አገራዊ እርቅ የሚጀምረዉ ብርቱካንን በመፍታት ነዉ

ከግርማ ካሳ

ግንቦት 7 ከተደረገዉ የዘጠና ሰባቱ ምርጫ ጀምሮ፣ ግንቦት 15 ቀን 2002 ዓ.ም እስከሰተደረገዉ ምርጫ ድረስ የነበሩትን ወራቶች ብንቆጥር ወደ 60 ይጠጋሉ ። ከነዚህ ወራቶች ዉስጥ ሰላሳ ስምንቱን ወራት፣ በሁላችንም ልብና አይምሮ ዉስጥ ያለችዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በቃሊቲ እሥር ቤት ነዉ የነበረችዉ። የ2002 ምርጫም ከተጠናቀቀ ከሁለት ወራት በኋላም አሁንም እህታችን በዚያዉ እሥር ቤት ትገኛለች።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ በተለይም ለስድስት ወራት ጨለማ ቤት ዉስጥ እንድትቀመጥ በመደረጉ፣ ከፍተኛ የጤንነት መታወክ እንደደረሰባት በሰፊዉ የተዘገበ ሲሆን፣ እናቷ ወ/ሮ አልማዝ ገብረ እግዚአብሄር፣ በየሳምንቱ ከፈረንሳይ ለጋሲዮን ቃሊቲ ድረስ እየተጓዙ፣ ከእሥር ቤቱ ዋና መግቢያ በር፣ ብርቱካን እስከታሰረችበት ቦታ ድረስ፣ በአንድ እጃቸዉ ስንቅ በሌላ እጃቸዉ የብርቱካንን ህጻን ልጅ ሃሌን ይዘዉ፣ በአሮጊት ጉልበታቸዉ፣ ከአሥራ አምስት ደቂቃ በላይ በመጓዝ ስቃይ እየደረሰባቸዉ ይገኛል።

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በግፍ መሰቃየት በርሷና በቤተሰቧ ላይ ካደረሰዉ ሰቆቃ በተጨማሪ ኢሕአዴግም ላይ ትልቅ ጉዳት እያደረሰ፣ የአገራችንን ስም በአለም አቀፍ ደረጃ እያጠፋ ነዉ። ሰብዓዊነትን እንደምናካበር፣ እንደሰለጠንንና የሃያ አንደኛዉ ክፍለ ዘመን ሰዎች እንደሆንን ሳይሆን በአሥራ ዘጠነኛዉ ክፍለ ዘመን ይኖሩ እንደነበሩ ሰዎች እየታየን ነዉ።

በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳና በቤተሰቧ ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ በብዙዎቻችን ልብ ዉስጥ እንደ እሣት ሆኖ እያቃጠለን ያለ ትልቅ ጉዳይ ነዉ። ብዙዎቻችን በየጓዳችንና በያለንበት «እህ» ያስብለናል። በኢሕአዴግ ላይ ጥሩ አመለካከት ከነበረን አመለካከታችን ወደ መጥፎ፣ መጥፎ አመለካከት ከነበረን ደግሞ ወደ በጣም መጥፎ እየተቀየረ ነዉ። በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ እየደረሰ ያለዉ ግፍ ኢሰብዓዊና ትልቅ የጭካኔ ድርጊት እንደሆነ ብዙዎቻችን ስለምናምን ኢሕአዴግን እንደ አንድ ኢትዮጵያዊ የፖለቲካ ድርጅት ሳይሆን እንደ «አዉሬ» እየቆጠርነዉ ነዉ። ከኢሕአዴግ ጋር የበለጠ እየተካረርን። ይህ ደግሞ ዉሎ እያደረ ሁላችንንም ወደ ማንፈልገዉ ደረጃ ያደርሰናል።

ኢሕአዴግ ደጋፊዎችን ለማግኘት ብዙ ገንዘብ እያወጣ እንደሆነ በሰፊዉ ይዘገባል። ዜጎችን በጥቅም ሆነ በጉልበት የድርጅቱ አባላት እያደረገ፣ ለአባላቱም የስራ እድል እየከፈተ ፣ ኮንዶሚኒየሞችን አሰርቶ በመስጠት፣ የሕዝብን ልብ ለማግኘት እየሞከረ ነዉ። ይህም የሚያሳያዉ ኢሕአዴግ ምን ያህል በሕዝብ ዘንድ ያለዉ ተቀባይነት እንዲጨምር ትልቅ ፍላጎት እንዳለዉ ነዉ።

ሆኖም ግን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን አሥሮ፣ ኢሕአዴግ የሕዝብን ድጋፍ ለማግኘት የሚያደርጋቸዉ ማናቸዉም አይነት እንቅስቃሴዎች በቀዳዳ ኪስ ሳንቲም እንደመክተት መሆኑን ማንም የሚያጣዉ አይመስለኝም። በርግጥ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ክፉኛ የኢሕአዴግን ተቀባይነት በሕዝቡ ዘንድ የሸረሸረና የጎዳ ጉዳይ ሆኗል።

በኢትዮጵያ ህዝብ ዘንድ ብቻ አይደለም። ትላንት የኢሕአዴጉን መሪ እንደ ትልቅ ዴሞክራሲያዊ መሪ ያዩ የነበሩት የአለም አቀፉ ማህበረሰብ አባላትም፣ አሁን እንደ ሌሎች አምባገነን የአፍሪካ መሪዎች አንዱ አድርገዉ እያይዋቸዉ ነዉ። ኢሕአዴግ «ኢትዮጵያ በዴሞክራሲያዊ ሂደት ትልቅ እርምጃ እንድትራመድ አድርጊያለሁ» ቢልም ኢሕአዴግ የአለም አቀፉ ማህበረሰብ ግን በደርግ ጊዜ ወደ ነበረዉ ሁኔታ ኢትዮጵያ እየተመለሰች እንደሆነ በመናገር ላይ ይገኛል።

ይህም በ2002ቱ ምርጫ ተቃዋሚዎች 0.04% መቀመጫ ብቻ በማግኘታቸዉና ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አግባብ በሌለዉ እሥራት ላይ በመሆኗ ነዉ።

አንዳንድ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከአንዳንድ የኢሕአዴግ አመራር አባላት በስተቀር፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን መታሰር ተገቢና አግባብ ያለዉ ነዉ የሚሉ በአገር ዉስጥ ሆነ በዉጭ አገር ብዙ አይገኙም። በርካታ የኢሕአዴግ ደጋፊዎች ሁሉ ሳይቀሩ፣ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን መታሰር አግባብ የሌለዉ ትልቅ ስህተት አድርገዉ ነዉ የሚወስዱት።

በመሆኑም ሕግን በመናቅና ለሰብዓዊነት ደንታ ቢስ በመሆን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንድትታሰር ያደረጉ ጥቂት የኢሕአዴግ አመራር አባላት ልብ እንዲገዙ እመክራለሁ።

በደቡብ ሶማሊያ አልሻባብ የሚባለዉ ሽብርተኛ ቡድን፣ አሁን ከሶማሊያ አልፎ በጎሮቤት አገሮች የሽብር ሥራዉን መፈጸም ጀምሯል። እግዚአብሄር የሰጠንን የአባይ ዉሃ እንዳንጠቀም ታሪካዊ ጠላታችን ግብጽ ዘመቻ ጀምራብናለች። ምናልባትም ጦርነት ልትከፍትብን ትችላለች።

ጊዜዉ ኢትዮጵያዉያን እርስ በርስ የምንጠቃቃበት ሳይሆን፣ በፍቅር በአንድነት የልጅ ልጆቻችን የሚኮሩባት፣ የእያንዳንዱ ዜጎች መብት የሚከበርባት፣ እስር ቤቶቿ ዜሮ የፖለቲካና የሕሊና እሥረኞች ያሉባት፣ አንዲት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ለመገንባት የምንነሳበት ዘመን ነዉ። ጊዜዉ በጋራ በመያያዝ ዋነኛ የአገራችን ጠላቶች የሆኑትን ረሃብ፣ በሽታ፣ መሃይምነትና ድህነት ላይ የምንዘምትበት ጊዜ ነዉ።

በመሆኑም ይህ እዉን እንዲሆን፣ አሁን በስልጣን ላይ ያለዉ የኢሕአዴግ መንግስት ትልቅ ሚና ሊጫወት ይችላል ብዬ አምናለሁ።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በእሥር ላይ በቆየች መጠን ኢትዮጵያዉያን ወደ እርቅ፣ ወደ ሰላም ወደ ብሄራዊ መግባባት የመምጣት እድላችን በጣም የጠበበ ነዉ የሚሆነዉ። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳንና በብዙ ሺሆች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እሥረኞችን አሁን በመፍታት፣ ኢሕአዴግ ለእርቅና ለሰላም ፍቃደኛነቱን እንዲያሳይ እንጠይቃለን።

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እንዲሁም በርካታ የሕሊና እሥረኞች የአገራችንን እሥር ቤቶች ባጣበቡት፣ የዜጎች ክብርና ማንነት በተደፈረበት ሁኔታ ምንም አይነት ልማትም ሆነ ዘለቄታ ያለዉ መሻሻል ሊኖር አይችልም። የአንድ ጋር ዜግች ፣ ወንድማማቾች ሆነ ሳለ፣ እንደጠላት እየተያየን፣ ለመጠፋፈት እየተፈላለግን፣ የዜሮ ድምር ጨዋታ በመጨዋት በአለም የተናቀ፣ ድሃ፣ የተሰደደና ለማኝ ሕዝብ ሆነን እንቀራለን።

እግዚአብሄር ከዚህ ያድነን !

([email protected])