ጥያቄ አለኝ ለአቶ ተስፋዬ ገብረ አብ?
ከግርማ ካሳ
«ያልተመለሰው ጥያቄ ብርቱካን መቼ ትፈታለች? የሚለው ብቻ ነበር። አሁን እሱም ቢሆን መልስ ማግኘቱ ከወደ አዲሳባ እየተሰማ ነው። ብርቱካን ሚደቅሳና የቀድሞ የደርግ ባለስልጣናት የግእዙ መስከረም ከማለቁ በፊት ቃሊቲን ለቀው እንደሚወጡ የወሬ ጭምጭምታ አለ» የሚል አነበብኩኝ፣ አቶ ተስፋዬ ገብረዓብ በቅርቡ «ብርቱካን ከተለቀቀች በኋላ» በሚል ርእስ ባቀረቡት ጽሁፋቸዉ።
ብዙዎቻችን የሰማናዉና የጠበቅነዉ ለአዲሱ አመት ብርቱካን ሚደቅሳ ትፈታለች የሚል ነበር። ነገር ግን ከአንድ ሺህ በላይ እስረኞች፣ ያዉም አብዛኛዎቹ በርግጥ ወንጀል የፈጸሙ፣ በምህረት ሲፈቱ፣ ወንጀል ሳትሰራ የታሰረችዉ ብርቱካን ሚደቅሳ ግን በቃሊቲ ነዉ ያሳለፈችዉ።
ተስፋ ማድረጉ መልካም ነዉ። የምንሰማዉን ወሬና ጭምጭምታ እግዚአብሄር እዉነት ያድርገዉ። በርግጥ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ተፈታ ማየትና ድምጿን መስማት የማያስደስተዉና የማያስፈነጥዘዉ ኢትዮጵያዊ አለ ብዬ አላስብም።
ነገር ግን ጭምጭምታዉ ተግባራዊ ሆኖ እስካላያነዉ ድረስ መዘናጋት ያለብን አይመስለኝም። አሁን የሚደረገዉ የትግሉ አቅጣጫ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በማስፈታት ላይ ማነጣጠር ይኖርበታል ባይ ነኝ። ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታት አለባት።
ይሄን ብዬ አቶ ተስፋዬ ወዳነሱት ሌላ ነጥብ ልመለስ። ወያኔን ለመታገል ዱላ ያስፈልጋል ይሉናል። «በዚህ ዘመን፣ ከወያኔ ጋር በዚህ ደረጃ (ዱላ ይዞ) ሊታገል የማይችል ፖለቲከኛ ፖለቲካውን ትቶ ገዳም ቢገባ ይሻለዋል። ሴት እህታችን ለነፃነት ስትታገል ታስራ፣ ወንድ ወንድማችን ስንቅ አቀባይ የሆነበት የተገላቢጦሽ ዘመን ላይ ደርሰናል። ትውልድ አለመኮላሸቱን የምናረጋግጠው በተግባር ብቻ ነው። የወያኔ መርህ ግልፅ ነው። አንድ ሰው የገደለ “ወንጀለኛ” ይባላል። አንድ ሺህ ሰው የገደለ ደግሞ መሪ ይሆናል። እንዲህ ከሚያስብ ሃይል ጋር ምን አይነት ትግል ማድረግ ይገባል?» የሚልም ጥያቄ ያቅርቡልናል?
ለአገር ነጻነት፣ ለሰላምና ለፍትህ የቆመችን ሴት ማስፈታት ያልቻልን እንዴት አድርገን ነዉ አገርን ልናስፈታ የምንችለዉ ? ፊደል መቁጠር የማይችል እንዴት አድርጎ ነዉ ደራሲ የሚሆነዉ ? ፔትሽኖች ሲዘጋጁ በሚሊዮን የምንቆጠር እያለን የምንፈርመዉ በመቶ የምንቆጠር ነን ። ሰልፍ ሲዘጋጁ በአሥር ሺሆች ሆነን ከተሞችን ማናወጥ ስንችል የምንመጣዉ፣ ካለን ቁጥር ጋር ሲነጻጸር፣ በጣም ጥቂቶቹ ነን። ታዲያ ቀላሉን ፊርማ መፈረምና ሰልፍ መዉጣት ያልቻልን እንዴት አድርገን ነዉ ጎንደር ተራሮችና ባሌ ጫካ ሄደን ሽፍታ የምንሆነው ? አቶ ተስፋዬ ዱላ ያስፈልጋል ሲሉን ምን ማለታቸዉ ነዉ ? «በትጥቅ ትግል ካልሆነ ወያኔ/ኢሕአዴግን መቀየር አይቻልም ! ከትጥቅ ትግል ሌላ የሚያስብ ገዳም መግባት አለበት ነዉ» እያሉን በሰላም በአገር ቤት መንቀሳቀስ ሞኝነት አድርገዉ ከወሰዱብን ታዲያ እርሳቸዉ የሚመርጡልን መንገድ የትኛዉ ነው?
እግዚአብሄር ረድቷት ብርቱካን ሚደቅሳ ጤነኛ ሆና ከቃሊቲ ከወጣች የትግሉ መሪ ሆና ትቀጥላለች የሚል ተስፋ ነዉ ያለኝ። በመታሰሯ ያሰባሰበችዉን ህዝብ ከተፈታች በኋላ የበለጠ ታያይዘዋለች። በተለያዩ ምክንያት ያልተስማሙትን ታስማማለች። እርሷ ጤነኛ ሆና ትፈታ እንጂ ከዚያ በኋላ ትግሉ ምን መልክ እንደሚይዝ አቶ ተስፋዬ ገብረአብ ያኔ ያዩታል።
በመሆኑም ብርቱካን ከተፈታች በኋላ ምን ይሆናል ብለን ማሰብ የለብንም ባይ ነኝ። ብርቱካንን ለማስፈታት የሚደረገዉ ትግል እርሷ ከተፈታች በኋላም፣ እርሷ የታሰረችበትን አላማና ግብ አንግቦ በርሷ መሪነት ተጧጡፎ ይቀጥላል።
ይህ እንግዲህ የሰላማዊዉን ትግል በተመለከተ ነዉ። ከሰላሙ ትግል ሜዳ ዉጭ የሚደረገዉን ትግል በተመለከተ ግን (በተለይም በኤርትራ በኩል የሚደረገዉ ትግል) ምን መልክ እንደያዘና እንደሚይዝ መቼም ጉዳዩን በቅርበት የሚከታተሉ ወገኖች ያጡታል ብዬ አላስብም።
በአሥመራ በኩል ትግል እናደርጋለን ከሚሉት መካከል ኦነግና የአርበኞች ግንባር ዋናዎቹ ናቸዉ። ኦነግ እዚያዉ አስመራ ዉስጥ ለሶስት እንደተከፈ ይነገርለታል። የአርበኞች ግንባር ደግሞ በዉስጡ ሥር የሰደደ ችግር ስላለበት ፣ ችግሩን እስኪፈታ ድረስ ከደጋፊዎች ገንዘብ የማሰባሰብ እንቅስቃሴዉን እንዳቆመ ኢትዮጵያ ሪቪዉ ዘግቧል።
ሌላዉ የግንቦት ሰባት ንቅናቄ ነዉ። ግንቦት ሰባት በመሰረቱ በአሁኑ ጊዜ ከነኢሕአፓ ጋር የሚመደብ ነዉ። ኢሕአፓ ፍኖት ራዲዮ እንዳላትም ግንቦት ሰባትም የራሱ ራዲዮ አለዉ። ከዚያ ዉጭ ይቅርታ ይደረግልኝና ስለግንቦት ሰባት እንቅስቃሴ ይኸዉ ሁለት አመት ተኩል ሆነ ምንም የማውቀዉ ነገር የለም።
እንግዲህ አቶ ተስፋዬ በኤርትራ በኩል የሚደረገዉን ትግል ለምን አትቀላቀሉም ከሆነ የሚሉን እኔም ለርሳቸዉ ጥያቄዎች አሉኝ ፡ የትኛዉ ትግል ? በኤርትራ በኩል ትግል አለ እንዴ ?
በነገራችን ላይ በኤርትራም ሆነ በማናቸዉም መንገድ ዜጎች ለመብታቸዉ ነፍጥ የማንሳት ሙሉ መብት እንዳላቸዉ አምናለሁ። በኤርትራ በኩል የትጥቅ ትግል እናራምዳለን የሚሉ ከአሥር በላይ ድርጅቶች አሉ። እነዚህ ድርጅቶች አንድ ሆነዉ ፣ አንድ ማእከላዊ እዝ መስርተዉ ቢነሱ አንድ ነገር ነበር። ነገር ግን ያ አልሆነም። አንዳንዶች ለዚህ ሻእቢያን ተጠያቂ ያደርጋሉ። አንዳንዶቹ ደግሞ የድርጅቶች መሪዎችን . . . ያም ሆነ ይህ በኤርትራ በኩል ይደረጋል የተባለዉ ትግል የትም ሲደርስ አላየንም።
ዝናብ ሊዘንብ ሲል ዣንጥላችንን እናወጣለን። የተጨበጠ የሚታይ ነገር ሲከሰት ያኔ በኤርትራ በኩል ስለሚደረገዉ ትግል እናወራለን። አሁን ደመና የሌለበት የጠራ ሰማይ እያለ ዣንጥላችንን ይዘን አንዞርም። እንደገና ልድገመዉና ጥያቄዉ «የትጥቅ ትግል ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም» የሚለዉ አይደለም። ጥያቄው «የትጥቅ ትግል አለ ወይንስ የለም» የሚለዉ ነዉ። ይህን መመለስ በማይቻልበት ሁኔታ ለሕዝቡ የማይሆን ተስፋ በመስጠት፣ በሰላም መታገል ገዳም እንደመግባት ነዉ ብሎ መስበክ፣ ህዝቡ ለመብቱና ለነጻነቱ በሰላም እንዳይታገል ማዘናጋት ነዉር ነዉ።
(አቶ ተስፋዬ አማርኛዬን አይተዉ በአቶ ስዬ ላይ እንዳደረጉት በተረባ እንደማይወርዱብኝ ተስፋ አለኝ። መቼም በቤተ ክህነት እንዳደገ ባለቅኔ ሰዉ ልንሆን አንችልም)