በተለያዩ የአውሮፓና የሰሜን አሜሪካ ሃገራት ውስጥ ሆነው የፋሽስቱን የመለስ ዜናዊን አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም በስለላ የተሰማሩ ኢትዮጵያዊያንን እየተከታተለ የሚያጋልጥ አንድ ግብረሃይል እንቅስቃሴ መጀመሩ ታወቀ

“ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በአገራችንንና በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለው ሰቆቃ ሰልባ ነኝ “በሚል ሽፋን የሃሰት ማስረጃ በማቅረብ በአውሮጳና በሰሜን አሜሪካ የፖለቲካ ጥገኝነት ካገኙ ቦኋላ መልሰው በአገር ቤት ውስጥ የሚፈጸመውን የመብት አፈናና የሰብአዊ መብት ጥሰት ለማጋለጥ የሚንቀሳቀሱትን ኢትዮጵያዊያንን፣ በመሰለል ለአገዛዙ መረጃ የሚያቀብሉ ኢትዮጵያዊያንን ተከታትሎ የሚመዘግብና እንደአስፈላግነቱ ለየሚኖሩበት አገራት መንግሥታት የሚያጋልጥ  አንድ ኮሚቴ ተቋቁሞ  ከሰሞኑ እንቅስቃሴ መጀመሩን  ለዝግጅት ክፍላችን የደረሰ መረጃ አመለከተ።

በደረሰን መረጃ መሠረት የኮሚቴው መቋቋም አስፈላጊ የሆነበት ምክንያት ፤ ከአገራችን ሁኔታ ጋር ተመሳሳይነት ባለው ሁኔታ፣  በውጪ አገር የሚኖሩ ሶሪያዊያን በበሽር አል አሳድ የሚመራው አምባገነን የአናሳ መንግሥት በአገራቸው ህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ሰቆቃ ለማጋለጥ የሚንቀሳቀሱትን ሶሪያዊያን እየሰለለ ለአገሩ መንግሥት መረጃ የሚያቀብል አንድ ትውልደ ሶሪያ ተግባሩ በአሜሪካን አገር ተደርሶበት የወንጀል ክስ የተመሰረተበት በመሆኑ እንደሆነና፤ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በተመሳሳይ ሆኔታ ያሰማራቸው በዚህም ተግባራቸው የሚታወቁ ሰዎች በመኖራቸው እንደሆነ ለማወቅ ተችሎአል።

በዩናይትድ ስቴት የቨርጂኒያ ክፍለሃገር ነዋሪ የሆነው  መሃመድ አናስ ሱኢድ  በፖለቲክ ጥገኝነት ገብቶ የአሜሪካ ዜግነት ካገኘ ቦኋላ መልሶ ለሶሪያ አንባገነን መንግስት እንደሚሰልል ለኤፍ ቢ አይ መረጃ ከደረሰ ቦኋላ በተደረገበት ክትትል ቁጥጥር ሥር ውሎ ክስ እንደተመሰረተበት ይፋ ከሆነ ወዲህ ፤ መለስ ዜናዊ የስልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ባቋቋመው የዲያስፖራ መምሪያ አማካኝነት በትናንሽ ጥቅማ ጥቅሞች በርካታ ሰላዮችን ገዝቶ ኢትዮጵያዊያኑን ለማሰለል እያደረገ ያለው እንቅስቃሴ በቸልታ መታየት እንደለሌበት የብዙዎች እምነት እና መነቃቂያ ሆኖአል ተብሎአል።

ኢትዮ ሚዲያ በመባል የሚታወቀው ድረገጽ ባለፈው ሳምንት እንደዘገበው  ከአውሮፓ የኮበለሉ ከፍተኛ የኤምባሲ መልእክተኞች በተለይ በቤልጂየም እና በሆላንድ ነዋሪ ኢትዮጵያውያንን እየሰለሉ መረጃ የሚያስተላለፉ ሰላዮች ስም ዝርዝር ለዝግጅት ክፍሉ መላካቸውን ገልጾአል። ድረ ገጹ በበኩሉ አክሎ እንደገለጸው የእነዚህን ሰላዮች ስም ዝርዝር ከህግ ባለሞያዎች ጋር ተማክሮ ይፋ እንደሚያደርግና፣ እነኝህ የወያኔ ሰላዮች በከፊል ለዚሁ እኩይ ተግባር በወያኔ በስደተኝነት ስም ወደ አውሮፓ የተላኩ ሲሆን ሌሎቹ ደግሞ በአዲስ አበባ የመኖርያ ቤትና ቦታ ለማግኘት ሲሉ በረሃብ እያአለቀ ባለው ወገናቸው ላይ ይቅር የማያሰኝ ደባ እየፈጸሙ ያሉ መሆናቸውን ገልጹአል።

በርካታ መረጃዎች እንደሚያረጋግጡት የዘረኛው መለስ አገዛዝ  በአሜሪካ፣ በአውሮፓ፤ በአውስትራሊያ እና በአፍሪካ ሀገሮችም ሳይቀር በሚሊዮን ዶላር በጀት በመመደብ ከረጂም አመታት በፊት ጀምሮ ሰላዮቹን እንዳስማራ ከኮበለሉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ሰራተኞች እንዲሁም በውጪ ሃገራት ለኤምባሲዎች በማገልገል ላይ ከሚገኙና ቅርበት ካላቸው ምንጮቻችን ያገኘነው መረጃ ይጠቁማል።

አሜሪካዊ ዜግነት ያለው  የ47 አመቱ ሶርያዊ መሃመድ አናስ ሱኢድ  በውጭ የሚኖሩ ሶርያውያንን የፖለቲካ እንቅስቃሴና የተቃውሞ ሰልፎችን በስእል እና በድምጽ በመቅረጽ፤ በስደት የሚኖሩትን በማስፈራራት እና በልዩ ልዩ ዘዴዎች በማወክ፤ ተግባር ላይ ተሰማርቶ የነበረ በመሆኑና መረጃዎችንም ለባሻር አል አሳድ መንግስት በማቀበል ሲሰራ እንደነበር የተደረሰበት በስደት የሚኖሩ የሶርያ ተወላጆች ባደረጉት ክትትል እና ጥቆማ መሆኑ ታውቆአል።

ኢትዮጵያዊያን ስደተኞች በመካከላቸው ሆነው የወንጀለኛውን መለስ ዜናዊ አገዛዝ ዕድሜ ለማራዘም ሌት ተቀን የስለላ ሥራ የሚሰሩትንና መረጃ በማቀበል የሚታወቁትን ሰላዮች በተደገፈ ማስረጃ በማጋለጥ እንዲተባበሩ አስተባባሪ ኮሚቴው ጥሪውን እያቀረበ በዝግጅት ክፍላችን

የስልክ አድራሻ

0044203 286 9661     ወይም

0044 208 133 5670 እንዲሁም

በኢመል አድራሻችን [email protected] ወይም

[email protected]

ብትልኩልን ጥቆማችሁን ለኮሚቴው የምናደርስ መሆናችንን በአክብሮት እንገልጻለን።