ሽብር ለማስነሳት ይንቀሳቀሳሉ የተባሉ ወጣቶች አሁንም እየታደኑ በመያዝ ላይ መሆናቸውን የደህንነት ምንጮች ገለጡ
በቅርቡ ሰላማዊ ሰልፍ ለመጥራት ሲዘጋጁ የነበሩ 6 ወጣቶች ከተያዙ በሁዋላ፣ የወጣቶቹ ጉዋደኞች ናቸው የተባሉት ሁሉ እየታደኑ በመያዝ ላይ መሆናቸውን ለማወቅ ተችሎአል።
ሰሞኑን በወያኔ ጸጥታ ሃይል ከተያዙት ወጣቶች መካከል 4ቱ በመገናኛ አካባቢ፣ 2ቱ ደግሞ በመርካቶ እንደተያዙና በ እስር ቤት ከተወሰዱ ቦኋላ በሽብረተኛው የመለስ ዜናዊ የጸጥታ ሰራተኞች እጅግ አሰቃቂ የሆነ ድብደባ እንደተፈጸመባቸው የደረሰን መረጃ ያመለክታል።
ወያኔ አለኝ በሚለው ህገመንግሥት ሰላማዊ ሰልፍ ማድረግ እውቅና ከተሰጣቸው መብቶች አንዱ እንደሆነ ቢታወቅም ህገመንግሥቱን ከለላ አድርገው በአደባባይ ሰላማዊ ሰልፍ ለማካሄድ ሲንቀሳቀሱ የነበሩትን ወጣቶች ስብስቦ በሽብርተኝነት ሥም እስር ቤት ማጎርና ሂሊናን በሚሰቀጥጥ ጭካኔ በግርፋት ማሰቃዬት፤ ወያኔ ስልጣን ከያዘ ከ20 አመታት ቦኋላም ቢሆን ጫካ በነበረበት ወቅት ከተጠራመተው የአውሬነት ባህሪው ገና ያልተላቀቀ መሆኑን ያሳያል የሚሉ በርካቶች ናቸው። ወያኔ በብሄር ጥላቻ አእምሮአቸው የቦዜ አባላቱን በገራፊነት ባሰማራባቸው የማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ የታሰሩ እነዚህ እስረኞች እጅግ አሰቃቂ የሆነ ድብደባ እንደተፈጸመባቸውና በሀይል የግንቦት7 አባላት ነን ብላችሁ መስክሩ እየተባሉ እንደሚጠየቁ ከደህንነት አካባቢ የተገኙ መረጃዎች ያጋልጣሉ።
እንዲሁም ወጣቶቹ ዘራቸው እየተሰደበ በእንጨት ላይ ተንጠልጥለውና ተገልብጠው እንደሚገረፉ ፣ ምግብ ሳይበሉ እንዲውሉ እንደሚደረጉ፣ በአንድ እግራቸው ለረጅም ሰአት እንዲቆሙ እንደሚገደዱ የደረሰን መረጃ አክሎ አመልክቷል።
በምርመራ እና በድብደባ ወቅት ሁሉም መርማሪዎች ከአንድ ብሄር የመጡ መሆናቸውን የሚናገሩት ምንጮች፣ በጥበቃ ሥራ ላይ የተሰማሩ የሌሎች ብሄር አባላት በሽብር ተጠርጥረው ከታሰሩት እስረኞች ጋር እንዳይገናኙ ይከለከላሉ ተብሎአል።
በወያኔ እስር ቤት ያለው ዘረኛነት ያስመረራቸው እንደነ አቶ ክንፈ ሚካኤል ደበበ የመሳሰሉት ደፋር ፖለቲከኞች ለምርመራ ከተመደቡት ህወሀት መርማሪ ፖሊሶች ጋር እስከ መሰዳደብ መድረሳቸውን፣ ምንጮች አክለው ገልጸዋል። ይህ በዚህ እንዳለ እነ አርቲስት ደበበ እሸቱ ከሌሎች እስረኞች ጋር እንዳይገናኙ መደረጋቸውን ለማወቅ ተችሎአል።