ጥሪ በመለስ ዜናዊ ጎራ ለሚገኙ ወገኖቻችን

የመለስ ዜናዊ አገዛዝ በከፍተኛ ሽብር ውስጥ ገብቷል። ይህ አገዛዝ የቆመበት መሠረት በጣም ስስና ደካማ በመሆኑ በዘወትር ስጋት ውስጥ ነው።

በአንድ ወይም በሌላ ምክንያት ለመለስ ዜናዊ የወገኑ ኢትዮጵያዊያን መኖራቸው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ የሌለው ጥንካሬ ያለው እንዲመስል አድርጓል። ይህ ደግሞ በተራው የኢትዮጵያንና የኢትዮጵያዊያንን  መከራ አብዝቷል።

በመለስ ዜናዊ እና ዘረኛ ቡድኑ ዙሪያ ያሉ ሰዎች ሁሉ የመለስን አገዛዝ ከልባቸው ይደግፋሉ ብሎ  ግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ አያምንም። አንዳንዱ በአንድ አጋጣሚ ገብቶ መውጫ ቀዳዳ አጥቶ የሚዳክር ነው። ሌላው ደግሞ ባለሙያ ነኝ፤ የሙያ አገልግሎት ብቻ እየሰጠኹ ነው እያለ እራሱን የሚታልል ነው። ቀሪው ደግሞ “ወይን-ለኑሮ” በተሰኘው ዘይቤ “ያባትህ ቤት ሲዘረፍ አብረህ ዝረፍ” እያለ ለጊዜዓዊ ጥቅም ሲል የተጠጋ  ነው።

ይሁን እንጂ ደጋግመን ልናስታውሰው የሚገባ ሃቅ አለ። በማንኛውም ምክንያት ከመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ጎን የቆመ ኢትዮጵያዊ አገሩን ኢትዮጵያንና ወገኖቹን እየጎዳ ነው።

ዛሬ ያሉ የኢህአዴግ ድርጅቶች በሙሉ የመለስ ዜናዊ የስለላ ተቋማት ናቸው። ለህወሃት ፍቅር ያላችሁ ወገኖች ስሙ! ያ የምትወዱት ህወሃት ዛሬ የለም። ዛሬ ያለው የመለስ ዜናዊና የአዜብ መስፍን የግል የስለላ ተቋም ብቻ ነው። የዛሬው ህወሃት ለትግራይ ልጆችም አይተኛም። ለብአዴን መልካም አመለካከት ያላችሁ ወገኖችም ስሙ! ብአዴን ዛሬ የለም። ዛሬ ያለው የመለስ ዜናዊና የአዜብ መስፍን የግል የስለላ ተቋም ብቻ ነው። ብአዴን ለአማራ ልጆችም አይተኛም። በሌሎችም የመለስ ዜናዊ አሻጉሊት ድርጅቶች ውስጥ ያላችው ኢትዮጵያዊያን ንቁ!!! ድርጅት የሚባል ነገር የላችሁም። ድርጅት የሚመስሉት ነገሮች የመለስ ዜናዊና የአዜብ መስፍን የግል የስለላ ተቋማት ብቻ ናቸው። በተቋማቱ መሣሪያነት፤ በእናንተ ተባባሪነት ወገን ሲበደል፤ አገር ስትፈራርስ ማየት እንደምን ያስችላችኋል?

“ቤተሰብ አለኝ፤ ልጆች አሉኝ” የሚሉ ሰበቦች የመለስ ዜናዊ ቡድንን ለመጠጋት ምክንያቶች ሊሆኑ ይችላሉ። ነገር ግን ልጆችም ቢሆኑ የሚመኩበት አባት እንዲኖራቸው ይፈልጋሉ።

በትንሹም ቢሆን ከመለስ ቡድን ጋር መነካካት ለመለስ ዜናዊና ዘረኛ ቡድኑ የልብ ልብ መስጠት ነው። በትንሹ እንኳን የጥቅም ተካፋይ የሆነ ሰው ትልቁን ዘረፋ የመቃወም የሞራል ብቃት  አይኖረውም። በዚህ የተበረታታው የመለስ ዜናዊ ቡድን እነሆ ዛሬ የእርሻ መሬቶችን ለባእዳን ቱጃሮች እስከ መሸጥ ደርሷል። ይህን እየታዘቡ ከመለስ ዜናዊ ጋር መተባበር እንደምን ይቻላል?

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ፍርሃት በፈጠረው የወያኔ ጨካኝነትና ድድብና ተጠቅተዋል። ሰላማዊ ዜጎች “ሽብርተኛ” እየተሰኙ ብልቶቻቸውን ሳይቀር ተቀጥጠዋል። የመለስ ዜናዊ ቡድን ፈሪነት “ጆሮ ጠቢነትንና” ወሬ አቀባይነትን ተሰምቶ ወደ ማይታወቅበት ደረጃ አሳድጎታል። ይህ ደግሞ  በሕብረተሰባችን ውስጥ የነበረውን እና ለዘላቂ አብሮነታችን እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ማኅበራዊ መተማመንን እያጠፋው ነው። ይህን እያዩ ከመለስ ዜናዊ ጋር እንዴት መተባበር ይቻላል?

ደግመን እንለዋለን። የመለስ ዜናዊ ቡድን ደካማና በዘወትር ስጋት ውስጥ ያለ ነው። የሌለውን አቅም የሰጡት በተለያዩ ምክንያቶች ከጎኑ የቆሙ ኢትዮጵያዊያን ናቸው።

የዛሬ ጥሪያችን ለእነሱ ነው!

ወገኖች!

የመለስ ቡድን በኢትዮጵያ ጥላቻ የተሞሉ፤ የግል ጥቅም ያወራቸው፤ ትዕቢተኖች፣ ማይማን፣ ጉረኞችና ዘረኖች ስብስብ ነው። እነሱ የተካኑት ራሳቸው ያጠመዱትን ፈንጂ በቪዲዮ እየተቀረጹ ማምከንን ነው። እነሱ የተካኑት ሽብር በመንዛት ህዝብን በፍርሃት ቆፈን አስሮ መግዛትና ሃብቱን መቦጥቦጥ ነው። ፍርሃትን ማንገስ የተለመደ የአምባገነኖች የመጨቆኛ መሣሪያ ነው። ፍርሃት ለተወሰነ ጊዜ ዜጎች ተዋርደው፣ ተረግጠውና ተቀጥቅጠው እንዲገዙ የማድረግ አቅም አለው። ሆኖም ግን ፍርሃት ያቆመው ሥርዓት ለመናድ ጊዜ አይፈጅበትም። ፍርሃት ያቆመው የበርሊን ግንብ በሰዓታት ፈርሷል። በፍርሃት የቆሙ የቤን ዓሊ፣ የሙባረክና የጋዳፊ መንግሥታት ፈራርሰዋል።  የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ውድቀትም ተመሳሳይ እንደሚሆን ጥርጥር የለንም።

እናም በመለስ ዜናዊ ጎራ ያላችሁ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን መስመራችሁን አስተካክሉ። ነገ ሊረፍድባችሁ ይችላል። በአገራችሁ፤ በወንድሞቻችሁና በእህቶቻችሁ ላይ ብዙ ውድመት ከደረሰና ብዙ ጥፋት ከተሰራ በኋላ “መስመራችንን አስተካክለናል” ከተጠያቂነት አታመልጡም።

አንዳንዶቻቸሁ ከዚህ በፊት ላቀረብናቸው ጥሪ አዎንታዊ መልስ ሰጥታችኋል። ይህ መልካም ነገር ነው። ከፊሎቻችሁ ግን ለመወሰን እንደተቸገራችሁ እንሰማለን። እናንተን የምንጠብቅበት ጊዜ የለንም።  የቆማችሁበትን መስመር በፍጥነት ፈትሻችሁ አስተካክሉ።

ከመለስ ዜናዊ አገዛዝ ራሳችሁን ለማግለል የወሰናችሁ ወገኖቻችን፣ የአገዛዙን እድሜ ለማሳጠር በሚደረገው ትግል ውስጥ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ አስተዋጽኦ በማድረግ እስከዛሬ – በማወቅም ሆነ ባለማወቅ  – የበደላችሁትን ህዝብ እንድትክሱ እንጠይቃለን።

ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!