የወያኔ ጸጥታ ሃይሎች በደቡብ ኢትዮጵያ የሀዲያና አላባ አካባቢ ነዋሪዎች ላይ በከፈቱት ተኩስ እሩምታ የ4 ንጽሃን ህይወት መቀጠፉንና በርካቶች መቁሰላቸው ተዘገበ

በሃዲያ ዞን የባዳወቾ ወረዳ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ የአላባ ብሄረሰብ አባላት የሚኖሩበት አከባቢ በአላባ ልዩ  ወረዳ ስር እንዲካለል ቀድም ሲል ያቀረቡት ጥያቄ መልስ ባለማግኘቱ የተነሳ በተፈጠረው ችግር፤ ችግር ፈጣሪ የሆነው የወያኔ ጸጥታ ሰራተኞች በህዝቡ ላይ በከፍቱት የተኩስ እሩምታ ከ20 ሰዎች በላይ በጥይት መመታታቸውና ከመካከላቸው የ4ቱ ህይወት ወዲያውኑ ማለፉን ዘጋቢያችን ከስፍራው ካስተላለፈው ዜና ለመረዳት ተችሎአል።

የአላባ ህዝብ ለተቃውሞ በመውጣቱ ምክንያት የፈደራል ጸጥታ ሰራተኞች በቦታው ደርሰው ህዝቡን ለመበተን በከፈቱት ተኩስ የቆሰሉት በርካታ ሰዎች በአሁኑ ሰ ዓት በአዋሳ ሆስፒታል ውስጥ ህክምና እርዳታ እየተሰጣቸው መሆኑን የጠቀሰው ዘጋቢያችን፤ የወያኔ ፈደራል ፖሊሲ በአሁኑ ሰዓት  በአካባቢው በብዛ ተሰማርቶ እንደሚገኝ አስታውቆአል።

ወያኔ በከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲው ለዘመናት በሰላምና በፍቅር ተቻችሎ ይኖር የነበረውን ህዝብ በመለያየት በዘረጋው የአስተዳደር መዋቅር ቅር የተሰኙት የደቡብ ህዝቦች በተለያዩ ጊዜያቶች ተመሳሳይ የሆነ ጥያቄ ሲያቀርቡ እንደነበር የሚታወስ ሲሆን  ከወያኔ ይሰጥ የነበረው ምላሽ ግን ፍጹም ፋሽስታዊ በሆነ ጭካኔ በጥይት መደብደብና ጸጥ ማሰኘት መሆኑ ተደጋግሞ መከሰቱ አይዘነጋም።

ባደወቾ ወረዳ ፕሮፌሰር በየነ ጴጥሮስ በተደጋጋሚ ለምርጫ እየተወዳደሩ ያሉበት ወረዳ ሲሆን በአሁኑ ሰዓት የወያኔ ፌደራል ሃይል በስፍራው ገብቶ ለማረጋጋት ቢጥርም ከፍተኛ የጸጥታ ችግር እንዳለና ነዋሪው አከባቢውን ጥሎ ወደ አጎራባች ወረዳዎች እየተሰደደ መሆኑን ከስፍራው የደረሰን ዜና አመልክቷል። አራቱን ሰዎች በጥይት መትተው የገደሉት የሃዲያ ዞን ፖሊሶች መሆናቸውንም ስማቸውን መግለጽ ያልፈለጉ ሰዎች ለኢሳት ምንጭ እንደተናገሩ ኢሳት በትናንትናው ዕለት ዜና እወጃው ዘግቦታል።

በ1995 አመተምህረት በአዋሳ ላይ በ1996 ደግሞ በጋምቤላ ላይ የተፈጸመው አስቃቂ ጭፍጨፋ በክልሉ የሚኖሩ ብሄር ብሄረሰቦች አንስተውት ከነበረው አስተዳደራዊ ክልሎች ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይታወቃል።

ወያኔ በተፈጥሮ ለምና ድንግል የሆነውን ወልቃይት ጠገዴን፤ ሴቲት ሁሜራና ፤ እንዲሁም በወሎ ክፍለሃገር ስር ይተዳደሩ የነበሩትን ቆቦንና ራያን የመሳሰሉትን ቦታዎች በሃይል ወደ ትግራይ ክልል እንዲዛወር እንዳደረገ፤  በምስራቅ ኢትዮጵያ የሱማሌንና ኦሮሞ ብሄሮችን የሚያዋስኑ ቦታዎች እንዲሁ ለግጭትና ለ እርስ በርስ ጦርቶች ሚቹ ምክንያት እንዲሆኑ እንዳደረገ ተደጋግሞ ሲዘገብ መቆየቱ አይዘነጋም።