ወያኔ ህዝብ ከፋፍሎ ለመግዛት ባለው ራዕይ የፈጠረው የሃይማኖት አክራሪነት ከፍተኛ የሆነ የደህንነት ስጋት ማስከተሉን ባለሥልጣናቱ ገለጹ
በአገራችን ውስጥ ለዘመናት የኖረውን የባህል፤ የቋንቋና የሃይማኖት ልዩነቶችን ለሥልጣን እድሜ ማራዘሚያ እንደ አይነተኛ መሳሪያ ሲጠቀምበት የኖረው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ፤ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ አንዱን እምነት ተከታይ በሌላው ላይ በጠላትነት ለማስነሳት ሲያደርገው የነበረው የውስጥ ለውስጥ ሥራ አደባባይ ላይ መታየት በመጀመሩ ”የአገሪቱን ደህንነት ሊያሰጋ ከሚችልበት ደረጃ ላይ ደርሶአል” በማለት ህዝብ ለማሸበር እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የግንቦት 7 ዘጋቢ ከአዲ አበባ በላከልን ሪፖርት ገለጸ።
ለዘመናት በሰላም ተከባብሮና ተቻችሎ የኖሩትን የሁለቱን ታላላቅ ሃይማኖቶች አባቶችን ለፖለቲካ ሥርዓቱ ታማኝ በሆኑ ግለሰቦች በመተካት፤ የአንዱ ዕመነት ተከታይ ሌላውን በጥርጣሬና በጥላቻ እንዲመለከት ላለፉት 20 አመታት ያልተቋረጠ መሰሪ ሥራ እንዲያከናውኑ ሲያደርጋቸው ከቆየ ቦኋላ ከቅርብ ጊዜ ጀምሮ አክራሪዎች ተነስተዋል፤ ሰላምና ጸጥታ ሊያደፈርሱ ነው ወዘተ በሚል ሰበብ መግለጫ እንዲሰጡ እያደረጋቸው መሆኑ ታውቆአል።
በዚሁ መሰረት ሰሞኑን የእምነት ዳይሬክተር ጄኔራል የተባለው መረሳ ረዳ ”የዋህቢዝም እምነት ተከታዮች በህቡእ በመንቀሳቀስ አመጽ እየቀሰቀሱና እረብሻ እንዲፈጠር እየሰሩ ነው” በማለት ለጋዜጠኞች መግለጫ መስጠቱ ታውቆአል። መግለጫውን ተከትሎም የፌደራል ጉዳዮች ሚኒሰትር የሆነው ሽፈራው ተክለማርያም ይህንኑ ወያኔ ራሱ የፈጠረውን የውሸት ስጋት በመድገም ”የዋህቢ እምነት ተከታዮች ራሳቸውን በህእቡ በማደራጀት ከፍተኛ የሆነ የጸጥታ ስጋት ደቅነዋል” በማለት አስተጋብቶአል።
በወያነ የፌደራል ፖሊስ ዋና ጽህፈት ቤት ውስጥ ሰሞኑን በተካሄደው የግንዛቤ ማሽጨበጫ ጉባኤ ተብዬ ስብሰባ ላይ የወያኔ ባለሥልጣናትና የመንፈስ አባቶች ተብዬዎች ከዚህ ቀደም በተከታታይ በሀረር፣ በጂማ፣ በወለጋ፣ በኢሉባቦርና በባሌ የታዩት ግጭቶች በሙሉ የዋህቢ እምነት አክራሪዎች የፈጠሩት ነው ማለታቸው ተያይዞ የደረሰን ዜና ያስረዳል። ከዚህም አልፈው ዋህቢዎች ኢትዮጵያን በሼሪያ ህግ የምትተዳደር የሙስሊም አገር ለማድረግ እየሰሩ ናቸው ማለታቸው ለዘመናት ተከባብሮና ተቻችሎ በሰላም የሚኖረው ክርስቲያኑንና ሙስሊሙ ህብረተሰብ በጥርጣሬ እንዲተያይና በኑሮ ውድነትና በአስተዳደር በደል ምክንያት በወያኔ ላይ አንድ እየሆነ የመጣውን የተቃውሞ ድምጽ ለመከፋፈል አልመው መነሳታቸውን ለሁለቱም እምነቶች ቅርበት ያላቸው ሰዎች ይናገራሉ።
የግንቦት 7 ዘጋቢ ያነጋገራቸው የሁለቱም ሃይማኖት ተከታዮች ወያኔ አንድ ጊዜ የሙስሊሙ ሌላ ጊዜ ደግሞ የክርስቲያኑ ደጋፊ አድርጎ ራሱን በማቅረብ፣ ለዘመናት ታችቸሎ የኖረውን ህዝብ በማበጣበጥ የስልጣን እድሜውን ለማራዘም እየሞከረ ነው ማለታቸውን ዘግቦአል። በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ወያኔ አህባሽ የሚባለው የእስልምና እምነት እንዲስፋፋ በፖሊሲ ደረጃ ነድፎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑ በርካታ ሙስሊሞችን እያስቆጣ ነው ተብሎአል፡፡
በኢትዮጵያውያን ሙስሊሞች ጉዳዮች ሁሪያ ጸሀፊና ተመራማሪ የሆኑት አቶ አቡበክር አለሙ ሰሞኑን በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ “የዚህ ሰሞኑ የኢህአዴግ ሀይማኖተኛነት እንቆቅልሽ” በሚል ርእስ ባወጡት ጽሁፍ የአዲስ አበባ የፍትህ ቢሮ ሀላፊ አቶ ጸጋየ ሀይለማርያም ለሙስሊሞች በተዘጋጀ ስብሰባ ላይ “ቅንጅትና ኢህአዴግ አንድ ላይ ሊደራጁ እንደማይችሉት ሁሉ ውሀብያና ሱኒም አንድ ላይ ሊሆኑ አይችሉም” በማለት የተናገሩትን ነቅፈዋል።
አደስ ዘመን ጋዜጣም መስከረም 19 2004 ዓ.ም. በእኩልነት ከማያምኑ ጸረ ሰላም ሀይሎች ሙስሊሙ ህብረተሰብ ትክክለኛውንና ከአያት ቅድመ አያቶቹ የተረከበውን የእስልምና እምነት እንዲጠብቅ፣ እምነቱን ለመከለስ ከሚንቀሳቀሱ አክራሪዎችና ጽንፈኞች እራሱን እንዲያገልና የጸረ ሰላም ሀይሎች ድብቅ አላማ ማስፈጸሚያ እንዳይሆን ማስጠንቁን ጸሀፊው ገልጸዋል።
አቶ አቡበክር በጽሁፋቸው “ለመሆኑ ህብረተሰቡ ከአያት ቅድመ አያቶቹ የተረከበውን ነገረ ሀይማኖት የትኛው እንደሆነና በጸረ ሰላም ሀይሎች የተበረዘውን እና የተከለሰውን የሀይማኖት ቀኖና ደግሞ የትኛው እንደሆነ እንዲያውቅና እንዲገነዘብ የማድረግ ሀላፊነት ያለበት ማነው? መንግስት ወይስ የሀይማኖቱ ሊቃውንት?” ሲሉ ጠይቀዋል።
ከወራት በፊት በወሎ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ 6 የዩኒቨርስቲ ሴት ተማሪዎች አክራሪ የሆነውን እስልምና ትከተላለችሁ በሚል በፌደራል ፖሊሶች ተይዘው ማእከላዊ እስር ቤት ውስጥ መታሰራቸውን የግንቦት 7 ድምጽ ዘግቦ እንደነበር ይታወሳል።