በተቃወምከው ግዜ ቀንበሩን ከላይህ ላይ ትሰብራለህ!!
ላለፉት ሃያ ዓመታት በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ የተጫነብን ቀንበር መከራችንን አብዝቷል። መከራውም መሸከም ከምንችለው በላይ በመሆኑ ሮሮአችን ገደቡን ጥሶ ሦስት ትውልድን በአንድ ላይ እያስለቀሰ ነው። ህጻናት ልጆች ደጋግ አባቶቻቸው በካቴና ታስረው ወደ ወይኒ ሲጨመሩ እያዩ አምርረው እያለቀሱ ነው።የሚንከባከባቸው ውድ አባታቸው ለምን እንዲህ በአደባባይ ተይዞ እንደሚታሰር የሚነግራቸው ባለመገኝቱ ለጋ አእምሯቸው ለጭንቀት ተጋልጧል። የቤቱ ምሶሶ አባት በመታሰሩ ምክንያት እናቶች ልጆቻቸውን የሚመግቡትን ማቅረብ ባለመቻላቸው በጎስቋላ ቤታቸው ጣሪያ ሥር እያለቀሱ ነው። እንባቸው በፈርኦን እጅ ስቃዩዋ በዝቶ እንዳለቀሰችው ራሄል እንባ ጽዋውን ሞልቶ እየፈሰሰ ነው።
ዛሬ በአገራችን ሰውንም የማያፍር እግዚአብሄርንም የማይፈራ መለስ ዜናዊ የሚባል ሌላ ፈርኦን ተነስቷል። ይህ ሌባና ክፉ ዘረኛ ግለሰብ የዜጎችን በህይወት የመኖርና ያለመኖር እድል ፈንታ ወሳኝ ሁኗል።
የፈርኦን እጅ በድሆች ዜጎች ላይ በጠነከረ ግዜ የፈጣሪን ፊት እስከሚያይ ድረስ ክብርን ያገኘ አንድ ሰው ተነሳ።ሙሴ ይባላል። ሙሴን የመሰለ ነብይም ዳግም አይነሳም ተብሎ በመጽሃፍ ቅዱስ ተጽፎ እናነባለን።
ሙሴ የፈጣሪን ፊት እስከሚያይ ድረስ ያደረሰው ምንድ ነው ?
ሙሴ በፈርኦን ቤት ያደገ የንጉስ ልጅ ልጅ ተብሎ በድሎትና በምቾት ይኖር ነበር። ፈርኦን ደግሞ ሰውንም ያማያፍር እግዚአብሄርንም የማይፈራ ክፉ ሰው ነበር። በዚህ ክፉ ፍጡር ቤት ውስጥ በድሎትና በምቾት ከመኖር ይልቅ ወገኖቹ የተሸከሙትን የመከራ ቀንበርን መቃወም በመምረጡ የፈጣሪን ፊት እስከሚያይ ድረስ ደረሰ።
ዛሬ ብዙዎች በመለስ ዜናዊ ማእድ ዙሪያ ተሰባስበው ጮማ እየቆረጡ ባለ ቀለሞችን መጠጦች እየተጎነጩ በደስታና በድሎት ሠክረዋል። ሚሊዮኖች በችጋር ሲያልቁ የዘመኑ ፈርኦኖች ግን በድሆች ላይ እየተሳለቁ ነው።
ለራሳችሁ ክብር የምትሰጡ ኢትዮጵያዊያን በተቃወማችሁት ግዜ ቀንበሩን ከራሳችሁ ላይ ትሰብራላችሁና ሳታፈገፍጉ የዘመኑን ፈርኦናዊያን በእውነትና በጽናት ተቃወሟቸው።
የዘመኑ ፈርኦኖች 8.5 ቢሊዮን ሰርቀው በውጭ አገራት ባንኮች ሲያስቀምጡ ኢትዮጵያዊያን በራብና በበሽታ ይቀጣሉ። መለስና ግብረ-አበሮቹ ልጆቻቸውን በአውሮፓና በአሜሪካን ልከው እንደላቀው ሲያስተምሩና ሲያኖሩ ኢትዮጵያና ልጆቿ ግን ከቀያቸን ዘልቀን እንዳናልፍ ተደርገን ዘመኑ ከደረሰበት የእድገት ደረጃ ተለይተንና ርቀን እንድንኖር ተፈርዶብናል። ይህን የመሰለ ግፍ በገዛ አገራችን ላይ ሲፈጸም ዝም ለማለት ሰው መሆናችን ያስገድደናል።
ከዚህ ሁሉ ውረደትና እንግልት በኋላ የሚያስፈራን ምንድ ነው? ሞት ነው? አሁንስ ቢሆን ኢትዮጵያና ልጆቿ ከሞት መች አመለጥን? መለስ ዜናዊ በፈለገና ደስ ባለው ግዜ ዜጎችን ገድሎ ቤተሰቦቻቸውን ሜዳ ላይ ላለመበተኑ ምን ዋስትና አለን? መለስ ዜናዊ የጫነብን የመከራ ቀንበር ዛሬ ካልተቃወምነው ነገ ሸክሙ በልጅ ልጆቻችን ላይ የከፋ ትውልዱንም መለስ ዜናዊ ለሚፈጥረው ክፉ ዘረኛ ሥርዓት ትተን እንድናልፍ ይሆናል። ልጅ ልጆቻችንም በገዛ አገራቸው መጻተኛና ስደተኞች ሁነው ይኖራሉ።
መለስ ዜናዊ በሃሰት ዜጎችን እየከሰሰ የሞትና የእድሜ ልክ እስራት ሲፈርድ አይተን እንዳላየን ሰምተን እንዳልሰማን መሆን ፈጣሪን እፈራለሁ ከሚል ሰው የሚጠበቅ ተግባር አይደለም። ፍትህ ሲጓደል ህግ ለመለስ ዜናዊ ቂም መወጣጫ ሲሆን እያየን እስከ መቼ ዝም እንላለን? በመለስ ዜናዊ ዘረኛና ዘራፊ ስርዓት የብዙ ደጋግ ዜጎች ቤተሰቦች ሜዳ ላይ ተበትነው ጦማቸውን ሲያድሩ እያዩ ዝም ማለት ትክክለኛ ተግባር አይደለም። እንዲህ ዓይነቱን ግፍ ተሸክመን እንኖር ዘንድ አይገባም። መለስ ዜናዊን የመሰለ ዘረኛና የሌቦች አለቃ ክብራችንን ሲያዋርደውና የመኖር ህልውናችንን ሲፈታተነው እያየን ዝም ለማለት አኛ ሆዳችን የሚገዛን አይደለንም። ማንነታችንን ለዘመኑ ፈርኦኖች አሳልፈን ለመስጠት ሃሞታችን አይፈቅድም። ሰው ከመሆን ተራ ሊያወጣን የሚሰራውን ዘረኛውንና ዘራፊውን ሥርዓት በቻልነው መንገድ ሁሉ እንታገለዋለን። ለክብራችንም ስንል ከተገፉ ወገኖቻችን ጎን ቆመን አገራችንን ከሌቦች እናጸዳለን።
በመጨረሻም ክብርህን የምትወድ ኢትዮጵያዊ ሁሉ ማወቅ ያለብህ ማንም ሰው ሊረዳህ አይመጣም።ሳታፈገፍግና ሳታቅማማ የተጫነብህን ቀንበር ለመስበር መቃወም ያንተና ያንተ ድርሻ ብቻ ነው።ታላቁ ነብይ ሙሴ ፈርኦን በወገኖቹ ላይ የጫነውን ቀንበር በመቃወሙ ፈጣሪ አክብሮታል።አንተንም ፈጣሪ ያከብርህ ዘንድ የጨለማውን ጣኦት መለስ ዜናዊን በቃህ ማለት ከአንድ ፈጣሪን እፈራለሁ ከሚል ሰው የሚጠበቅ የተወደደ ተግባር ነውና ለጨለማው ጣኦት እምቢ በማለት ክብርህን ማስጠበቅ አለብህ።
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ ይሁን !!!