በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኙ ሶሪያዊያንን ሲሰልል የተገኘ አሜሪካዊዉ የሶሪያ ዜጋ ክስ ተመሰረተበት

በስደተኛነት ገብቶ የአሜሪካ ዜግነት የተሰጠዉና አብረዉት በዩናይትድ ስቴትስ ነዋሪ የሆኑ የሶሪያ ዜጎች የአገራቸዉ መንግስት በወገኖቻቸዉ ላይ የሚያደርሰዉን የሰብአዊ መብት ረገጣ በመቃወም  የሚያደርጉትን ሰላማዊ ሰልፍ በተለያየ መልክ እየመዘገበና እየቀረፀ ለሶሪያ መንግስት በድብቅ መረጃ ሲያቀብል የተገኘ ሶሪያዊ ክስ የተመሰረተበት መሆኑን አሶስየትድ ፕሬስ ዘግቧል።

መሃመድ አናስ ሃታም ስኡድ የተባለዉ ቅጥረኛ የራሱን ወገኖች በመሰለል መረጃዉን ለሶሪያ መንግስት እንደሚሰጥና በየጊዜዉ ወዳገሩ እየተጓዘ ከፕሬዝዳንት አሳድና ከሌሎች ባለስልጣናት ጋር እንደሚገናኝ ታዉቋል።

በዩናይትድ ስቴትስ የሚገኘዉ የሶሪያ ኤምባሲ “መሰረትና ተቀባይነት የሌለዉ” በማለት  ክሱን አጣጥሎታል። እንደተባበሩት መንግሰታት ድርጅት ግምት ከ3 ሺህ ያላነሱ ሰላማዊ ዜጎችን የገደለዉ የአሳድ አምባገነን መንግስት ድምበር በመሻገር በዉጭ አገር የሚገኙ የዳያስፖራ አባላት አረመኔያዊ ተግባሩን እንዳይቃወሙ ሰላዮችን ማሰማራቱ የህዝብን የለዉጥ ጥያቄ በሃይል ለማፈን የሚያደርገዉን ጥረት ያሳያል ተብሏል።

ኦክቶበር 3 ቀን የወጣዉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናል ዘገባ የሶሪያ መንግስት ኤምባሲዎችና ሌሎች ቅጥረኞቹ በዉጭ አገር የሚገኙ ሶሪያዊያንን እንደሚያሳድዱ መግለፁ የሚታወስ ሲሆን ከዚሁ ጋር በተያያዘ የብሪታኒያ የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በአገሩ የሚገኙትን የሶሪያ አምባሳደር ጠርቶ በብሪታኒያ የሚገኙ ሶሪያዊያንን አንድ ዲፕሎማት ለማስፈራራት ጥረት ማድረጉን በመግለፅ አነጋግሯቸዋል።

የፌዴራል አቃቢያን ድርጊቱ የአሜሪካንን የህዝቦች የመሰብሰብ ህገ መንግስታዊ መብት የሚፃረርና ተቀባይነት የሌለዉ እንደሆነ ገልፀዋል። የዩናይትድ ስቴትስ የምስራቅ ቨርጂኒያ ጠቅላይ አቃቤ ህግ ማክ ብራይድ “መሰብሰብና በሰላማዊ ሰልፍ ተቃዉሞ ማቅረብ በአሜሪካ ምድር ላይ መብት በመሆኑ ይህንን መብት ሰዎች እንዳይጠቀሙ ለማድረግ ማንም ሰዉ ማስፈራራት አይችልም” ብለዋል።

የአሜሪካ የብሄራዊ ፀጥታ ቃል አቀባይ ቶሚ ቪተር በበኩላቸዉ “ይህ በዩናይትድ ስቴትስ ተቃዋሚ ሰላማዊ ሰልፈኞችን ለመቆጣጠር የአሳድ መንግስት የሚያደርገዉ ቁጥጥር የጭካኔ ተግባሩ እንደይጋለጥ ለማፈን ማንኛዉንም ነገር እንደሚፈፅም ያሳያል” በማለት ገልፀዉታል።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ሽብርተኛው መለስ ዜናዊ ባቋቋመው የዲያስፖራ ጽቤት አማካይነት በውጪ ያሰማራቸው ሰላዮች ተመሳሳይ እጣ እንደሚገጥማቸው አንዳንድ መረጃዎች ለኢትዮጵያ ሳታላይት ቴሌቪዥን መድረሱን ኢሳት ዘግቦአል። በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የወያኔን ነፍሰገዳይ አገዛዝ እድሜ ለማራዘም እርዳታ የሚሰጡትንና በስለላ ስራ ላይ የተሰማሩትን ባንዶች ዝርዝር በተጨባጭ ማስረጃ በማስደገፍ መረጃውን ለዝግጅት ክፍላችን በስልክ ወይም በኢሜል  በማስተላለፍ እንዲተባበሩ የግንቦት 7 ድምጽ ጥሪውን ያቀርባል።