ከዕለቱ ምርጥ አሣዛኝ ዜናዎች ጥቂቶቹ ነጻነት ዘገዬ

ዓለም በአሣዛኝ ዜናዎች መጥለቅለቅ ከጀመረች ዋል አደር ብላለች፡፡ አሁን አሁን የዜና ማሠራጫዎች ራሳቸው ክፉ ዜና ማወጅን በጣም ከመልመዳቸው የተነሣ መልካም ዜናን እንደቅንጦት እያዩት ይመስላል ብዙም ሲሳቡበት አይታዩም፡፡ እርግጥ ነው ከወደ አሜሪካን ሀገር በሣተላይት የሚሠራጭ ሱፕሪም ማስተር የሚባል ቴሌቪዥን ዐውቃለሁ፡፡ ይህ በአንዲት ቬትናማዊት የሂማሊያ መነኩሲት የሚመራው የ24/7 ቲቪ በዜና ዕወጃው መጥፎ ዜናን አያቀርብም (ይህች ሴት ብርሃነ ብራህማ እንደተገለጠላትና የብፅኢትነት ደረጃ እንደደረሰች ለተከታዮቿ ያወጀች ሴት ናት) ፡፡ የልማትና የዕድገት እንዲሁም የረድኤት ነክ ዜናዎችን በጥንቃቄ እየመረጠ ነው እሚያቀርብ፡፡ ይህ የቴሌቪዥን ጣቢያ በተለይ ሰው ሠራሽ አደጋዎችንና ፖለቲካ ነክ ዜናዎችን ማቅረብ ሲያልፍም አይነካው፡፡ ባይሆን የተፈጥሮ አደጋዎችን ይዳስሳል፤ ሴትዮዋም ዕርዳታ ስትሰጥና ስታሰባስብ ያሳያል፡፡ በተረፈ የሁሉም የዓለም ዜና ጣቢያዎች በተለይ በዚህ ዘመን ደግ ነገር ላለማውራት የተገዘቱ ይመስል የካሜራ አፈሙዛቸውንና የአንደበት ጦራቸውን መዓት ጠሪ ወሬዎች ላይ ሲደቅኑ ይህ ጣቢያ ትኩረቱ የልማትና የዕርዳታ ዜናዎችና ሀተታዎች ላይ ነው፡፡

ዛሬ ለምሳሌ ጥቂት መልካም ዜናዎች ነበሩ፡፡ ለነገሩ እነዚህኞቹ በአልጀዚራም ተገልጸዋል – የሚሰጣቸው ትኩረት እንደመከራው አይሆንም እንጂ፡፡ አንዱ መልካም ዜና የበርማ መንግሥት ካጎራቸው 2000 በላይ የፖለቲካ እሥረኞቹ መካከል የተወሰኑትን ሊፈታ መሆኑ ነው፡፡ ከዚህ ዜና መቼም ኢሕአዴግ ሊማርበት እንደሚቸል አልጠራጠርም፡፡ በዚህ በዘመነ ግሎባላይዜሽን ዓለም ወደአንድ መንደርነት እያመራች በምትገኝበት ወቅት ወያኔ በጭቆና አገዛዝ ከእርሱ ብዙም ከማይተናነሱት የበርማ ወታደራዊ ገዢዎች ተምሮ ያሠራቸውን የፖለቲካ እሥረኞች ካልፈታና በገፍ ማሠሩንም አቁሞ ወደ ብሔራዊ መግባባት ካልተመለሰ መቼም ቢሆን ወደሰላማዊ መድረክ አይመለስም ማለት ነው፡፡ ተስፋየን መቅኖ እንዳያሳጣብኝ አደራውን፡፡ ምኞት ደግሞ አይከለከልም፡፡

የዛሬዋን ዕለት በዋናነት ጨምሮ ከሰሞኑ አሣዛኝ ዜናዎች መካከል እነዚህ ግንባር ቀደም ናቸው፡፡ ላልተከታተሉ ጠቅለል አድርጌ ማቅረብ አሰኝቶኝ ነውና ለዜናዎቹ ቀልብ አትንፈጉ፡፡

በቀዳሚነት የማስቀምጠው ከሰባት ቢሊዮኑ የዓለም ሕዝብ መካከል ቁራሽ እንጀራ አጥቶ ለርሀብ የተጋለጠው የሕዝብ ቁጥር ሩብ ወይም አንድ አራተኛ እንደሚሆን መነገሩ ነው፡፡ በዚህ ሥሌት ወደ ሁለት ቢሊዮን የሚጠጋው የዓለም ሕዝብ በርሀብ አለንጋ እየተገረፈ ነው ማለት ነው፡፡ በአልጀዚራ የተላለፈውን ይህን ዘገባ ለተከታተለ ወገን ሰው ሆኖ መፈጠሩን ይጠላል፡፡ ከኬንያ አገኘሁት ብሎ ይህ ታዋቂ የዜና ማዕከል ያቀረበው በምሥል የተደገፈ ዘግናኝ ጥንቅር እንዳሳየው ከሆነ ሕዝቡ የሚላስ የሚቀመስ አጥተው እዚያና እዚህ የወዳደቁ አጥንቶችን በመሰብሰብ – የምን አጥንቶች እንደሆኑ እንኳን ለማወቅ ግድ በሌለው ሁኔታ – በድንጋይ ይፈረካክሷቸዋል፡፡ ከዚያም በድስት ጥደው ያፈሉታል፡፡ ቀጥለው በዕቃ እያደረጉ ለልጆቻቸውና ለራሳቸው በማደል ይጠጡታል፡፡ በእጅጉ ይሰቀጥጣል፡፡ ስንቶች የዓለምን ሀብት ለብቻ ተቆጣጥረው አላግባብ በዘረፉት ገንዘብ የሚሠሩትን እንደማያሳጣቸው ሁሉ እነዚህ ወገኖች በዚህ መልክ ይኖራሉ፡፡

ከዚህ ዜና በተያያዘ የወያኔዋ ኢትዮጵያ በመለስና ጭፍሮቹ እንዲሁም ቅጥረኛ የውጭ ሀገር ወሽካታ ‹ባለሙያዎቹ› ከሚደሰኮረው የ11 በመቶ ዓመታዊ ዕድገት ጎን ለጎን በአሁኑ ሰዓት ይህች የ85 ሚሊዮን ሕዝብ መኖሪያ የሆነች ታሪካዊት ሀገር በሚያሳዝን ሁኔታ በዓለም እጅግ ከተራቡ አሥር ሀገራት ውስጥ የመጀመሪያውን ተርታ ልትይዝ ተገድዳለች፡፡ በዛሬው ምሽት የርሀብ ዘገባ ከሰሃራ በታች ካሉ ሀገሮች ኢትዮጵያን፣ ዛምቢያንና ኬንያን ቀድሞ በርሀብተኝነት የተሠለፈ ሌላ ሀገር የለም፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅርና ሶማሊያ እንኳን ባቅሟ ከነዚህ ሀገሮች ተርታ ቀጥላ ነው ያለችው፡፡ በክፉ ነገር ሲሆን ከአንድ እስከ አምሥት እንዲያም ሲልና መሻሻል ስናሳይ ከአንድ እስከ አሥር ከመሆን የሚያግደን ነገር አለመጥፋቱ በወያኔ አመራር ምን ያህል ዕድለኞች መሆናችንን ያመላክታል፡፡ በጦርነትና በፖለቲካ አለመረጋጋት ምክንያት ፓኪስታን በክልሏ በርሀብ የአንደኝነቱን ደረጃ ይዛ 200 ሚሊዮን ከሚገመተው አጠቃላይ ሕዝቧ 83 ሚሊዮኑን ለከፋ ርሀብ በመዳረግ ግዙፎቹን ሀገሮች ቻይናንና ሕንድን የጎሪጥ እያየች የመሪነቱን ሥፍራ በኩራት ተቆናጥጣ የተጠቀሱትንና ሌሎቹን የዞኑን ሀገሮች እያሾፈችባቸው ትገኛለች – መታደል ከዚህ በላይ አለ? በማያባራ የድሮን የአየር ጥቃት በገዛ ግዛት ውስጥ የሚኖርን ምሥኪን ሕዝብ በቦምብ እያስቀተቀጡ፣ የፖለቲካ ትርምስ በፈጠረው ውስታዊ ሀሁከት የዜጎችን ዕለታዊ ሕይወት ለአጥፍቶ ተፊ የእሳት እራት ተልእኮ እየዳረጉ ሀገርን በሰላም ማስተዳደር ማለት እንዲህ ነው፡፡ አደራ ‹የራሷ አርሮባት…› እንዳትሉና ግፍ እንዳትናገሩ፡፡ ችግር ችግር ነው፡፡ የኛ ችግር እንደሕዝብ የሁሉም ችግር ነው – የነሱም የኛ፡፡ የጃፓንና የኮርያ ሕዝብ ሲቸገር – ያኔ በአንጻራዊ ሁኔታ በደጉ ዘመን – እኛ አልረዳናቸውም? ታዲያስ? የሕዝብ መጥፎ የለውም – የመሪ እንጂ፡፡

የአፍሪካውን በርሀብ የመሪነት ልጓም ግን ኢትዮጵያ ለማንም እንደማታስረክብ አረጋግጣለች፡፡ በአበባ ምርት ግን ወደፊት ሳንሸለም አንቀርም፡፡ ጥሩ ጥሩ የእርሻ ሥፍራዎች እየተመረጡ ለልማታዊ የጥፋት ባለሀብቶች ሊያውም የመጣል ያህል በርካሽ ዋጋ ስለሚቸበቸቡ በኛ ሀገር ርሀብ መንገሡ አይፈረድበትም – ‹የማያድሩበት ቤት አያመሹበትም› ይባል የለም? ወያኔ ሃያ ዓመት የሠለጠነብን እኛ ስለፈለግን እንጂ እርሱ ስለፈለገ አይደለም፤ ስለዚህ እኛ ስንፈልግ አንዲትም ቀን አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት እንደማናቆው ስለሚረዳ የሚያደርገውን ሁሉ እሚያደርገው ከልቡና ከብሔራዊ ስሜት በመነሳት ሳይሆን በማይወዳቸው ሰዎች መካከል ሳይወድ በግዱ ድንገት እንደገባ የሩቅ ብዕሲ ግዴለሻዊ ስሜት ነው፡፡ በዚያ ላይ ዕድሜ ለነሳካካዎ ግሎባል ለመሬታችን ባዕድ የሆነና በግዳጅና በውድ ዋጋ ለገበሬው የሚሸጥ ማዳበሪያ በመሬታችን ላይ እየተረጨ ካለ ማዳበሪያ ወይ ፍንክች ያለውና እህል ለማብቀል የሰነፈውን መሬት ገበሬው በየማሣው ይቁጠረው፡፡ በሀገራችን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን በመሬታችንና በለም አፈራችን ላይም የተሠራውና እየተሠራም ያለው ግፍና በደል ተዘርዝሮ አያልቅም፡፡ በፊት በመጠነኛ ዋጋና ከአዝመራ በኋላ በሚከፈል ሂሣብ ገበሬውን እያታለሉ ለማግባባትና ማዳበሪያውን እንዲገዛ እያደረጉ በሬ በጨው እንደሚታለል የዋሁን ገበሬ አነሆለሉት፡፡ ቀጥለው አፈሩ ያለማዳበሪያ ምንም ዋጋ የሌለው መሆኑን ገበሬው እንዲገነዘብ ካደረጉ በኋላ የገበሬው ሀብት ንብረት ሁሉ ተሸጦ የማይከፍከው ዋጋ በአንዲት ከረጢት ማዳበሪያ ሊያውም ሳይወድ በግዱ ይሸጡለት ገቡ፡፡ በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበሬዎች ማዳበሪያ ይሸጡ የነበሩ የገ/የስ ቤኛን አማልጋሜትድ ኩባንያን የመሳሰሉ ሌሎች ተወዳዳሪዎችን ወያኔዎች ከሕግ በላይ የሆኑ ሻጥረኛ ፍጡራን በመሆናቸው በሸርና በተንኮል ድርጅታቸውን አዘግተው ከሀገር አባረሩና ሕዝቡን አሳልፈው ለቀን ጅቦቹ ለወያኔው ኢንዳውመንታዊ ‹የደም ዋጋ› ዐሣማ ድርጅቶች ለጉናና ለአምባሰል ሸጡት – በእውነቱ የወያኔን ወንጀልና ኃጢያት መመዘንና ልኬቱን ማወቅ የሚችል አንድም ፍጡር በምድር ላይ ሊኖር አይችልም፡፡ የነሱ ዕኩይ ሥራ ተገዳደርክ አልባልና ፈጣሪ ራሱም የሚደርስበት አይመስለኝም፡፡… ብቻ የሆነው ሁሉ ሆኖ ዋናው ነገር በዴሞክራሲ ዕጦት ብቻ ሣይሆን፣ በመሪር አገዛዝ መንሠራፋትም ብቻ ሣይሆን፣ ከእግር እስከ ራሱ በጎጠኝነት ልክፍት የበከተ መንግሥት ባለቤት በመሆናችን ብቻም ሣይሆን በርሀብም በዓለም አንደኞች መሆናችንን ማወቁ ነው፡፡ እግዚአብሔር ካልጠበቀን መጪው ዘመን ከኢሕአዴግ ጋር ድቅድቅ ጨለማ ነው፡፡

ወደሌላ አሣዛኝ ዜና እንለፍ፡፡ በካናዳ አንድ ግዛት ውስጥ አደገኛ ክስተት እየተመዘገበ ነው፡፡ ይህ በቆዳ ስፋቱ ኢትዮጵያን ሁለት እሚያህል በሕዝብ ብዛቱ ግን ከ30 ሺህ የማይበልጡ ነዋሪዎች የሚገኙበት ኑናቩት የሚባል ግዛት ራሳቸውን በማጥፋት ከዓለም አንደኛ የሆኑ ዜጎችን መያዙ ዛሬ ተዘግቧል፡፡ ኢኑዊት በመባል የሚታወቁት እነዚህ የቀድሞ ኢስኪሞች ዝርያ በተለያዩ ምክንያቶች ራሳቸውን እየገደሉ በማለቅ ላይ ናቸው፡፡ ከተጠቀሱ ምክንያቶች ውስጥ ጠጪነት፣ ሀሽሽና በኑሮ እርካታ ዕጦት የተነሣ መሆኑ ተሰምሮበታል፡፡ ያሳዝናል፡፡ ፈጣሪ ልቦና ሰጥቷቸው ከዚህ መጥፎ ድርጊት እንዲታቀቡ ይርዳቸው፡፡ የኛን ቢያዩ ምን ሊሉ ነው? ‹እናቱ የሞተችበትና ወንዝ የወረደችበት እኩል ያለቅሳሉ› አሉ?

በሶማሊያ ውስጥ ካለፉት 21 ዓመታት ወዲህ በነገሠው መንግሥት አልባነትና ሥርዓተ አልበኝነት የተነሳ በተፈጠረው ሁከት ብዙ ችግሮች እየደረሱ ነው፡፡ ተስፋ መቁረጥ፣ ድህነት፣ ርሀብ፣ ሥራ አጥነት፣ የወንጀል መበራከትና የመሳሰሉት በሶማሊያ ውስጥ ከተንሠራፉ ሁለት አሠርት ዓመታትን አስቆጠሩ፡፡ በዚህም ምክንያት ከሕዝቡ አንድ ሦስተኛው ለአእምሮ በሽተኛነት መዳረጉ በጥናት ተደርሶበታል፡፡ አንድ በሕክምና ርዳታ ላይ የተሰማራ የዚያችው ሀገር ዜጋ በገነፈለ ስሜት እንደገለጸው ከሆነ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ሊሆን እንደሚችልና የህመሙ ዓይነት ደግሞ አእምሮኣዊ ብቻ ሣይሆን በሽታ የተባለ አንድም ሳይቀር ባይነት ባይነት ተግበስብሶ ወደሶማሊያ ግዛት እንደገባ በምሬት ተናግሯል – ሥነ ልቦናዊ፣ አእምሮኣዊ፣ አካላዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ በሽታዎች ሕዝቡን ተብትበው እንደያዙት ራሱ ሰውየውም አእምሮውን በሳተ መልኩ ዕጆቹን ያለ ቅኝት እያወናጨፈ በስሜት ጦዞ ሲናገር እኔም በጦዘ የዝምታ ድባብ ተውጬ አዳምጬዋለሁ – የንግግሩ መልእክትም ሆነ የአነጋገሩ ሁለመናዊ ቃና በደንብ ይገባናል፡፡ ለምን ብትሉ – የእርሱ እከክ የኔም ነውና፡፡ የማይጠቅምና የማይረባ መንግሥት ከሌለ መንግሥት ባልተናነሰ እንዲያውም በበለጠ ይጎዳል፡፡ የሌለ መንግሥት እንዴት ይጎዳል እንዳትሉ – አለመኖሩም በራሱ ጉዳት ነውና፡፡

ሌላው ዜና በአሜሪካን ሀገር የለውጥ አርበኞች ተነስተው ዎል ስትሪት የሚባለውን የሀብታም ነጋዴዎች መሸቀጫና መናኸሪያ ሊቆጣጠሩ መሞከራቸው ነው፡፡ እነዚህ ‹የዘመናት ብሶት የወለዳቸው ጀግኖቹ› አሜሪካውያን የለውጥ አርበኞች ሀብታሞቹ በየሚዲያ ተቋማታቸው ሊያላግጡባቸው ቢሞክሩም ከጊዜ ወደጊዜ ደጋፊ እያገኙ እንደመጡና ሚዲያውም (በሀብታሞቹ ቁጥጥር ሥር ያልሆነው ገለልተኛው ሚዲያ ማለት ነው) በተወሰነ ደረጃ እያገዛቸው እንደሆነ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የአሜሪካንን የሀብታሞቹን መንግሥት በመቃወም ‹እኛ 99 በመቶ ሆነን ሳለን አንድ በመቶ የማይሆኑቱ ባለጸጋዎች ሁሉንም ነገር ለብቻቸው ይዘው ይጫወቱብናል› ብለው ለመብታቸው የተነሱት እነዚህ ጭቁን ዜጎች አነሳሳቸው ሥራ እንዲያገኙ፣ ተምረው ያሰቡት ቦታ እንዲደርሱና የመኖር ዋስትናቸው እንዲረጋገጥላቸው እንጂ ለመንግሥትና ለሕገ መንግሥት ግልበጣ እንዳልሆነ በአቋም መግለጫቸው ገልጸዋል -( ያባቱን ኮቴ ከኋላ ሆኖ እየለካ ለአቅመ -ግመሮ መድረሱን በሚለካው ታዳጊ ዝንጀሮ የምትመሰለዋና የአሜሪካንን ውድቀት የምትመኘዋ ያቺ መልቲ ሀገር ኢራንም በደስታ ጮቤ እየረገጠች ናት)፡፡ እነዚህን አሜሪካውያን ብሶተኞች በሚመለከት ‹ያልተነካ ግልግል ያውቃል› መቼም አንልም – ከመነካት በላይ በደርግና በወያኔ ክፉኛ ተነቁረናልና፡፡ ለማንኛውም ፈጣሪ ይራዳቸው ከማለት በስተቀር እኛስ ለራሳችን ምን ተያዘልንና ልንረዳቸው እንችላለን?

በሰሜን አፍሪካ በኩል እሳት እየነደደ ነው፡፡ ይሄ ዓለምን እየለበለበ የሚገኘው ኢኮኖሚያዊ ቋያና ፖለቲካዊ ቀውስ በጥቂት ሀገሮች ብቻ ተወስኖ አልቀረም፡፡ የግብፁ ሆስኒ ሙባረክ በሕዝባዊ አመፅ ከሥልጣን ከወረደ ወዲህ ግብፅንና ሕዝቧን የተመቻቸው አይመስሉም፡፡ በተለያዩ የቦኩ ቁርሾዎችና ዘመን አመጣሽ የሞኝነት አመፃዎች እየታመሱ ናቸው፡፡ የሚጣሉበት ቢጠፋ ሃይማኖትን ተንተርሠው መተጋተግንና መቆራቆስን መርጠዋል፡፡ በመንግሥት የፀጥታ ኃይሎችና በተቃውሞ ሠልፈኞች መካከል በሃይማኖት ሰበብ ሰሞኑን በተነሣ ሁከት ከ24 ሰዎች በላይ ተገድለዋል፤ በርካታዎች ቆስለዋል፤ ብዙ ንብረትም ለእሳት ላንቃ ተዳርጓል፡፡ ይህ 90 በመቶ ይሆናሉ ከሚባሉቱ ሙስሊሞች ውስጥ የወጣውና 10 በመቶ ይሆናሉ የሚባሉትን የኮፕቲክ ክርስቲያን ግብጻውያንን ቤተ ክርስቲያን ባቃጠለው አክራሪ ኃይል የቀሰቀሰው የጠብ ያለሽ በዳቦ ሁከት ግብጽን የት ድረስ ሸኝቶ ለሌላ ተመሳሳይ ሁከት በመዳረግ እንደሚመለስ ገና የምናየው ይናል፡፡ ሁኔተው ግን እጅግ አስጊ ነው፡፡ የሰው ልጅ ወደ አረመኔነት እየተለወጠ ያለ ይመስላል፡፡ ከ‹ባልሽ ባሌ ይበልጣልና ሽሮ አበድሪኝ› አለቻት አሉ አንዷ ብልጥ ሚስት ሌላዋን፡፡ የሰው ልጅ የጅልነትና የለየለት የዕብደት ደረጃ ገባ ማለት እሚቻለን ‹የኔ ሃይማት ካንተ ይበልጣልና ቤተ አምልኮህን አቃጥዬ አንተንም አርጄና ጨፍጭፌ መቀጣጫ ሳላደርግህ ሃይማትህን ክደህ የኔን ተከተል!› ማለት ሲጀምር ነው፡፡ ይህን እያየን ነው፡፡ አንድነትን ለማጽናትና በተባበረ ክንድ ሀገርን ለማልማት ግብጻዊነት አንሶ ተገኝቶ ወደሃይማኖት የማያገባን ጉዳይ ውስጥ ገብተን ከተርመጠመጥን፣ ኅብረትን ለመመሥረትና በጋራ ጥረት ሀገራዊ ብልፅግናን ለማስገኘት ኢትዮጵያዊነት አንሶ ተገኝቶ የዘውግ ውሻልን በመሻት የጎጠኝነት አረንቋ ውስጥ ተዘፍቀን መምቦራጨቅ ካማረን በርግጥም ሰዎች እንደሰው ከማደግ እሚያግደን አንዳች የዕድገት ማነቆ ውስጥ ገብተናል ማለት ነውና የጤንነታችን ጉዳይ በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡
በሌላ ዜና ደግሞ ተፈጥሮ ፊቷን ያዞረችባቸው የብዙ ሀገሮች ዜጎች በጎርፍ፣ በውሽንፍርና በናዳ እያለቁ ነው፡፡ ዛሬ ለምሳሌ የቱርክ ምሥራቃዊ የባሕር ዳርቻ አካባቢ በኃይለኛ የጎርፍ ማዕበል ተመትቶ ስድስት ሰዎች የደረሱበት አልታወቀም፡፡ ብዙ ሕንጻዎች ፈርሰዋል፤ ብዙ ንብረት ወድሟል፡፡ በታይላንድም ሰሞኑን ብቻ ከ256 በላይ ዜጎች በጎርፍና በከባድ የውኃ መጥለቅለቅ አልቀዋል፡፡ አሁንም ድረስ በዋና ከተማዋ ባንኮክ በከፍተኛ አደጋ ውስጥ ትገኛለች፡፡ የአስቸኳይ ጊዜ ዐዋጅም ታውጇል፡፡ በማሌዥያ፣ በሕንድ፣ በቻይና፣ በኢንዶኔዥያ… ተመሳሳይ የተፈጥሮ አደጋዎች ሲደርሱ ሰንብተዋል አሁንም አደጋውና ሥጋቱ ገና አልተቀረፈም፡፡ በተፈጥሮ አደጋዎች ብቻ ሳይሆን በፖለቲካውና በኢኮኖሚውም ረገድ እየታመሱና እየተንገረገቡ ያሉ ሀገሮች ቁጥር የትዬ ለሌ ነው – አሜሪካንን ጨምሮ በተለይ ግሪክንና ባጠቃላይ አውሮፓን ብናይ ባንኮች እየተዘጉና ሊዘጉ እየተንጠራወዙ በከፍተኛ ችግር ውስጥ ናቸው፡፡ በዓለም ዙሪያ ብዙ ሠራተኞች ከሥራ ገበታቸው እየተፈናቀሉ ናቸው፡፡ በመካከለኛው ምሥራቅ ያለውም ሁኔታ በጣም አስጊ እየሆነ መጥቷል – ካምሡሩ እንደተለቀቀ ፈንጂ ሊፈነዳ እተንተከተከ ነው፡፡ በኃያላኑ ዘንድ ተንቆ የሚገኘው የእስራኤልና የፍልስጥኤም ጉዳይም የአርማጌዴዖንን የትንቢቶች ሁሉ ፍጻሜ ትንቢት ሊያረዳ ያቆበቆበ ይመስላል፡፡ በብዙ ሀገሮች ውስጥ ያሉ ሕዝቦች በግልጽ ባልታወጁ የኢኮኖሚና የፖለቲካ ጦርነቶች እየተቆሉ ነው፡፡ ኑሮ ከዳር እዳር እያሻቀበ ይገኛል፡፡ የሕዝብ እንግልትና ሥቃይም እንዲሁ፡፡ በሶማሊያና በሰሜን ኮርያ የገባው ርሀብም ሕጻናትንና አዛውንትን እየጨረሰ ነው፡፡ ብዙው ሕዝብ ሲታይ በቁሙ ነሁልሎ ቂል ሆኖ ይታያል – ተስፋ መቁረጥ፣ ከሃይማኖትና ከሞራል አጥሮች እየወጡ እንደልብ መሆን፣ ባለ ገንዘብ መደሰት፣ ለነገ አለማሰብ፣ ለትውልድ አለመጨነቅ፣ ለቀኒቷ ብቻ ማሰብ፣ ግዴለሽነት፣ እንስሳዊነትና ሌላም ሌላም ሰቅጣጭ ነገሮች በጣም እየተዘወተሩ መጥተዋል፡፡… ሞኝ አትበሉኝና ምፅዓት እየመጣብን ይሆን እንዴ? እንደሱማ ከሆነ እኛ ኢትዮጵያውን በተለይ ቀለጥን ማለት ነው፡፡ እንደተበታተንን ሊመጣብን? ሌላው ሰው ሁሉ ስንትና ስንት መልካም ጊዜ አሳልፎ እኛ እንዲህ ነጻነት እንደተጠማን ከሁለት ያጣ ጎመን ሆነን ልንቀር? ይህንንስ አንድዬ ጨክኖ አያደርውም! አንድ አምሥት ዓመትማ ሊሰጠን ይገባል፡፡ የተለያየና የተነፋፈቀ ተገናኝቶ፣ የተጣላና የተመነቃቀረ ታርቆና ተስማምቶ፣ የተራበ ጠግቦ፣ በጥጋብ የታወረ በአስተዋይነት የሕይወት ተሞክሮ አቅል ገዝቶና ሶብሮ፣ የደኸዬ አግኝቶ፣ የተሰደደ ወደሀገሩ ገብቶ… ጥቂት ሳንደሰትማ ምፅዓትን አያምጣው፡፡ ገና ምኑን አየንና?

አይይ… ሁሉን አሣዛኝ ዜና ልሸፍን ብዬ ብነሳ ተጎልቼ ማደሬ ነው፡፡ ባይሆን ጥቂት ልበልና ላብቃ – ሊያውም እኮ ከአንድ ጣቢያ የቀራረምኩት ነው፡፡ የሊቢያ ውሎ በመጠኑ ለድል የተቃረቡ ይመስላል፡፡ 70 በመቶውን የስርትን ከተማ አብዮተኞቹ መያዛቸው ተሰምቷል፡፡ መስዋዕትነቱ ግን አይሏል፡፡ አጥፍቶ ጠፊ ጋር መታገል መቼም ችግር ነው፡፡ የሆኖ ሆኖ በግጥም ለመጣ በግጥም ነው መልሱ እንዲሉ የጀመሩትን ጦርነት በድል ከመዘምዘም ወዲያ ሌላ አማራጭ የላቸውም – እነ አብዮተኞቹ፡፡ ቀድሞውን ባልዘፈንሽ ነው ነገሩ – ከዘፈንሽም ባላፈርሽ፡፡ በጣም ከሚያሳዝነው የዛሬ ዕለት ውሎ ግን አንዱ የመኪናው ቤንዚን አልቆበት እዚያው ስርጥ ውስት ሲድሞነሞን ከየት እንደተተኮሰ ባልታወቀ የመሣሪያ ጥይት ወይም የፈንጂ ፍንጣሪ ሁለቱም ዐይኖቹ መጥፋታቸው ነው፡፡ ዕብዱ ጋዳፊና አምላኪዎቹ ጀምበራቸው እስክትጨልም በሊቢያውያን ላይ እየደረሰ ያለው መከራና ዕልቂት የሚዘገንን ነው፡፡ ለነገሩ ድል የሚጣፍጠው እንዲህ ዜጎች ማንም ከማንም ሳይለይ ሲራኮቱበት ይመስለኛልና ለአሁኑ ሰቅጣጭ ቢሆንም ለወደፊቱ ትውልድ የሚኮራበትና በ‹እኔን ያየህ ተቀጣ› አስተማሪነቱ የታሪክ አኩሪ ቅርስ ሆኖ ሊመዘገብ የሚገባው የሊቢያውያን ብቻ ሣይሆን የመላው ጭቁን ሕዝቦች የጋራ ሀብት ይመስለኛል – ይህ ድላው በሚዘመዘምበት ወቅት( ያቺን ጥቁሮችን የማግለልና በጅምላ የማሰቃየት መጥፎ ነገራቸውን ግን ማረም አለባቸው)፡፡ በየመንና በሦርያ በዛሬው ዕለት ብቻ በነዚያ ደናቁርት የሥልጣንና የገንዘብ ጥመኞች በሽር አላሳድና አብደላ ሣለህ በጥይት ሲደበደቡ የዋሉት ንጹሓን ዜጎችም ከዕለቱ ዜና የሚካተቱ ናቸው፡፡ የዚያን የጎምቱ ሰውዬ የዘመኑ ካሙዙ ባንዳ – የዚምባብዌው ሙጋቤም ጉዳይም እንዳንዘነጋው፡፡ ካህናቱን እየለያዬ ገሚሱን ወደርሱ ሲያሰልፍ ያልደገፈው ደግሞ ሃይማኖትና ፖለቲካ ለየቅል ብሎት ሚናውን ለይቷል፡፡ ዛኑ ፒ ኤፍም እንደወያኔ/ኢሕአዴግ ሁሉ በሃይማኖቱ ሠርጎ በመግባት የልዩነት ቀዳዳ እየፈጠረ ጳጳሳቱንና ካህናቱን ማናቆሩን ተያይዞታል፡፡ ቀሪውም ምዕመንና ሕዝብ በዚያው መጠን ጎራ እዬለዬ አንዱን በመደገፍ ወይም በመቃወም መራኮት ይዟል፡፡ በዚያም ምክንያት የአንገሊካን ሊቀ ጳጳስ ሃራሬ መጥተው በዕድሜ ልክ ፕሬዚደንቱ በ‹ዳግማዊ ካሙዙ ባንዳ›ና በአኩራፊው ጳጳስ መካከል ሽምግልና ይዘዋል (ካሙዙ ባንዳ ማለት የቀድሞው የማላዊ ፕሬዚደንት የነበረ ሲሆን በ94 ዓመቱ ላይ ሆኖ የሀገሪቱ የዕድሜ ልክ ፕሬዚደንት መሆኑን ያወጀ ቅሌታም አፍሪካዊ ነው) ፡፡ ሆሆ! ቢበቃኝስ? ዓለምነህ ዋሴን ሆኜ ዐረፍኩት እኮ፡፡ ምን አገባኝና ነው አለሥራየ ጥልቅ ብዬ እንዲህ የምዳክረው?