ፍኖት ነጻነት ርእሰ አንቀጽ – ያለማቋረጥ እያደገ ያለው የዋጋ ንረት
በ1997 ዓ.ም 6.8% የነበረው የዋጋ ንረት በተከታዮቹ ሁለት አመታት 12.3 በመቶ እና 15. 8 በመቶ ደረሰ፡፡ ይህም ማለት የንረቱ እድገት መጠን በሁለት ዓመት ውስጥ 132 በመቶ ሆነ ማለት ነው፡፡ ከ1999 ዓ.ም በኋላ ያሉት አራት ዓመታት አጠቃላይ የዋጋ ንረት መጠንን ስንመለከት ደግሞ 1999 ላይ 15.8 በመቶ የነበረው በ2003 ዓ.ም 57 በመቶ ደርሷል፡፡ ይህም አጠቃላይ የአራት ዓመት የዋጋ ንረት እድገቱን 36ዐ.7 ፕርሰንት መድረሱን ያመላክታል፡፡
ከ1997 ዓ.ም ጀምሮ ያሉትን ስድስት ዓመታት አጠቃላይ የዋጋ ንረት እድገት ስንመለከት ደግሞ 714% ይሆናል፡፡ ይህም ማለት የገንዘብ የመግዛት አቅም ባለፉት ስድስት ዓመታት በ714 ፕርሰንት ወድቋል ማለት ነው፡፡
በአንፃሩ አማካይ ዓመታዊ ገቢ በ1997 ዓ.ም 165 ዶላር የነበረ ሲሆን አሁን 35ዐ ዶላር እንደደረሰ የአይኤም ኤፍ ሪፖርት ያመለክታል፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት አማካይ አመታዊ ገቢ በ112 በመቶ አድጓል ማለት ነው፡፡
ከላይ ከተመለከቱት መረጃዎች የምንረዳው በስድስት ዓመቱ የገቢ እድገትና የዋጋ ንረት እድገት መካከል የ602 በመቶ ልዩነት እንዳለ ነው፡፡ በሌላ አነጋገር እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በ1999 ዓ.ም ይኖር የነበረውን ኑሮ ዛሬ ለመኖር እንዲችል የዋጋ ንረቱ ከ14.4 በመቶ መብለጥ አልነበረበትም ወይም አማካይ አመታዊ ገቢ 1171.5 ዶላር መድረስ ነበረበት፡፡
በሃብታሙና በድሃው ዜጋ መካከል ያለው የሃብት ክፍተት እየሰፋ መሄድ እንዳለ ሆኖ የኢትዮጵያውያን የድህነት ደረጃ ባለፉት ስድስት ዓመታት በ324.7 በመቶ እንዳደገ መረዳት ይቻላል፡፡ ይህንን አሰቃቂ ሁኔታ ይበልጥ አስፈሪ የሚያደርገው ገዢው ፓርቲ ችግሩን ለማስወገድ ቀርቶ ባለበት እንኳን ለማስቆም አለመቻሉ ነው፡፡ እየወሰዳቸው ያሉት ርምጃዎችም አስተውሎት የጎደላቸው በመሆናቸው ችግሩን የበለጠ ሲያባብሱት እንጂ ሲቀንሱት አልታዩም፡፡
የኢኮኖሚ ኃይሎች (ፍላጎትና አቅርቦት) ገበያውን መምራት ሲሳናቸው መንግሥት ጣልቃ ገብቶ ማረጋጋት እንዳለበት እምነታችን ነው፡፡ ይህ ሲባል ግን መንግሥት የገበያ ኃይሎችን መቆጣጠር ወይም መተካት አለበት ማለት አይደለም፡፡ በትክክል መሥራት እንዲችሉ የሚረዱ የፊስካልና የገንዘብ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ በማድረግ የኢኮኖሚውን አቅም ያጠናክራል እንጂ፡፡
በእርግጥ ገዢው ፓርቲ ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ የፖሊሲና የቀጥተኛ ጣልቃ ገብነት ርምጃዎችን ወስዷል፡፡ እዚህ ላይ የሚነሳው ዋናው ጥያቄ ታዲያ ለምን የዋጋ ንረቱ የበለጠ እየተባባሰ ሄዴ? የሚለው ነው፡፡
የኢህአዴግ መሠረታዊ ችግር የችግሩን መነሻ ለይቶ ለማወቅ አለመቻሉ ላይ ነው፡፡ ኢህአዴግ የዋጋ ንረቱ በተከታታይ እየተመዘገበ ያለው የኢኮኖሚ እድገት የፈጠረው ነው ብሎ ያምናል፡፡
እ.ኤ.አ በ1929 በአሜሪካ የተከሰተው የኢኮኖሚ ዝቅጠትን ተከትሎ የተስፋፋው የኬንዚያውያን (Keynesian) የምጣኔ ኃብት ባለሙያዎች አስተሳሰብ በምጣኔ ኃብት እድገትና በዋጋ ንረት መካከል ቀጥተኛ ግንኙነት ስለአለ መንግሥት በከፍተኛ ኢንቨስትመንትና የሥራ ዕድል ፈጠራ ኢኮኖሚውን ሲያሳድግ የሕዝብ ገቢም አብሮ ያድጋል የሚል ነው፡፡ በመሆኑም የፍጆታ ወጪ መጠን ይጨምራል፡፡ ይህም የሸቀጦችና የአገልግሎት ዋጋ እንዲንር ያደርጋል የሚል በመሆኑም ኢኮኖሚው ባደገ ቁጥር የዋጋ ንረቱም ይቀጥላል ማለት ነበር፡፡
ይህ አስተሣሰብ በወቅቱ ትክክለኛ የነበረ ቢሆን በ1970ዎቹ የታየው የስራ አጥነትና የዋጋ ንረት “Stagflation” በተመሣሣይ ጊዜ በመከሰቱ (Stagflation) ውድቅ እንዲሆን አድርጎታል፡፡ በሃገራችን በአሁኑ ሠዓት እየታየ ያለው ክስተትም ከ1970ዎቹ የምዕራባውያን የኢኮኖሚ ቀውስ ጋር ተመሣሣይነት አለው፡፡
የዋጋ ንረቱ ሥራ አጥነቱ በእጅጉ እየተባባሱ ናቸው፡፡ ከገቢ አንፃር ሲታይም ከላይ እንደተገለፀው ባለፉት ስድስት ዓመታት ውስጥ የዋጋ ንረት በ714 በመቶ ሲያድግ ዓመታዊ ገቢ በ112 ፕርሰንት ብቻ ነው ያደገው፡፡ በመሆኑም በሃገራችን ያለው የዋጋ ንረት የኢኮኖሚው እድገት የወለደው ነው ሊባል ፈፅሞ አይችልም፡፡
በአንድነት ፓርቲ ዕምነት እይታ የዋጋ ንረቱ መሠረታዊ ምክንያቶች የሚከተሉት ናቸው፡-
1. መንግሥት ከፍተኛ ብዛት ያላቸው የገንዘብ ኖቶችን አሣትሞ በኢኮኖሚው ውስጥ መርጨቱ፣
2. የመንግሥት ወጪ መጠን በከፍተኛ ደረጃ እያደገ መምጣቱ፤ ይህም በሃገር ውስጥ ምርት አቅርቦት እድገት አለመደገፉ፣
3. በውጭ ምርቶች ላይ መሠረቱን የጣለው አቅርቦትና የውጭ አገር ምርቶች ዋጋ መናሩ፣
4. የብር ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየወደቀ መምጣትና የውጭ ምርት አቅርቦትና ፍላጐት አለመጣጣም፣
5. የመንግሥት የነዳጅ ድጎማ መነሳት፣
6. የመሠረታዊ ዕቃዎች ፍላጎትና አቅርቦት ከፍተኛ ሁኔታ አለመጣጣም፣
7. መንግሥት የግሉን ዘርፍ ተክቶ አቅርቦትና ሥርጭትን ለመቆጣጠር የሚያደርገው ጥረት፣
8. በግል ባንኮች ላይ ተጥሎ የነበረው የብድር ጣሪያ የአገር ውስጥ ምርትንና ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦችን አቅርቦት መገደቡ፣
9. በግል ባንኮች ላይ የተጣለው የግምጃ ቤት ሰነድ ግዢ ግዴታ የሃገር ውስጥ ምርትንና ከውጭ የሚገቡ ሸቀጦች አቅርቦትን የሚገድብ መሆኑ የሚፈጥረው የአቅርቦት እጥረት፣
10. በመሬት ፖሊሲው ምክንያት የመሬትና የገበሬው ምርታማነት መቀነስ፡፡ ይህንንም ተከትሎ የሃገር ውስጥ ምርት አቅርቦትና ፍላጎት አለመጣጣም፣
11. የመሠረተ ልማት ዝርጋታ ውስንነትና የዜጎች ከክልል ወደ ክልል ተንቀሳቅሶ የመሥራት መብት መገደብን ተከትሎ የምርትና የሰው ኃብት እንቅስቃሴ መወሰኑ፡፡ በዚህም ምክንያት የሰው ኃብትና ምትርት ከፍተኛ አቅርቦት ካለበት አካባቢ ወደ ከፍተኛ ፍላጎት ያለበት ቦታ ለመንቀሳቀስ አለመቻሉ በሃገራችን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ በመምጣት ላይ ላለው የዋጋ ንረትና የኑሮ ውድነት ዋነኛ ምክንያቶች ናቸው፡፡
እነዚህን ችግሮች በአንክሮ ስንመለከት የሁሉም ምክንያቶች መነሻ የተዛቡ የመንግሥት ፖሊሲዎችና አስተውሎት የጎደለው የመንግሥት ጣልቃ ገብነት እንደሆነ እንረዳለን፡፡
በመሆኑም መንግሥት ይህን ውስብስብ ችግር ለመፍታት ቁርጠኝነቱ ካለው በመጀመሪያ ደረጃ የልማት እስትራቴጂውና ፖሊሲዎቹ ላይ መሠረታዊ ለውጥ ሊያደርግና ከግብታዊ ጣልቃ ገብነት ሊቆጠብ ይገባል፡፡ ይህን የማያደርግ ከሆነ ግን እየተባባሰ ያለው የኑሮ ውድነትና የዋጋ ንረት ማቆሚያ የሌለው እንደሚሆንና ካሁኑ የባሰ የተወሳሰበ ሰብአዊና ማሕበራዊ ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል ልብ ሊል ይገባል፡፡
ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።
የፍኖት እትም አሥርን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ