ኮ/ል መንግስቱ እና አቶ መለስ… ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለየቅል

በዚህ በቀይ ባህር ወደብ እና ጠረፍ ላይ ሆነን ካሌብን፣ ጥንታዊ የባህር ኃይላችንና የንግድ መርከቦቻችን በቀይ ባህር የነበረን ገናናነት አዱሊስንና መጠራን፣ ዳህላክን እና ናኩራን በአጠቃላይ የታሪክ ኩራታችንን አሉላን ጭምር እንመለከታለን። ቀይ ባህር እና [የባህር] በሮቻችን የታሪካችን ልዩ አሻራዎች ናቸው። – ኮ/ል መንግስቱ ኃ/ማርያም አዲስ ዘመን ጥር 22 ቀን 1969 ዓ.ም.*
* * * * * * *
የኢትዮጵያውያን የቀይ ባህር የባለቤትነት ስሜት ወይም አሰብን ለማስመለስ የነበራቸው ሞራል ገድለን ቀብረነዋል። አንዲት ሀገር ወደብ ከሌላት አትበለጽግም የሚለውን አስተሳሰባቸውን መግደላችን ከደርግ መደምሰስ ቀጥሎ የተቀዳጀነው ሁለተኛ ድል ነው። – መለስ ዜናዊ ባለፈው መስከረም በአዲስ አበበ የኤርትራውያን ጉባኤ አያይዞ በትግርኛ ካደረገው ቃለ-መጠይቅ በግርድፉ ተደምጦ የተተረጎመ።

ኢትዮጵያ በማን እጅ ነች?

ከላይ ያሉት ጥቅሶች በግልጽ የሚያሳዩት ነገር ቢኖር አንድ ትልቅ ቁም ነገርን ነው። እሱም በአገር-በቀል አምባገነናዊ መንግስት (Dictatorship) እና በቅጥረኛ መንግስት (Mercenary) መካከል ያለው እጅግ ግዙፍ ልዩነትን ነው። ኢትዮጵያ በቅጥረኛ መንግስት የምተገዛ ብቸኛ ሀገር ናት። ይህ ሀቅ እንዳይታወቅ መለስ ከሚጠቀምባቸው በርካታ ስልቶች አንደኛው መመሪያችን “አብዮታዊ ዲሞክራሲ” ነው የሚለውን ጨዋታ ሲሆን፣ በሌላ በኩል ደግሞ “የወያኔ ሓርነት ትግራይ” መሪ ነኝ ማለቱ ነው። ‘አብዮታዊ ድሞክራሲ’ እነ አቶ ስዬን ለመምታት ከወረወረው የ‘ቦናፓርቲዝም’ ብትር እምብዛም የተለየ አይደለም። ሀሳባቸውን በነጻ፣ ያለፍርሃት እና መሸማቀቅ የሚገልጹበት የትግራዮች ድርጅት ያለ ይመስል፣ የወያኔ/ትግራይ መሪ ነኝ ብሎ መለስ የሙጥኝ ብሎ የያዛት አባባል ግን ትኩረት ያስፈልጋታል። በትግራይ ተወላጅነታቸው የሚታወቁ የወያኔ መሪዎች እንኳን ዛሬ፣ ድሮ ጫካ እያሉም ቢሆን በፍጹም የአስተሳሰብ ነፃነት ኑሯቸው አያውቅም።

የነሱ ነፃነት መለስ እና ስብሃት የሚያነበንቡትን ኤርትራ ከኢትዮጵያ “ቅኝ” አገዛዝ ነፃ መሆን አለባት! ኢትዮጵያ የራስዋ ወደብ ኖሯት አያውቅም! ኢትዮጵያ የብሄር ብሄረሰቦች እስርቤት ነች! ወ.ዘ.ተ. የመሳሰሉ የጠላት መፈክሮችን እንደ ገደል ማሚቶ ማስተጋባት ነው። እንደነ ሀየሎም አርአያ እና ይርጋ አበበ የመሳሰሉ ስመጥር ኮማንደሮቻቸው በዚሁ በኤርትራ ሰበብ እነ መለስ ቢገድልዋቸውም አንድ ስልጣን አለኝ የሚል የወያኔ አመራር ትንፍሽ ሲል አልተደመጠም።

ሌላ ቀርቶ 70 ሺ የኢትዮጵያ ወጣት የተሰዋለት ጦርነት በድል አፋፍ ላይ እያለ ጠላት ደርሶ ‘ጦርነቱ በ24 ሰዓት ይቆማል” ብሎ ሲያከሽፈው አንድም የወያኔ ባለስልጣን ከኮሪዶር ያለፈ ማጉረምረም አላደረገም። ከመለስ ዜናዊ ሌላ በስልጣኑ የሚተማመን ባለስልጣን ቢኖር ኑሮ ለኢትዮጵያ ህዝብ “ድልህ በጠላት እየተቀማ ነው፣ ድልህን ላለማስነጠቅ ከኛ ጎን መሆንክን በድጋፍ ሰልፍ ግለጽልን!” የሚል መልእክት ቢያስተላልፉ ኖሮ ህዝቡ በነቂስ እንደሚወጣ አያጠራጥርም ነበር። የመለስ እጣ ፈንታም ወይ እስር ቤት ወይም ስደት ይሆን ነበር። ይህ ሳይሆን ቀርቶ ግን ኢትዮጵያን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ወደብ-አልባ እንድትሆን መለስ ዜናዊ ያቀረበው ባለ 12 ቁጥር ምስማርም በአልጀርስ ስምምነት ስም ተረቆ ለመፈረም እና ለመጽደቅ በቅቷል።

ኢትዮጵያውያን በጠላት እንደሚገዙ እንዳይታወቅ፣ ሀቁ እንደ እሳተ ጎመራ ፈንድቶ እንዳይወጣ የመለስ ካድሬዎች እና ሻብያም በበኩሉ ከፈተኛ ሚና ይጫወታሉ። ኢትዮጵያን ለማታለል ከሚጠቀሙበት (ለወደፊትም ቢሆን የማያቆሙት) አንዱ ስልት ቢኖር በኢትዮጵያ ስልጣን የተቆጣጠሩት “ትግራዮች ናቸው” የሚለውን ነው። ግን ትግራዮች ከተመቱ አመታት ተቆጥረዋል። ሀቁ ይህ ነው። በስልጣን ላይ ያሉት ‘ትግራዮች’ ደግሞ ሁሉም ባይባሉም አብዛኞቹ ትግርኛ ተናጋሪ አባዱላዎች ናቸው እንጂ እውነተኛ የመንግስት ስልጣን ያላቸው አይደሉም (They have no real government power)። “ከ60 በላይ የሚሆኑ ጀኔራሎች የትግራይ ተወላጆች ናቸው” እየተባለ ብዙ ጊዜ ተጽፏል። ይህ ደግሞ መለስ እና ሻቢያ እንዲነገር የሚፈልጉት ጉዳይ ነው። ሀቁ ግን ትግራይን በኢትዮጵያ ጉዳይ ከጨዋታ ውጭ ያደረጉት ገና ከጅምሩ ከደደቢት ነው። ያ ህዝብ በጥይትም፣ በረሀብም አዳክመውታል። እማኝነት ካስፈለገ ደግሞ አቶ አስገደ ገ/ስላሴ እና አቶ ገ/መድህን አርአያ የጻፉትን አንብቦ መረዳት ይበቃል።

ዛሬ የቅጥረኛው መንግስት ከፍተኛ ባለስልጣናት ለመሆን የበቁት በልዩ ልዩ መንገዶች ለመለስ ዜናዊ ያላቸውን ፍጹም ታዛዥነት ያስመሰከሩ ሎሌዎች በመሆናቸው እንጂ በትግራይነታቸው አይደለም። 60 ትግርኛ ተናጋሪ ጀኔራል ቢጨፈለቅ አንድ በረከት ስምኦን አይወጣውም። ሀቁ እሱ ነው። ዛሬ እነ መለስ ለውጥ ፈላጊ ኢትዮጵያውያንን ለመግደል እስር ቤትን ወይም ጥይትን ብቻ አይደለም እየተጠቀሙ ያሉት። ረሀብም ጭምር እንጂ! (Mass starvation). በረሀብ የታረዘ ህዝብ ለአመጽ የሚያበቃ ጉልበት እንደሌለው አውቀው ለረዥም ጊዜ ሲጠቀሙበት ቆይተዋል።

አገር-በቀል አምባገነናዊ መንግስት ስልጣኑን ለማስጠበቅ ሲል የፖለቲካ ተቀናቃኞቹን ያስራል፣ ገፋ ቢል ይገድላል። ጠላት ግን አገርን ነው የሚገደለው። መንግስቱ ቀይ-ባህር የኢትዮጵያ የተፈጥሮ ድንበር ነው ሲሉ፣ ጠላት ግን የኢትዮጵያውያን አሰብን የማስመለስ ‘ቅስም ሰብረናል’ ይላል። ዱባና ቅል አበቃቀሉ ለይቅል እንዲሉ!
ስለዚህ ለድል የሚያበቃ የትግል ስልት ለመንደፍ መጀመርያ ኢትዮጵያ በቅጥረኛ ኃይል መውደቋን ማመን ያስፈልጋል። መለስ ዜናዊ በህዝብ ኃይል ከስልጣን ሲወገድና ኢትዮጵያ የራስዋ የሆነ ኢትዮጵያዊ መንግስት ሲኖራት፤ ቀዳሚው አጀንዳ መለስ ኢትዮጵያን ውክሎ የፈረማቸውን ውሎች ማስቀልበስ ይሆናል። ከነዚህ ቀዳሚ አጀንዳዎች አንዱ ደግሞ ቀይባህርን ወደ ጥንታዊት ባለቤትዋ ወደ ኢትዮጵያ ማስመለስ ይሆናል። ድርድሩን የሚመለከተው የተባበሩት መንግስታት ሲሆን፣ ጥያቄው ተቀባይነት እንዲያገኝ በኢትዮጵያውያን በኩል አገራችው በጠላት መያዝዋን፣ እና ጠላት ኢትዮጵያን ወክሎ የፈረማቸው ውሎች የኢትዮጵያን የህዝብ ፍላጎት ያካተቱ ስላልሆኑ እና ሆን ተብሎ ኢትዮጵያን ለመጉዳት የተደረጉ ስምምነቶች ስለሆኑ (ለምሳሌ አልጀርስ ስምምነትን) አለም አቀፉ ህብረተሰብ ግንዛቤ እንዲያገኝ በተደጋጋሚ ጥረት ማድረግ ነው።

በሌላ በኩል ደግሞ ህወሓት/ኢህአዴግ/ወያኔ …ወዘተ የሚሉ ማደናገርያ ቃላቶችን ቀብረን በምትካቸው “የቅጥረኛ ወይም የባንዳ አገዛዝ በኢትዮጵያ” የሚለውን ፅንሰ-ሀሳብ በስፋት ማሰረጽ ሲቻል ብቻ ነው ለውጥ የሚቀላጠፈው። አለበለዚያ የመለስ ዜናዊ ጉዳይ እንቆቅልሽ እንደሆነ ይቀጥላል። እንቆቅልሹን ለመፍታት ገሚሱ ሚስጥሩ አብዮታዊ ደሞክራሲ ጋር ያለ እየመሰለው፣ አንብቦ ቁልፏን ለማግኘት መከራውን ያያል። ሌላው ደግሞ “የእርቅ መንግስት” ነው መፍትሄው ብሎ መለስ ዜናዊ እግር ስር ይወድቃል። የጨነቀው እርጉዝ ያገባል እንዲሉ ጥቂት ወገኖች ደግሞ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ሻብያን ይማጸናሉ! (Not knowing that Eritrea is the shock observer of Meles Zenawi, and vice versa). 20 አመት ሙሉ በዚህ አዙሪት ውስጥ ሲያሽከረክሩን ምን ያህል ይታዘቡን!!!

*ጥቅሱ “አሰብ የማን ናት?” ከሚለው የዶ/ር ያ ዕቆብ ኃ/ማርያም መፅሐፍ የተገኘ ነው።
(በዚህ ዙርያ ገና ብዙ ያልተባለለት ጉዳይ አለ። የቅጥረኛው መንግስት ካድሬዎች ደግሞ በሀሳቡ ዙርያ የሚነሳውን እሳት ተሎ እንዲያጠፉ ይታዘዛሉ። ስለሆነም ምህረት ከሌለው የጠላት ግምገማ ለማምለጥ ብለው የባጡን የቆጡን ቢቀባጥሩ አትፍረዱባቸው)።

ኢትዮሚድያ (Ethiomedia) – October 12, 2011