በአርባ ምንጭ ነዋሪዎችና በወያኔ ዘረኛ አገዛዝ መካከል የተፈጠረው ፍጥጫ አሣሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱ ተሰማ

ዘረኛውና ፋሽስቱ የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለው  አፈናና ጭቆና ባስመረረው የአርባምንጭና አካባቢዋ ነዋሪዎችና በአገዛዙ መካከል በተነሳው ውዝግብ እስካሁን ወደ 65 የሚጠጉ ሰዎች መታሰራቸውን የኢትዮጵያ ሳታላይት ቴለቪዥን ኢሳት የዘገበ ሲሆን፤ አካባቢው በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ እንደሚገኝ ለማወቅ ተችሎአል።

ኢሳት በአካባቢው ያሉትን ወኪሎቹን ዋቢ አድርጎ እንዳጠናቀረው መረጃ ከሆነ፤ውጥረቱ ይበልጥ እየተባባሰ የመጣው፤ ከሁለት ሳምንት በፊት በወረዳቸው፣ በዞናቸውና በቀበሌያችው በተንሰራፋው የመልካም አስተዳደር እጦት ምክንያት፣  ለችግር መጋለጣቸውን አዲስ አበባ በመምጣት ለመገናኛ ብዙሀን ይፋ ያደረጉ የአርሶ አደሮች ተወካዮች ለእስር መዳረጋቸውን ተከትሎ ነው።

በመጀመሪያ የታሰሩት፤ አቤቱታ ለማቅረብ  አዲስ አበባ የመጡት አቶ ዳሞታ ኡቃ፣ አቶ ዶኮ ኮዶ ፣ አቶ ዳንኤል ዳርዬ እና ሌሎች የቀበሌው ሶስት አርሶ ደሮች ሲሆኑ፤ አሁን ግን የታሳሪዎቹ ቁጥር አስከ 65 እንደሚደርስ ተነግሯል።

“አዲስ አበባ ድረስ ሄዳችሁ ለተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጉዳዩን ተናግራችኋል” በሚል ሰበብ የአካባቢው ፖሊስ አርሶ አደሮቹን ማሰሩን የጠቀሱት ምንጮች፤ እስረኞቹም፤- በላንቴ ፣ በጨንቻ እና በአርባ ምንጭ ከተማ ፖሊስ ጣቢያዎች እንደሚገኙ  ገልፀዋል።

ምንጮች እንደሚሉት፤  “አለ” በተባለው ችግር ዙሪያ ማጣራት እንዲያካሂዱ ከተመረጡ የአጣሪ ቡድኑ አባላት መካከልም፤ ሁለት የቀበሌው የግብርና ባለሙያዎች ከስራ ታግደዋል። አንዳንድ የላንቴ ቀበሌ ወጣቶችም እስርን በመፍራት  ወደ አርባ ምንጭ ከተማ እየሸሹ እንደሆነ ተናግረዋል።

ባለፈው ሳምንት  “ስብሰባ ስላለ፤ ፖሊስ ጣቢያ ድረስ መጥታችሁ ተሰብሰቡ” የሚል ትዕዛዝ በየቀበሌው መስተዳድሮች አማካይነት ሲተላለፍ፤  ህብረተሰቡ “መሰብሰቢያ አዳራሽ እያለ ፖሊስ ጣቢያ ግቢ ውስጥ አንሰበሰብም” ማለቱን ተከትሎ በርካታ ሰዎች መታሰር እንደጀመሩ ኢሳት ዘገቦ ነበር።

በስፍራው የሚንቀሳቀሱት ወኪሎቹን ጠቅሶ ዜናውን የዘገበው ኢሳት እንዳመለከተው  የወያኔ ታጣቂዎች በህብረተሰቡ ተወካዮች ላይ የወሰዱት የጅምላ እሰር እርምጃ፤ በአሁኑ ጊዜ ውጥረቱንና ፍጥጫውን እጅግ እንዳባባሰውና ወያኔ እየወሰደ ባለው እርምጃ  ያኮረፈው የአካባቢው ህዝብ፤“መልካም አስተዳደር አጥተናል”ለሚለው አቤቱታችን የአገዛዙ ምላሽ እስር ከሆነ፤ ከእንግዲህ የምናደርገውን እናውቃለን“ ማለታቸው ተዘግቦአል።