰበብ ወደ ኬንያ ከተጓዘ ቦኋላ በዩጋንዳ በኩል ወደ ካናዳ በመሄድ ጥገኝነት ለመጠየቅ ሙከራ አድርጎ እንደነበርና የጥገኝነት ማመልከቻውን ይከታተሉለት ለነበሩት ሳያማክር ብድግ ብሎ ወደ አገር ቤት እንደተመለሰና መልሶ ለዘረኛው የወያኔ አገዛዝ ማጎንበሱን እንደቀጠለ መዘገቡ ይታወሳል።
ከምርጫ 97 ቦኋላ ወያኔን እየተዉ የሚኮበልሉ ባለስልጣናት ቁጥር በመጨመሩ ስጋት የገባው የመለስ አገዛዝ፤ የያረጋል መኮብለል ለሌሎች አረአያነት እንዳይኖረው ፈርቶ የሆዱን በሆዱ በመያዝ ጊዜያዊ ምህረት እንዳደረገለትና ከነበርበት የክልል ፕሬዝዳንትነት አንስቶት በቅርብ ርቀት ሊቆጣጠረው ወደሚችልበት አዲስ አበባ በማምጣት በፌደራል መንግስቱ መስሪያቤት እንደመደበው ይታወቃል። በወያኔ ጣልቃ ገብነት ተማሮና ለህይወቱ ሰግቶ ከአገር ወጥቶ የነበረው ያረጋል አይሸሹም በወቅቱ በቅርበት ይገናኙት ለነበሩ ሰዎች “አገር ቤት ጥሎአቸው በመጣ ቤተሰቦቹ በማሳበብ “የስደትን ህይወት ሊለምደው እንደማይችል ገልጾ እንደተመለሰ ምንጮች ይናገራሉ።
ወያኔ ሥልጣን ላይ ለመደላደል እንደመሳሪያ የተጠቀመባቸውን የሌላ ብሄረሰብ አባላትን እንደአገዳ ከመጠጣቸው ቦኋላ አንድ በአንድ ጎዳና ላይ አውጥቶ እንደምጥላቸው ይታወቃል።