በአንድ ሰው ስሜት የምትገዛ አገር!!!
ከምድር በታች ኢትዮጵዊያንን የሚያስተዳድር አንድ ህግ ብቻ አለ።ይህ ህግ የመለስ ዜናዊ ስሜት ነው። ይህ ስሜት ደግሞ በጫት፤በሲጋራና በመጠጥ ሱሶች የተበከለ ብቻ ሳይሆን ጥልቅ በሆነ ክፋትና ጥላቻ መንፈስ የተሞላ ነው። ይሄም መንፈሱ ጭካኔን፤ ጭካኔውም ፍርሃትን ፈጥሮበት አገራችንን እያሸበራት ይገኛል።
መለስ ዜናዊ ጫቱን ቅሞ ሲያበቃ የራሱ ጥላ ጭምር ግንቦት ሰባትን እየመሰለው ያየውን ሁሉ ያዙልኝ እሰሩልኝ ግደሉልኝ እያለ መቃዥት ከጀመረ ሰንብቷል። መለስ ዜናዊን የሚያቃዥውና የሚያስበረግገው የፍትህ፤ የእኩልነት፤ የህግ የበላይነት፤ የዴሞክራሲያዊ ተቋማት ግንባታ፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ ጥያቄዎች ናቸው። እነዚህ ሰው የመሆን ጥያቄዎች የሁሉም ጥያቄዎች ናቸውና መለስና በዙሪያው የተሰበሰቡ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ ጋሻ ጃግሬዎቹን ያሸበሩዋቸዋል።
መለስ ዜናዊና ግብረ-አበሮቹ ዴሞክራሲያዊ ተቋማት እንዲገነቡ ሲጠየቁ ይሸበራሉ። የእነዚህ ተቋማት በነጻነትና በህግ መቋቋም የመለስ ዜናዊና የግብረ-አበሮቹን ህልውና ከመሰረቱ የሚንድ ነው። የዚህ ቡድን የህልውናው መሠረት የቆመው በዝሪፊያ ነው። ይህን ዝርፊያ የሚጠይቅ፤የሚከታተልና ሌባውን ለፍርድ የሚያቀርብ አካል እንዲፈጠር የሚጠይቅ አካል ሁሉ በአሸባሪነት ይፈረጃል። ከአገሪቷ ካዝና ውስጥ 8.5 ቢሊዮን ዶላር ወጥቶ በውጭ ባንክ ውስጥ ተደብቆ መቀመጡን የተባበርት መንግስጠታት ከነገረን በኋላ ይሄ እንዴት ሆነ ብሎ የሚጠይቅ አካል አሸባሪ ነው።የአገሪቷን ለም መሬት ለባእዳን አልፎ የተሰጠው እንዴትና በምን ሁኔታ ነው ብሎ መጠየቅ አሸባሪነት ነው። ባገሪቷ ብሄራዊ ባንክ ውስጥ የተቀመጠ ወርቅ በባሌስትራ ተተክቶ ሲገኝ ይሄ እንደምን ሁኖ ተፈጸመ ብሎ መጠየቅ አሸባሪነት ነው።አስር ሺህ ቶን ቡና የደርሰበት ጠፋ ሲባል ገና በአውቶብስ ላይ ሊጠመድ የታሰበን ቦንብ ይዤ አከሸፍኩ የሚለው ቡድን አስር ሺህ ቶን ቡና የገባበትን እንደምን ማወቅ ተሳነው ብሎ መጠየቅ አሸባሪነት ነው። ይህን መሰሉን ወንጀል ማን እንደፈጸመው የሚከታተል ህጋዊና ገለልተኛ አካል ማቋቋም ማለት በገዛ አንገት ላይ ማነቆ ማስገባት ስለሚሆንበት መለስና ቡድኑ በጄ አይሉም። በተግባር ከተገለጡት የመለስ ዜናዊ አሸባሪ ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ እነዚህ ናቸው።
መለስ ዜናዊና ግብረ አበሮቹ የህግ የበላይነት ጥያቄ ሲነሳ ይሸበራሉ።መለስ ዜናዊና ግብረ-አበሮቹ ህግን የሠሩት ዜጎችን ለማጥቂያነት ነው እንጂ በአገሪቷ ውስጥ ሥርዓትና እኩልነት እንዲሰፍን አስበው አይደለም። በዚያ ጠባብ ብሄረተኛ አመለካከታቸው ያወጡት ህግ ውስጥ ያልተካተተ ሁኔታ ቢፈጠር እንኳ እድሜ ለጫት በአንዲት ጀንበር ህግ አውጥተው አድረው ዜጎችን ለማንገላታት ይጠቀሙበታል። መለስ ዜናዊ ወደ ዱር ከገባ ጀምሮ ከህግ በላይ ሁኖ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል ሲፈጽም የኖረ ነው።ከብዙ ወንጀሎቹ መካከል ጥቂቶቹን ብቻ እናስታውስ። የሃውዜን ህዝብ ሆን ተብሎ ገበያ እንደወጣ እንዲጨፈጨፍ የተደረገው በመለስ ዜናዊ መሪነት ነው።ለርሃብተኛ የተመጸወተውን የነፍስ አድን እህል በሱዳን ገበያዎች ልኮ አሽጠው የረሃበተኛውን ገንዘብ በግል ባንክ እንዲቀመጥ የተደረገው በመለስ ዜናዊ መሪነት ነው። አባቶችን በህጻናት ልጆቻቸው ፊት ማዋረድና ህጻናቱ የአእምሮ ጭንቀት ውስጥ እንዲወድቁ የሚደረገው በመለስ ዜናዊ መሪነት ነው።ዜጎች ከያሉበት እየተለቀሙ ለመስማት በሚቀፍ ሁኔታ በዘራቸው ምክንያት እየተሰደቡ ሰቆቃ እንዲፈጸምባቸው የሚደረገው በመለስ ዜናዊ መሪነት ነው። በሞት አፋፍ ላይ የደረሱ ሩጦ ማምለጥ የማይችሉ ደካማ ሽማግሌዎችና አሮጊቶች ተይዘው የሚገረፉበት ዘመን የመለስ ዜናዊ ዘመን ነው።አሸባሪነት ማለት እንዲህ ዓይነት ነውር ተግባራትን መፈጸም ነው እንጂ የህግ የበላይነት ይከበር ማለት አይደለም።
መለስ ዜናዊና ቡድኑ ነጻ ሚዲያ በአገሪቷ ውስጥ እንዲፈጠር ሲጠየቁ ይሸበራሉ። ዛሬ ጎሬቤታችን ኬኒያ ከአስር በላይ የግል ቴሌቭዥን ጣቢያዎች አሏት። በኬኒያ ምድር መንግስት የሚሰራው ክፍም ሆነ ደግ ነገር ከህዝቡ ተሰውሮ አይቀርም።አንድ ኬንያዊ በራሱ ቋንቋ ከሚተላለፍ ከአስር በላይ የተሌቭዥን ጣቢዎች መካከል ደስ ያሰኘውን መርጦ ማየት ይችላል። ይሄ ግን ለኢትዮጵያዊያን የሚፈቀድ አይደለም። ይሄንንም የጠየቀ ከተገኘ አሸባሪ ተብሎ የእድሜ ልክ እስራት ይጠብቀዋል። የህዝብ ዓይንና ጆሮ ሆኖ ለህብረተሰብ እድገት ከፍተኛውን አስተዋጾ የሚያበረክተውን ነጻ ሚዲያ መከልከል ነው እንጂ አሸባሪነት ይሄ እንዲኖር መጠየቅ አይደለም። መለስ ዜናዊና ቡድኑ ነጻ ሚዲያ ቢቋቋም የሰሯት ወንጀል ሁሉ በመረጃ እየተደገፈች አደባባይ መውጣቷን ጠንቅቀው ስለሚረዱ ነጻ ሚዲያ እንዲኖር የሚጠይቀውን ሁሉ በአሸባሪነት ፈርጀው ያስራሉ፤ ሰቆቃ ይፈጽማሉ፤ይገድላሉ። እንዲህም በማድረግ ሽብረተኛ ተግባራቸውን ይገልጣሉ።
መለስ ዜናዊና ግብረ-አበሮቹ ገለልተኛና ነጻ የሆነ የሰብዓዊ መብት ተመልካች ተቋም እንዲኖር ሲጠየቁ ይሸበራሉ።ገለልተኛና ነጻ የሆነ የሰብዓዊ መብት ተመልካች ተቋም ቢቋቋም መንግስት የሚጎዳው ምንም ነገር አልነበረም። እነ መለስ ግን ገለልተኛና ነጻ ተቋም እንዲቋቋም የማይፈልጉት አንድ መንግስት ማሟላት ያለበትን መሠረታዊ ተፈላጊ ሁኔታዎችን ስለማያሟሉና ሃልፊነት የሚባል ነገር ስለማይሰማቸው ነው። ይሄ ቡድን የሚያወቀው የሰዎችን መብት ረግጦ የፈለገውን እስከሚሰለቸው ድረስ አስሮ፤በፈለገው ላይ የሞት ፍርድ ፈርዶ፤ ያልፈለገውን ደግሞ በጠራራ ጸሃይ ገድሎና ሜዳ ላይ ጥሎ ሲኖር እንጂ ለሰው ልጆች መብትና ክብር ሲሰራ አይደለም። የሰው ልጆችን ሲገድል ሲያስር ሲያሰቃይ የኖረ ቡድን ገለልተኛና ነጻ የሆነ የሰብዓዊ መብት ተመልካች ተቋም ይቋቋም ሲባል ይሸበራል። ይሄንንም የጠየቀ አካል ከተገኘም አሸባሪ ይባልና የሞት ፍርድ ይፈረድበታል።ይሄም ሌላ የአሸባሪነታቸው ጠባይ መገለጫ መንገድ ነው።
በአጠቃላይ በመለስ ዜናዊ ዘመን ሰብዓዊ መብትና የህግ የበላይነት ይከበር፤ሌባ ለፍርድ ይቅረብ፤ መልካም አስተዳደር ይስፈን፤ ዜጎች ሁሉ በእኩልነት ይኑሩ፤ ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት ያለገደብ ይፈቀድ ማለት አሸባሪነት ነው። እነመለስ ዜናዊ እነዚህን መብቶች ገፈው ዜጎችን ከሰው በታች አድርገው ለመግዛት ባላቸው ጽኑ እምነት ዜጎችን እያሸበሩ ይገኛሉ። ይሄን መብት ረገጣ ሽብር እምቢ በማለት በመለስ ዜናዊ “አሸባሪ” መባል የሊሻን ሽልማት ነው። በመለስ ዜናዊ “አሸባሪ” መባል እንደ በላይ ዘለቀና እንደ አብዲሳ አጋ ስመ ጥር አርበኛ መሆን ማለት ነው። በመለስ ዜናዊ አሸባሪ ተብሎ መጠራት እንደ መጽሃፍ ቅዱሱ ሙሴ ከቤተ-መንግስት ምቾት ይልቅ የተገፉና የተበደሉ ወገኖችን ወገኖቼ ብሎ ለእነርሱ ነጻ መውጣት ራስን መስዋእት አድርጎ ማቅረብ ነው። በዚህ ዘመን አሸባሪ መባል መለስ ዜናዊ ላቆመው በዝሪፊያ በዘረኝነትና በወንጀል ስርዓት ውስጥ አልሳተፍም ብሎ ለእውነትና ለፍትህ ጸንቶ መቆም ማለት ነው።በዚህ ዘመን አሸባሪ መባል መለስ ዜናዊ ላቆመው ጣኦታት አልገዛም ለሚሉ ብርቅየ ዜጎች የሚሰጥ የክብር ሽልማት ነው።
ዛሬ የመለስ ዜናዊን የክፋትና የዘረኝነት ሥርዓት በመቃወማቸው አሸባሪ የተባሉት ምርጥ የአገራችንን ልጆች ታሪክ በክብር መዝገቡ ይመዘግባቸዋል።ኢትዮጵያችን ስትፈርስ፤ ለም መሬቶቿ ለባእዳን ተላልፈው ሲሰጡ፤ ዜጎቿ በመከራ ውስጥ በሆኑ ግዜ፤ የሴቶቻችን እንባ እንደ መጽሃፍ ቅዱሷ ራሄል እንባ ጽዋውን ሞልቶ ሲፈስ አይተው ዝም አላሉምና ስማቸውን ትውልድ ሁሉ በክብር እንዳነሳው ይኖራል።
በመጨረሻም በጫት፤ በሲጋራና በመጠጥ ሱስ የናወዘውንና የሰው ደም ያሰከረውን መለስ ዜናዊንና ግብረ-አበሮቹን ከነ-ጣኦቶቻቸው ከኢትዮጵያችን ላይ እንዲነሱ የሚደረገው ትግል በውጭም በውስጥም ተጠናክሮ ይቀጥላል። እነዚህን ወሮ በላዎች ለረዥም ግዜ መሸከም ማለት አገራችንን ለከፋ ውርደት አሳልፎ መስጠት ማለት ነው። እነዚህ ሆዳቸው አምላካቸው ክብራቸው በነውራቸው የሆኑ ፈጣሪ የማያውቁ ሰውንም የማያፍሩ እርባና ቢስ ቡድኖች ከተቆናጠጡት ወንበር ወርደው ፍትህ እንዲነግስ፤ ነጻነት እንዲሰፍን፤እኩልነት እንዲታወጅ፤ የዴሞክራሲ ወጋገን በአገራችን እንዲንጸባረቅ ማድረግ ለራሱ ክብር ከሚሰጥ ዜጋ ሁሉ የሚጠበቅ ተግባር ነው። በእኛ በኩል የቀረን አማራጭ ይሄው ብቻ ነውና የጀመርነውን ትግል አጠናክረን እንቀጥላለን እንጂ ለደቂቃም ቢሆን አንዘናጋም።
ድል ለኢትዮጵይ ህዝብ ይሁን !!!