የመስቀል በአል በከፍተኛ ጥበቃ ስር እንደተከበረ ታወቀ

ህዝብ በተሰበሰበ ቁጥር ከፍተኛ ስጋት ላይ የሚወድቀው የወያኔ አገዛዝ በመስቀል በዓል እለት ከፍተኛ ጥበቃን ሲያደርግ እንደቆየ ለማወቅ ተችሏል።

ወደ መስቀል አደባባይ በሚወስዱት ስድስቱም መግቢያዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እንደተደረገ የታወቀ ሲሆን፣ ውሃ በላስቲክ ጠርሙስ እና ሸንኮራ አገዳ ይዞ መግባት ያልተቻለበት ሁኔታ እንደነበር ታውቋል። በአንድ የፍተሻ ጣቢያ አካባቢ ቆሞ የነበረ ወጣት አንድ የውጭ አገር ዜጋ የሲጋራ ማቀጣጠያውን እንዲጥል መገደዱን ለዝግጅት ክፍላችን ገልጿል።

ህዝቡ በበአሉ ላይ፥ “ሃይል የእግዚያብሔር ነው፤ ጉልበት የእግዚያብሔር ነው። አንመካ በጉልበታችን፣ እግዚአብሔር ነው የኛ ሃይላችን።” እያለ ሲዘምርም ተስተውሏል። ይህ መዝሙር ከዘጠኝ አመታት በፊት ከአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ጀምሮ በኢትዮጵያ ዙሪያ በተደረጉ የተቃውሞ ሰልፎች ወቅት በተማሪዎች ዘንድ የሚቀነቀን ታዋቂ ዜማ መሆኑ ይታወቃል። በተለይም በወቅቱ ከዘረኛው አገዛዝ የግፍ በትር አምልጠው በየቤተከርስቲያኑ ተሸሽገው ሳለ የአገዛዙ ደጋፊ በሆነው ፓትሪያርክ ትእዛዝ እንዲወጡ የተነገራቸው ተማሪዎች ይህንን መዝሙር ያዜሙ እንደነበር ይታወሳል።

በተከበረው የመስቀል በዓል ላይ፣ ቡራኬ ሊሰጥ የተነሳው ፓትሪያርክ አቡነ ጳውሎስ ከአንዳንድ ተሰብሳቢዎች ተቃውሞ እንደተደረገበትም ለማወቅ ተችሏል።