የካምፓላ ማስታወሻ

ክንፉ አሰፋ

በምስራቅ አፍሪካ የስራ ጉብኝታችን፤ ከኪጋሊ-ሩዋንዳ ተነስተን አመሻሹ ላይ ካምፓላ ስንገባ ጸሃይ ብርሃንዋን ለጨረቃ አስተላልፋ እልም ብላ ጠፍታለች። ውቧ ካምፓላ በምሽት ከምድር በላይ 2000 ጫማ ርቀት ላይ ስትታይ በከፊል ጨለማና፤ በከፊል ብርሃን ተሸፍናለች። ይህም ከምእራቡ ዓለም ለሚገባ ተጓዥ እንግድነቱ እንዳለ ሆኖ ለጊዜው ግርታን ይፈጥራል። ‘በኢትዮጵያ የምንሰማው የመብራት በፈረቃ አባዜ እዚህም አለ እንዴ?’ ስል ጠየቅሁ ራሴን። ብዙም ሳልውል ግን ችግሩ የተፈጠረው የኡጋንዳ የኤሌክትሪክ ሀይል ማመንጫ ጣቢያው “ክፉኛ በመመታቱ” እንደሆነ ሰማሁ።

የሃይል ማመንጫው “ክፉኛ የተመታው” ታዲያ በሚሳይል ወይንም ደግሞ በተፈጥሮ አደጋ እንዳይመስላችሁ። የተመታው በሙስና ነው። በሙስና ምክንያት መብራት በፈረቃ መጠቀሙ ለሀገሬው ህዝብ ብዙም እንግዳ ነገር አይደለም። በምስራቅ አፍሪካ እንደባህል እየነገሰ የመጣው ሙስና በሚያሳዝንና በሚያሳስብበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

የኡጋንዳ ባለስልጣናት ምንም እንኳን በሙስና ይዘፈቁ እንጂ ሀገሪቷን በሚደነቅ ሁኔታ በምግብ አቅርቦት ራስዋን የቻለች ሃገር እንድትሆን ሳያደርጓት አላለፉም። ዋናው እና መሰረታዊ የሆነው ምግብ እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ በፈረቃ አይደለም የሚበላው።

የፖለቲካ ሁኔታውማ፤ በተለይ የፕሬስ ነጻነቱ ከኢትዮጵያ ጋር ሊወዳደር የሚችል ነገር አይደለም። ፍየል ወዲያ ቅዝምዝም ወዲህ ቢሆን እንጂ…

ቡጋንዳ፣ ሉጋንዳ፣ ኡጋንዳ

ሕዝቡ ቡጋንዳ፣ ዋና ቋንቋቸው ጋንዳ (ሉጋንዳ)፣ የሃገርቱ ስም ኡጋንዳ።

ኡጋንዳ በመካከለኛው ምስራቅ አፍሪካ ከምድር ወገብ አካባቢ የምትገኝ፣ በቪክቶሪያ ሃይቅ እና በነጭ አባይ ምንጭነቷ የምትገለጽ በአጭር አነጋገር ውብ አፍሪካዊት ምድር ናት። ዋና ከተማዋ ካምፓላ በሰንሰለታማ ኮረብታዎች የተከበበች ስትሆን ከተማዋን ከኮረብቶቿ አናት ላይ ሆነው ሲመለከቷት በውበትዋ ከምእራቡ ዓለም ከተሞች የላቀች መሆኗን አይጠራጠሩም።

ኡጋንዳ ከእንግሊዝ ቅኝ ግዛት ስር ነጻ ከወጣች አርባ ዓመት አልፏታል። ይህ ስርዓት ቢወገድም ቅሉ የነጮች የበላይነት መንፈስ ከኡጋንዳ ምድር ጨርሶ ጠፍቷል ለማለት አያስደፍርም። የነጭ የበላይነት ዛሬም ድረስ በኡጋንዳ ምድር ጥላውን እንዳጠላ አመላካች ፍንጮች ይታያሉና። ነጭ አሁንም በዜጎቿ አንደበት ሲመለክ ይደመጣል። አይደለም በአገልግሎት በሁሉም ዘርፎች ማለት ይቻላል ቅድሚያ ዕድል ሲሰጣቸው የሚታዩት ነጮች ናቸው፤ የጸጥታ ቁጥጥር በሚደረግባቸው ስፍራዎች እንኳን ሳይቀር ፍተሻ ነጮችን የሚመለከት ጉዳይ አይደለም። ነጭ ይታመናል ጥቁር በጥርጣሬ ዓይን ይታያል። ለዚህም ነው ፍተሻው በጥቁር ላይ ብቻ መበርታቱ።

በኢኮኖሚው ዘርፍም ቢሆን ዋና ዋና የንግድ ተቋማቷ የተያዙት በተለይም እንግሊዞች ባስገቧቸው ህንዶች ነው።

ያኔ በዘመነ ቅኝ ግዛት የተገነቡት ዋና ዋና መንገዶች ዛሬ ፈራርሰው ይታያሉ። አምባገነን ባለስልጣኖቿ ከቅኝ ግዛት በተረከቧቸው መንገዶቿ ላይ አንዲት ኢንች የማስፋፊያ ስራ አልጨመሩምና። እንደዜጎቿ እምነት የመሰረተ ልማት ተቋማቷ ላይ የማስፋፋት ስራ ሳይሰራ የቆየው በሙስና ምክንያት ነው።

የኡጋንዳ ህዝብ በእጅጉ ተግባቢና እንግዳ ተቀባይ ነው። በባህሪውም ሆነ በአነጋገሩ የሰከነ እና ረጋ ያለ በመሆኑም በአንዳንዶች ዘንድ እንደ “ፈዛዛ” ህዝብ ይታያል።

የኡጋንዳን ህዝብ ከሌሎች አፍሪካውያን ወንድሞቹ የሚለየው ለመዝናናት እና ለምሽት ህይወት የበለጠ ጊዜና ትኩረት በመስጠቱ ነው። የሴቶቹ የፊት ገጽታ እኛ መልከመልካም እንደምንለው አይነት ባይሆንም እንኳን የሰውነት ቅርጻቸው ለሞዴል የተፈጠሩ ውቦች አስመስሏቸዋል፤ ሴቶቹ በእጅጉ ግልጾች ናቸው። ወንዶቹን የተመለከትን እንደሆነ ከወንድ ኡጋንዳውያን የወር ወጪ አንድ ሶስተኛው ለአልጋ እንደሚውል ማስረጃዎች ይጠቁማሉ።

የካምፓላን የምሽት ህይወት በአንክሮ ላስተዋለ ሁሉ ያቺን ሃገር ለምን ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ ክፉኛ እንዳዳከማት ለመገንዘብ አያዳግተውም። ኤች.አይ.ቪ/ኤድስ አንድ መንደር ሙሉ ሰዎችን እንዳጠፋባት የሚነገርባት ኡጋንዳ ይህንን ታሪክ ለመለወጥ ይበል የሚያሰኙ ስራዎችን ማከናወኗም ይነገራል። በርግጥም ግልጽነትን ስታስፋፋ የህብረተሰቡን የግንዛቤ ደረጃ ከፍ ለማድረግ ያለማሰለስ ስራ አከናውናለች።

በዚህም በተለይም የአዳዲስ የቫይረሱ ተጋላጮች ቁጥር በእጅጉ ማሽቆልቆሉን ነው ዘገቦች የሚያመለክቱት። ለቫይረሱ ስርጭት በ30 በመቶ መቀነስ የመከላከልና የመቆጣጠር ስራዎቻቸው ውጤት ነው። በኡጋንዳ ዛሬ ስለወሲብ ማውራት አይነኬ(ታቡ) አይደለም። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ስለ ወሲብና ተያያዥ ጉዳዮች በግልጽ ይወያያል፤ ግልጽነታቸውም ለለውጡ እርካብ ሆኖ አገልግሏቸዋል።

ነጭ አባይ ተገድቧል….

ኡጋንዳ የነጭ አባይ ምንጭ ነች። ይህ የተፈጥሮ ሐብት ዛሬ በህብረተሰቡ ላይ ለተጋረጠው የሃይል እጥረት አለኝታ መሆኑ አልቀረም። ዜጎቿ በሃይል አቅርቦት እጥረት ይሰቃዩ እንጂ ተስፋውን የጣሉት በዚሁ በነጭ አባይ ላይ ነው። የሃይል አቅርቦት ችግሩን ለማቃለል የሚያስችል መፍትሄ ተዘርግቶላቸዋልና።

ፕሮጀክቱ ችግሩን ለአንዴ እና ለመጨረሻ ጊዜ የሚፈታ ነው። ነጭ አባይ ክ300 ሜጋ ዋት በላይ የውሃ ሃይል ያመነጫል ተብሎ ይገመታል። በጂንጃ የነጭ አባይ ምንጭ የሆነው የቡጃጋሊ ግድብ ስራ ዘጠና አምስት በመቶ (95%) ተጠናቋል።

በመጭው አራት ወር ጊዜ ውስጥ የሃገሪቱን የሃይል ምንጭ ችግር ይቀርፋል የተባለው ይህ ግድብ ሲታቀድም ሆነ ሲሰራ ታዲያ በጩኸት እና በመፈክር አልነበረም። የሃገሪቱ አርቲስቶች አልዘፈኑለትም፤ ህዝቡም በሰልፍ ትርዒት አልደለቀም፤ በድራማ አልተቀኘም፤ በመፈክር አልዛተም። በፕሮጀክቱና ስለፕሮጀክቱ እንዲጮህለትም ሆነ እንዲጮህበት አልተደረገም። እነደ”ህዳሴ”ው መዋጮ ሁሉ የዜጎች ኪስ አልተበረበረም፤ ከወር ደመወዙ የተቆረጠ ነገር የለም። ቡጋጃሊ ሲገደብ ቦንድ አልተሸጠም፤ ወታደራዊ ማርሽም አልተሰማም።

እናም ሙሴቬኒ አንባገነን መሪ ይሁኑ እንጂ የሃገሬው የሃይል ምንጭ ችግር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ተቀረፏል ሲሉ በኩራትና በድፍረት የሚናገሩበት ወቅት ላይ ደርሰዋል። በርግጥም ይህንን በቃል ሳይሆን በተግባር እያሳዩ ነው።

አባይን በፕሮፓጋንዳና በጩኸት ለመገደብ የተነሱት የኢትዮጵያ ገዢዎች ታዲያ ይህንን እያዩ ቢሸማቀቁ አይደንቅም። አዎ! “የህዳሴው ግድብ” ፕሮጀክት ዛሬ ከወሬ አልፎ መቀለጃ እየሆነ መጥቷል።

Your browser may not support display of this image.

ነጭ አባይ ቡጃጋሊ ግድብ (ፎቶ ክንፉ አሰፋ)

በቅርቡ ከኢትዮጵያ የመጣች አንዲት ወጣት ከሽሙጦቹ መካከል የተወሰኑትን ቀልድ ነግራ አሳቀችኝ። የግድቡ የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን መክፈቻም መዝጊያም መሆን ህዝቡን አሰልችቶት ኖሮ ቴሌቪዥኑን ለመክፈት “ግድቡን ክፈቱት” ሲል ቴሌቪዥኑን ለመዝጋት ደግሞ “ግድቡን አጥፉት” እስከመባል ተደርሷል። ለአባይ ግድብ የቦንድ መዋጮ የተጠየቀው ቀልደኛው ሸምሱ፤ የሰነዘረውን ሐሳብ እዚህ ላይ ማስታወሱ ተገቢነት አለው፤ “እኔ ለቦንብም ይሁን ለቦንድ ምንም ገንዘብ አላዋጣም። ባይሆን በእኔ በኩል ያለውን አትገድቡት.. ” አለ… እያሉ መቀለድ ተጀምሯል። እንደዕውነቱ አባይ በጥበብ እና በስራ እንጂ በወሬ አይገደብም።

ኡጋንዳ እና የሰሜን አፍሪካው አብዮት

በሰሜን አፍሪካ የተቀጣጠለውና እየተቀጣጠለ ያለው ህዝባዊ አመጽ ከሚያሰጋቸው ጥቁር የአፍሪካ ሃገሮች መካከል የኢትዮጵያ እና የኡጋንዳ ስም በተደጋጋሚ ሲጠቀስ ይደመጣል። ከድህነት በታች ባሉ ሐገራት እየተከሰተ ያለው የኢኮኖሚ ድቀት፣ የፖለቲካ አለመረጋጋት እና የሰብአዊ መብት ረገጣ ለህዝባዊው አመጽ በአብይ ምክንያትነት የሚጠቀሱ ናቸው።

Your browser may not support display of this image.

ጂንጃ መንገድ የገጠር ተማሪዎች (ፎቶ ክንፉ አሰፋ)

ኡጋንዳን የጎበኘ ሰው ግን “ህዝቡ በምን ምክንያት ለአመጽ ይነሳል?” ብሎ መጠየቁ አይቀርም። በተለይ በእንግዳ ኢትዮጵያዊ እይታ በንጽጽር በርካታ የተሻሉ ነገሮችን ማስተዋል ይቻላልና። የህዝቡን የኑሮ ሁኔታ እና የፖለቲካውን ድባብ ከዛሬይቱ ኢትዮጵያ ጋር ለማነጻጸር መሞከር ፈጽሞ የሚከብድ ነገር ነው።

የዚህች ወደብ አልባ ሃገር የህዝቧ የነፍስ ወከፍ ገቢ 550 ዶላር ነው። ይህም ከኢትዮጵያ የነፍስ ወከፍ ገቢ (280) በሁለት እጅ ይበልጣል። በካምፓላ ከተማ ተመጽዋች የኔ ቢጤ ፈልጎ ለማግኘት አዳጋች ነው። ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የቦዳ ቦዳ (ባለ ሁለት እግር ታክሲ) አሽከርካሪዎች ወይንም ደግሞ ጉልት ቸርቻሪዎች ራሳቸውንና ቤተሰቦቻቸውን በቀን ሶስቴ መመገብ አያዳግታቸውም። ለዚያውም የፈለጉትን ምግብ አማርጠው ይበላሉ። በዛሬይቱ ኢትዮጵያችን ግን ስጋ መብላት ብርቅ እየሆነ መጥቷል።

ዝቅተኛው ቀርቶ መካከለኛ ገቢ ያለው (ካለ) ኢትዮጵያዊ ሉካንዳ ቤትን ተሳልሞ በማለፍ ወደቤቱ ሄዶ ቤት ያፈራውን የሚመገብበት ዘመን ላይ እንደተደረሰ ነው የሚሰማው። በኡጋንዳ የምግብ ችግር የለም። ሁሉም ቢያንስ ቢያንስ ማቶኬ እየተባለ የሚጠራውን የሃገሪቱን ምርጥ ባህላዊ ምግብ በኩራት ይመገባል። በጾም ውሎ ጾሙን የሚያድር ኡጋንዳዊ ለማግኘት እጅግ አዳጋች ነው። ሃብታሙም ሆነ ድሃው፣ መካከለኛ ገቢ ያለውም ሆነ በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚገኘው ዜጋ በኡጋንዳ ምድር እስካለ ድረስ ስጋ መብላት ብርቁ አይደለም።

በጭንቅንቅነቱ ከአዲስ አበባው መርካቶ ሊነጻጸር በሚችለው ናካሴሮ ገበያ ጉብኝት ስናደርግ በአስር ሺህ ከሚቆጠር ህዝብ መካከል አንድ እንኳን የቆሸሸ ልብስ የለበሰ ሰው አላየንም። በኡጋንዳ ከተሞች በባዶ እግሩ የሚሄድ ወይንም የተቀደደ ልብስ የለበሰ ሰው ከቶውንም አይታይም። ረሃብና እርዛት በኡጋንዳ ቦታቸውን እያጡ ለመሄዳቸው አብይ ምስክር ነው።

የፕሬስ ነጻነትን ያየን እንደሆነ የኡጋንዳ ፕሬስ የምዕራቡን ያህል ቅምጥል ባይሆንም “ነጻ ነው” ብሎ በድፍረት ለመናገር በሚያስችልበት ደረጃ ላይ ይገኛል። ይህም የሙሴቬኒን አስተዳደር ተመስጋኝ አድርጎታል። በኡጋንዳ ስምንት የቴሌቪዥን ጣቢያዎች ሲኖሩ አራቱ የግል ናቸው፤ ዜጋው ከሃያ ስምንት በላይ በሚሆኑ የራዲዮ ጣብያዎች የመገልገል ዕድሉን አግኝቷል። ከበርካታ መጽሄትና ጋዜጦች ውስጥ ዕለታዊዎቹ ብቻ ከደርዘን በላይ ናቸው። ከሁለት ሺህ (2,000) በላይ የኢንተርኔት አገልግሎት ሰጭ ድርጅቶች አሉ። ይህንን በኢትዮጵያ ገዥው ፓርቲ ቁጥጥር ስር ካለው የኤሌክትሮኒክስ ሜዲያ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ጋር ለማነጻጸር የሚከብድ አይሆንም።

ከኢንተርኔት አገልግሎት አንጻር ሃያ አራት ሚሊዮን ከሚጠጋው (24ሚ) ኡጋንዳዊ መካከል ተጠቃሚው አራት ነጥብ አምስት ሚሊዮን (4.5ሚ) የሚሆነው ህዝብ ነው፤ በኢትዮጵያ ደግሞ ከሰማንያ ሚሊዮን (80ሚ) ህዝብ ውስጥ የኢንተርኔት ተጠቃሚው ቁጥር ከሶስት መቶ ስልሳ ሺህ (360,000) አይዘልም።

ዋነኞቹ ጋዜጦች እና የቴሌቪዥን ስርጭቶች የሙሴቬኒን ስርዓተ-መንግስት ሲተቹ ላስተዋለ እንግዳ ዘገባዎቹ በርግጥ በአፍሪካውያን ሚዲያዎች መሰንዘራቸውን ይጠራጠራል። ይህ ሁኔታ ጋዜጠኞችና ተንታኞች በሽብርተኝነት ተወንጅለው ወደ እስር ቤት ከሚወረወሩባት ሃገራችን ጋር ሲነፃፀር የግል ቴሌቪዥን፣ ራዲዮ እና ኢንተርኔት አገልግሎት ለኢትዮጵያ እንደ ቅንጦት በሚታይበት ደረጃ ላይ ደርሷል።

ኡጋንዳ በህዝብ ብዛቷ የኢትዮጵያን አንድ ሶስተኛ (ሲሶ) እጅ ነው የያዘችው፤ በመሆኑም መረጃው በነፃ ፕሬስ ረገድ ኡጋንዳን ከእኛ ሐገር በተሻለ ደረጃ ላይ የሚያስቀምጣት ሲሆን የኢትዮጵያን በጨለማ ዘመን ውስጥ መገኘትም ይጠቁማል።

“የጠፉ የኛ ሰዎች!”

ቁጥሩ በስታስቲክስ ባይደገፍም ከ10 ሺህ የማያንስ ኢትዮጵያዊ ስደተኛ ኡጋንዳ ውስጥ እንዳለ ይገመታል። ስደተኛው በብዛት ወደኡጋንዳ የሚገባው በተለይ በኬንያ በኩል ነው። የስደት ህይወት በኬንያ አደገኛ ነውና። ለዚህም ሳይሆን አይቀርም የተገፉ ወገኖቻችን ኡጋንዳን ለሶስተኛ ሃገር ሰፈራ እንደመሸጋገርያ የሚጠቀሙባት። በርግጥም ኡጋንዳ ለኢትዮጵያውያን ስደተኞች ደህንነት የተሻለች ስፍራ ናት።

በርዕሰ ከተማዋ ካምፓላም ከማካራሪ ዩኒቨርሲቲ ተማሪ እስከ ሺሻ ሳቢ … ከሚሊዮነር ባለሐብት እስከ መንገድ ላይ ቀናፊ ስደተኞች ይኖራሉ። ጥረው ግረው በአጭር ጊዜ ውስጥ ባለሃብት በመሆን ኑሯቸውን እዚያው ያደላደሉ ኢትዮጵያውያን ቁጥር ቀላል አይደለም።

እንደሌሎቹ ከተሞች ሁሉ የኢትዮጵያ የባህል ምግብ ቤቶች በካምፓላም ተስፋፍተዋል። ሶማሌው፣ ነጮቹም ሆኑ ኡጋንዳውያን ምግባችንን ለምደውታል። እንደነጠላ የነጣውን የሩዝ እንጀራ የለመደ የጎጃምን ነጭ ጤፍ ቢረሳ አያስደንቅም። የሩዝ እንጀራ ቶሎ ይለመዳል፤ ሱስም ያስይዛል። በየምግብ ቤቱ ሲኬድ ምናልባት ሊያስከፋ የሚችለው የዝንቦቹ ነገር ነው። ምግቡ ገና ሲቀርብ ዝንቦቹም ያንዣብባሉ።ታዲያ በአንድ እጅ ሲበሉ በሌላኛው እጅ ዝንብ ማባረሩ ግድ ይላል።

በአንጻሩም ተስፋውን ወደ አውሮፓ፣ አውስትራሊያ እና ሰሜን አሜሪካ በማድረግ ዕድሉን ለአመታት በመጠባበቅ የሚሰቃየው ወገንም ጥቂት የሚባል አይደለም።

በካምፓላ የኢትዮጵያውያንን የኑሮ ሁኔታ ለማወቅ ጓጓሁና ወደ አንድ የመንደር ውስጥ ጫት(ሽሻ) ቤት ጎራ አልኩ። በዚያም ሽሻውን በላይ በላዩ የሚያቦኑ እና ጫት የሚቅሙ ወጣቶችን አገኘሁ። እነርሱን ባየሁ ጊዜ ከተስፋዬ ገብረአብ መጽሃፍ ያነበብኩት “የባከኑ የኛ ሰዎች” የሚለው ርዕስ ትዝ አለኝ።

አራት በአራት የምትሆነዋ ያች ክፍል በዘወትር ዕድምተኞቿ ጢም ብላለች፤ እንደሚስጢር ነጋሪ ድምፃቸውን ዝቅ አድርገው የሚንሾካሾኩ የመኖራቸውን ያህል ጆሮ ለማግኘት ከጣሪያ በላይ ድምፃቸውን ከፍ አድርገው የሚያወሩትንም አስተናግዳለች። ጥቂት ጊዜ እንዳስተዋልኩ “ተስፋዬ በዚህ ስፍራ ቢገኝ አንድ ሙሉ መጽሃፍ በፃፈ ነበር” አልኩ ለራሴ። ትግስቱንና ጊዜውን ላገኘ ጸሐፊ ከእያንዳንዱ የክፍሏ ደንበኛ አንዳንድ መጽሃፍ ሊያዘጋጅ እንደሚችል ገመትኩ።

ከጎኔ ቁጭ ያለ አንድ ወጣት ሲተዋወቀኝ በአንክሮ ተመለከትኩት፤ የፊቱ ላይ አጥንቶች አግጠው ቁጠሩኝ ቁጠሩኝ ይላሉ። እግሮቹ እንደ እንዝርት የቀጠኑ ሲሆን እንደሃረግ የወረደ ጺሙን በእጆቹ ያፍተለትላል፤ ትካዜ እንደተጫጫነው አሊያም ኑሮ እንደከበደው ሁለንተናው ያሳብቃል። ከፊት ለፊቴ የተሰደሩትን ለመቃኘት ሞከርኩ የብዙዎቹ ጉንጮች በጫት ተወጥረዋል፤ ሺሻውን እየተቀባበሉ በላይ በላዩ የሚያቦኑም አሉ። የዘገዩ የደቡብ ሱዳን ወጣቶችም ሽሻ ፍለጋ ወደክፍሏ ገብተው ቦታ ቦታቸውን ያዙ። ክፍሏ በጭስ ታፍና ውላ በጭስ ታፍና እንደምታመሽ ተረዳሁ። ብዙዎቹ ስደተኛ ወገኖቻችን ካምፓላ ሲገቡ ከሞላ ጎደል በዚህች ህይወት ማለፋቸው ግድ እንደሚሆንባቸው አሰብኩ።

ግማሽ ሰዓት ባልሞላ ቆይታዬ ያየሁት እና የሰማሁትን የወገኖቼን ሁኔታ ባጭሩ ግለጽ ብባል “የባከኑ የኛ ሰዎች” ከሚለው ይልቅ “የጠፉ የኛ ሰዎች!” ማለቱን እመርጣለሁ።

በቃ! በምርቃናው ጡዘት ሌላ ዓለም ውስጥ ገብተው ከሐገራቸውም፣ ከባህላቸውም ከአዕምሯቸውም ርቀው የጠፉ ጥቂት የማይባሉ ወንድሞችን አስተዋልኩ። አንዳንዶቹ ሳይወዱ ተገደው በዚህ ህይወት እንዲመላለሱ የተፈረደላቸው ወይም የተፈረደባቸው ይመስላሉ። የአምባገነኑን የመለስ ስርዓት ሸሽት ካምፓላ ገብተው ዕድል እስኪቃና ጊዜ የሚጠብቁ የመኖራቸውን ያህል ወደሰለጠነው ዓለም የመሸጋገር ዕቅዳቸውን ሙሉ በሙሉ ሰርዘው ካምፓላን ሙጥኝ ብለው የቀሩ እንዳሉም ተረዳሁ። የቻለ የተገኘውን ስራ እየሰራ በትርፍ ጊዜው ወደዚያች አካባቢ ጎራ ይላል። ያላለለት ደግሞ በኢንዱስትሪ በበለጸገው ዓልም ውስጥ ከሚኖሩ ወንድም እህቶቹ በሚላክለት ቤሳቤስቲን እንደነገሩ እየቆጠበ ይኖራል።

በካምፓላው የጫት (ሺሻ) መንደር የአበሻው የዕለቱ ርዕሰ ጉዳይ ደቡብ ሱዳን (ጁባ) ነበረች። ተናጋሪውን ግለሰብ በቅጽል ስሙ ቢቢሲ ይሉታል። ቢቢሲ ቀላ ያለ መልከመልካም አይነት ሰው ሲሆን ከግራና ቀኝ የራስ ጸጉሩ ላይ ሽበት ጣል ጣል ብሎ ይታይበታል፤ ከንግገሩ ምሑር ነኝ ባይ አይነት ነው። ጥያቄ የሚያስነሳበት ግን ከአነጋገሩ ሳይሆን ከንግግሩ ይዘት ላይ ነው። አብዛኛው ዕድምተኛ እንደ ምሁር ተቀብሎት ቀኑን ሙሉ ጆሮውን ሰጥቶት ይውላል።

እንደሰማሁት ሃያአራት ሰዓት ሙሉ ሲያወራ ውሎ ማደሩ ግን ለቢቢሲ ድካም ሳይሆን ደስታን ነው የሚስጠው። ንግግሩን ቀጠለ፤

“አሜሪካ ለደቡብ ሱዳን ለልማት የሰጠችውን 6 ቢሊዮን ዶላር የደቡብ ሱዳን ህዝብ በነፍስ-ወከፍ ተከፋፈለው። … የአንድ ሃገር ኢኮኖሚ የሚለካው ህዝቡ ባለው ሃብት መጠን ነው፤ ስለዚህ አሁን ደቡብ ሱዳን ካደጉ ሀገሮች ተርታ ተሰልፋለች…. አልበሽር ደደብ ባይሆን ኖሮ ስልጣኑን ያስረክባቸዋል እንጂ ደቡቡን ክፍል አያስገነጥልም ነበር።…”

ከ ”ቢቢሲ” ጎን ቁጭ ብሎ የሚከድመው አበሻም እራሱን እየነቀነቀ “ልክ ነው፤ ትክክል፤…” ይላል። … አንዳንዶች ይጽፋሉ። ሌሎች በምርቃናው ጀልባ ተጭነው ወደ ሌላው ዓለም የሚቀዝፉ ይመስላሉ።

በእንዲህ አይነት ስፍራ ደግሞ ያለምንም የረባ ተግባር ረዘም ላለ ጊዜ መቆየት ፈጽሞ የሚከብድ ነው። አዎ! በትካዜ እንደተዋጥኩ ከዚያ ስፍራ ለመልቀቅ ተገደድኩ።

ለመላው አፍሪካዊ ከቅኝ ገዢዎች ቀምበር መላቀቅ ከፍተኛውን ሚና የተጫወተችው ኢትዮጵያ ናት። የኛዋ ኢትዮጵያ። ይሁንና ዛሬ እንኳን ለሌላው ልትተርፍ ቀርቶ የራሷን ልጆች በአግባቡ መያዝ ተስኗታል፤ በዲሞክራሲ እጦት ዜጎቿ በየጊዜው እንደአሸዋ ለመበተን ሲገደዱ እንጂ ሲሰባሰቡ አይታይም። ተስፋ ጨልሞባቸው በየሐገሩ ሲንገላቱ የማየትን ያህል የከበደ ነገር የለም።

በቅኝ ያልተገዛን ነጻ ህዝቦች ነን የምንል ኢትዮጵያውያን እንደ ምጽአት ስንሰደድ በቅኝ ገዢዎች ክንድ የደቀቀችው ኡጋንዳ ግን በባትሪ ቢፈለግ እንኳን አንድ የተሰደደ ዜጋ አይገኝባትም። የፍትህ እጦት፤ ስደት፤ ውርደት…

በቀጣዩ ማስታወሻዬ እስክንገናኝ ቸር እንሰንብት!

ክንፉ አሰፋ
ኢንቴቤ፣ ጥቅምት 2011 ዓ.ም.