የመለስ ፓርላማ ነገ ይሰበሰባል- አወዛጋቢ የሆነዉ የብርቱካን ጉዳይ እልባት ያገኛል ይባላል

አቡጊዳ – መስክረም 24 ቀን 2003

የመለስ ፓርላማ ነገ ይሰበሰባል- በኢሕአዴጎች ዘንድ አወዛጋቢ የሆነዉ የብርቱካን ጉዳይ እልባት ያገኛል ይባላል!

99.6% የሚሆነዉ የመለስ ፓርላማ አባላት ዛሬ ወደ አዲስ አበባ የገቡ ሲሆን ነገ በኢፌሴል ፓርላማዉ እንደሚሰበሰብ ከአዲስ አበባ የደረሰን ዜና ያመለክታል። ፓርላማዉ በመጀመሪያዉ ስብሰባ አቶ መለስን ጠቅላይ ሚኒስትር አደርጎ ይሾማል ተብሎም ይጠበቃል።

በኢሕአዴግ አመራር አባላት መካከል ትልቅ ዉዝግብን እንደፈጠረ የሚነገርለት የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰርም በቀጣዮቹ ሁለት ሳምንታት ዉስጥ እልባት ያገኛል የሚል ተስፋ እንዳለ አዲስ አበባ የሚገኙ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።

ለወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በማሰብ ሳይሆን የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መታሰር ኢሕአዴግን ይጎዳል፤ በሌሎች ጠቃሚ ጉዳዮች ላይ እንዳናተኩር መሰናክል ፈጥሮብናል» በሚል በርካታ የኢሕአዴግ አባላትና ደጋፊዎች ወ/ት ብርቱካን እንድትፈታ ጠንካራ ተቃዉሞ እያቀረቡ ሲሆን ይህ በኢሕአዴግ ዉስጥ እየመጣ ያለዉ ግፊት ከአለም አቀፉ ማህበረሰብ እየመጣ ካለዉ ጠንክራ ጫና ጋር ተደምሮ የአቶ መለስን አገዛዝ አጣብቂኝ ዉስጥ እንደከተተ ምንጮቻችን ይገልጻሉ።

በዚህም ምክንያት አቶ መለስ በሚመሰርቱት አዲስ መንግስት፣ ለዚህ ትኩስና አወዛጋቢ የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጉዳይ እልባት ሰጥተዉ መገላገል እንደሚፈልጉ ከምንጮቻችን የደረሰን ዜና ሲያትት፣ ለዚህም እንዲረዳ ፕሮፌሰር ኤፍሬም ይሳእቅ በአሁኑ ወቅት አዲስ አበባ፣ በአራት ኪሎና በቃሊቲ መካከል እየተመላለሱ እንደሆነም የደረሰን ዘገባ ይገልጻል።

የወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መፈታትን በመተመለከተ አቶ መለስ የመፈታት እድሏ ዜሮ ነዉ ባሉበት አፋቸዉ በቅርብ ጊዜ በኮሎምቢያ ይቅርታ ከጠየቀች የመፈታት እድሏ ከፍ ያለ ነዉ የሚል መልስ መስጠታቸዉ ይታወሳል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በአገር ሽምግልና ወግ መሰረት፤ ለአገር ሰላምና እርቅ ስትል ይቅርታ መጠየቋን ቃሌ በተሰኘዉ ጽሁፏም በግልጽ ማስቀመጧ ግልጽ ነዉ።