“የት ነበራችሁ???……” ከአቢይ ኢትዮጵያዊ

ሥጋዊ-ወመንፈሳዊ
ብትጠየቁ ዛሬ፤ለሞት ሽረት መልሳችሁ፤
የደም-ዕዳ እንዳትከፍሉ:
ትናንትስ የት ነበራችሁ???
ሕዝቡ በአንድነት ሊቆም:-ብሶቱ አመፅን ፀንሷል፤
በሰላም ሥም ሲረገጥ ሃያ ዓመታትን ታግሷል::
አሁን ግን በቁሙ እንዳሞቶ ሰበብ ብቻነው የሚሻው፤
ርኩስ ሲፈጠር ከጥንትም:-
ሞት ብቻ ነውና ማርከሻው።
እናም ! ልብ እናድርግ የሕዝብ ዳኝነት ሳይመጣ፤
በማይቀር አመፅ ተወግረን ባደባባይ-ሞት ሳንቀጣ፤
ይቅርታው እንዲቀላችሁ፤
አሁንም ለአንድነት ትጠራላችሁ።
የኢትዮጵያ ሕዝብ:በሞት እሣት ሲታመስ፤
በየጎጡ ሲከልሉት:ባደባባይ ደሙ ሲፈስ፤
በመራር ድምፅ ሲተናነቅ:ለነፃነቱ ሲታገል፤
ከባንዳ-ወያኔ ሲፋለም፤በተንኮላቸው ሲገደል።
የመረጠም በሰላም:የርጉማን ልብ ለመስበር፤
ሕዝብ እንዳይሞት ሲለማመጥ በየዋሕነቱ ሲጠፈር።
አቅም ያጣው በሹልክታ ከባርነቱ ሊያመልጥ፤
“የተሻለ ነው”ብሎ: የስደት ሕይወቱን ሲመርጥ።
የሞት ሸለቆን ሲጋፈጥ:ቤት ንብረቱን እየደፋ፤
ከሚወዳት ኢትዮጵያ በባንዳ ተንኮል ሲገፋ።
እኮ ምንድነውሳ መልሳችሁ?
ትናንት የት ነበራችሁ???
ጉጅሌው-ወያኔ እንደሥጋ ትል፤
ከውስጣችን እየበላ ቆዳችንን ሲተለትል፤
አጥንታችንን ሲግጥ እያፈሰሰ ደማችንን፤
ሕፃናት በሚሊዮን ሲረግፉ፤እንዴት እንግለፅ ሞታችንን? ? ?
እኮ!ምን ቢባልነው የምታምኑት፤
“አያገባንምን” ትታችሁ በሕሊና’’ኳ የምታዝኑት።
ዛሬማ ብሶ ባርነቱ ሕዝቡ ይኖራል በጭለማ፤
በነፃነት አርማችን በሞት ሽረት ሰንደቅ-ዓላማ።
የባንዲራውንም ሴራ የሰንደቅ-ዓላማውን ሚሥጥር፤
በልቡ-ፅላት ፅፎታል ወጣቱ ያውቀዋል ከምር።
እናም! ! !ይቅርታው እንዲቀላችሁ፤
አሁንም በሕዝቡ ትጠራላችሁ፤
ዛሬም ብትንቁ ሕሊናን:-ለሕዝቡ ደንታ ከሌላችሁ፤
ነገ ግን መባሉ አይቀርም:-
በግላጭ “የት ነበራችሁ? ? ?”
ቤተ-ክርስቲያን ስትዘምሩ???
በየመስጊዱ ስትቆጥሩ???
በአሸባሪነቱ ስትሰጉ???
የጊዜን ጥግ ስትመሽጉ??
ሰውን ማመን ትታችሁ ተስፋቆርጣችሁ በትግሉ፤
በፀሎት በዱአ ታጥባችሁ ደም ያላያችሁ ስትመስሉ።
የነገን ገቢ በኢንቨስት ወተቷን ናፍቆ በማለም፤
ለቭዲዮ ለሲዲ ንግድ ሙዚቃ ብሎ ማሳተም።
አሊያም የግል ጥቅም ለማሳደድ፤ከባንዳ-አጋዚ መጣበቅ፤
በኮንዶምኒየም ለመዝረፍ የሌለ ወሬ ማሳበቅ።
በማሾክሾክ ምስክር ሆኖ በመቆጠር፤
በደሞዝ በሰራተኛነት ለባንዳነት በመቀጠር፤
ሕዝቡ ሲሞት:- ሲሞት ሀገር፤
እኮ ምን ታደርጉ ነበር? ?
ጀግና የሞት ሞቷን ስታንገበግበው ወያኔን፤
በባንዳዎች ተጠልሎ ሲጨፈጭፈው ወገኔን፤
አገር ላይ ላዩን አማን እንዲመስል፤
ሕዝቡን አዘናግታችሁ ስታበስሩት የሌለ ድል።
በናንተ ደርሶ ግን “እኛ የለንበትም” የምትሉት፤
ሕዝብ እያስፈጃችሁ በሕዝብ ሥም የምትምሉት።
እረ!ምን ትውልድ ነን እኛ፤እኛነታችንን ያጣን፤
ልጆቻችንን ሲ-ማግዱ ሕሊናችንን የማይቀጣን።
“ተረገምን” አንበል በፈጣሪያችን አናሳብብ፤
ያለፉትን ዓመታት ብቻ ለአንድ አፍታ ቆመን እናስብ።
በትዕቢት ተወጥሮ ውርደቱን በግፍ ሲያፋጥን፤
በባንዳ እና በሆዳሞች:- ኅይል አግኝቶ ሲደነድን።
ለድል ስንቃረብ ወያኔን ለመዘርጠጥ፤
የሕዝቡ አመፅ ተቀልብሶ:-በደም-እምባ ሲለወጥ።
እንደገና ደም ስንከፍል፤መስዋዕትነትታችን ሲከስሞ፤
የሚጮህ ጠፍቶ ተስፋችን በባዶ ትግል ሲጨልም፤
እኮ.ምንድነውሳ መልሳችሁ..
ትናንት..የት ነበራችሁ????….
የሕዝብ አመፁ ሲመጣ፦ የዘረፉትም አይወስዷችሁ፤
ለደም-ክፍያ ጥያቄ ምንድነው”ሣ” መልሳችሁ?
ጀግና ለሕዝብ ፍርድ ይመጣል አይቀርምና ነገ፤
ወጣቱ ከነቃ ሰንብቷል፤በኢትዮጵያዊነቱ ካደገ።
ማን ለምን እንደቆመ፤የአሰላለፉን ዓይነት፤
የጎጠኞችን ሥም ዝርዝር፤የባንዳዎችን ምንነት።
ጠንቅቆ ይዟል ለታሪክ ማን ኢትዮጵያን እንዳደማት፤
የድሃ ሀብት ነፃነቷን ማን በተንኮል እንደቀማት።
ማን እምዬ እያለ፤እየሞተላት ሲያነሳት፤
ማንስ ወግቶ ሊግድላት፤እኝ አድርጎ ጡቷን ነከሳት።
መድኅኔያለም ይጠብቃታል፤አላህ ፈጣሪ እንዳቀፋት፤
ልጆቿ ረገፉ እንጂ ኢትዮጵያንስ ማን ሊያጠፋት።
ዛሬ ትናንት ሳይባል:-የሕዝብ ዳኝነት ሳይመጣ፤
በማይቀረው አመፁ ባደባባይ-ሞት ሳንቀጣ፤
ምንድነው’ኮ መልሳችሁ፤ዛሬ ከማነው ውሏችሁ
የደም ጥያቄ ሲመጣ፦ የዘረፉትም አይወስዷችሁ::
ምንድነው”ሣ” መልሳችሁ???በደሙም ሳይጠይቋችሁ ፤
“አላውቅም”በማለታችሁ እንጦርጦስ ትወርዳላችሁ።
እናም!!!ይቅርታው እንዲቀላችሁ፤
አሁንም በሕዝቡ ትጠራላችሁ፤
ዛሬንም ብትንቁ ሕሊናን:-ለሕዝቡ ደንታ ከሌላችሁ፤
ነገ ግን መባሉ አይቀርም:-
በግላጭ “የት ነበራችሁ???”