ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የተከሰተውን የርሃብ አደጋ ስፋትና ጥልቀት ለመሸፋፈን ቢሞክርም ችግሩ ከቁጥጥር ያለፈ በመሆኑ ገሃድ እየወጣ መሆኑ ተገለጸ
በምስራቅ አፍሪቃ በተለይም በኢትዮጵያ የተከሰተውን የርሃብ አደጋና እልቂት ጨካኙና ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ የማለባበስና የመደበቅ ሙከራ ቢያደርግም የርሃብ አደጋው ስፋትና ጥልቀት ከዘረኛው አገዛዝ የመደበቅ ሙከራ የላቀ በመሆኑ ችግሩ ለአለም ህዝብ ይፋ እየሆነ መምጣቱ ታወቀ።
በደቡብ ኢትዮጵያ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ የተከሰተው ረሃብ ለበርካታ ዜጎች እልቂት ምክንያት መሆኑ የሚታወቅ ሲሆን ይሄው ርሃብ በተከሰተበት አካባቢ ባሉት አዋሳኝ ክልሎችም የተከሰተው ድርቅ በተጨማሪ የዝናብ እጥረት መባባሱ ታውቁአል። ለተለያዩ ተግባራት ወደ ደቡብ የኢትዮጵያ ክልል የተጉአዙ የአይን እማኞች ለተለያዩ ዜና አውታሮች እንደገለጹት በደቡብ ክልል በየሜዳውና አስፋልት ዳርቻ የተለያዩ የቤት እንስሣት አልቀው እንደሚታዩና በርካታ ከብቶቻቸው የሚሞቱባቸው አርብቶ አደሮች ሳር ፍለጋ ከሞት የተረፉትን ለማዳን እየገሰገሰገሱ፤ እንደሚገኙ ታውቁአል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘ የቪ ኦ ኤ ዘጋቢ እንደገለጸው ከአዲስ አበባ ወደ ደቡብ የኢትዮጵያ ክፍል 705ኛው ኪሎሜትር በቦረና ዞን የሚታየውን ድርቅና ከፍተኛ የሆነ የእንስሳት ሞት በግልጽ ያሳያል ያለ ሲሆን ከ1.5 ኪሎሜትር እስከ 2 የሚሆን ርቀት ውስጥ 16 የሞቱ የከብት ቅሪቶችን ቆጥረናል፣ ይሄ በመንገዱ ዳር ያየነው ብቻ ነው። ውስጣ ውስጡን ያለቀውን፣ ወድቆ የሚታየውን የእንስሳት ቅሪት አድማስ ይቁጠረው በማለት ገልጾታል።
እንደ ቪ ኦ ኤ ዘጋቢ ሪፖርት የሚበዛው ነዋሪ ከከብት እርባታ በሚገኙ ተዋጽዖዎች የሚተዳደርበት ቦረና ከ60-75 ከመቶ የሚሆኑ ከብቶች መሞታቸው እንደሚገመት ገልጾ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት እንደሚለው ከሆነ የሚያዝያው ወር የገና ዝናብ ለሁለተኛ ጊዜ ሳይጥል በመቅረቱ ከሩብ ሚሊዮን በላይ ከብቶች ሞተዋል ማለቱ ታውቁአል።
እውነታው ይህ መሆኑ እየታወቀ ዘረኛውና አረመኔው የወያኔ አገዛዝ በኢትዮጵያ የተከሰተውን ረሃብና እልቂት ዘጋቢዎች በትክክል እንዳይዘግቡ የሚችለውን ሁሉ በማድረግ ላይ የሚገኝ ሲሆን የእራሱ የሚገዛትን አገር ችግር በመደበቅ ረሃቡ ሌሎች ከሰሃራ በታች ያሉትን አገሮች ክፉኛ እንዳጠቃ ነገር ግን ኢትዮጵያ ለረሀብ የሚያጋልጡ ችግሮችን ለመቅረፍ ችላለች በማለት ባዶ ፕሮፖጋንዳ እየነዛ እንደሆነ ታውቁአል።
ይህ በእንዲህ እያለ ካራቱሪ በመባል የሚታወቀው ኩባንያ ከዘራፊው የወያኔ አገዛዝ የተቸረለትን ለም መሬት ከህንድ አገር ለሚመጡ ገበሬዎች የማከራየት እቅድ እንዳለው አዲስ ነገር ኦን ላይን በመባል የሚታወቀው የዜና አውታር፣ አጋልጦአል። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዊያንን ከቀያቸው በጦር መሳሪያ በማስገደድ እያፈናቀለ ለውጪ ሃገራት ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ለም መሬት እየቸበቸበ ያለው አጥፊው የወያኔ አገዛዝ አሁንም ለዚሁ የካራቱሪ ኩባንያ የአዲስ አበባ ከተማን ግማሽ የሚያክል 25 ሺህ ሄክታር ተጨማሪ ለም መሬት ከጋምቤላ ክልል የሸጠ መሆኑ ታውቁአል። የካራቱሪ ኩባንያ በጋምቤላ ክልል ብቻ ከ 300 ሺህ ሄክታር ለም መሬት ከዘረኛው አገዛዝ በርካሽ ዋጋ መግዛቱ ይታወሳል።
ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊያንን ለማጥፋት ቆርጦ በተነሳው ዘረኛ አገዛዝ በሚሊየኖች የሚቆጠሩ ዜጎች በግፍ ከቀያቸው እየተፈናቀሉ፣ ለርሃብና ሞት እየተዳረጉ በሚገኙበት ሁኔታ የሃገሪቱን ለም መሬትና አንጡራ ሃብት ለውጪ ሃገራት ባለሃብቶች በዘፈቀደ መቸብቸቡን ለማስቆም እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ እንዲነሳ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ጥሪ ማቅረቡ አይዘነጋም።