በሎንዶንና በኦስሎ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የወያኔ አገዛዝ ተቃዋሚዎችን በሽብርተኝነት እየፈረጀ ማሰሩን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ወጡ
የሥልጣን ዘመኑን እስከወዲያኛው ለማራዘም የሚችል መስሎት የሚቃወሙትን ሁሉ በሽብርተኝነት እየፈረጀ ዘጎችን ወደ እስር ቤት ማጎር የጀመረው የመለስ ዜናዊ አገዛዝ ያለአገባብ እያሰቃያቸው ያለውን ወገኖቻችንን እንዲፈታ ለመጠየቅ በ እንግሊዝና በኖርዌዬ የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን ባለፈው አርብና እሁድ በየሚኖሩባቸው አገሮች ዋና ከተሞች በሎንዶንና ኦስሎ ሰልማዊ ሰልፍ ማድረጋቸውን የግንቦት 7 ዘጋቢዎች ባስተላለፉት ዜና ገለጹ።
መለስ ዜናዊ ሽብርተኛ ነው፤ መለስ ዜናዊ ፋሽስት ነው፤ መለስ ለፍርድ ይቅረብ የታሰሩት ጋዜጦኞች በመሉ ይፈቱ ወዘተ የሚሉ መፈክሮችን ያነገቡ የሁሉቱም አገር ሰልፈኞች በኢትዮጵያ አገራችን ውስጥ በወያኔ ፋሽስታዊ አገዛዝ እየተፈጸመ ነው የሚሉትን በደሎች በመዘርዘር ለየሚኖሩባቸው አገሮች መንግሥታዊ ተቋሞችና ፓርላማ አባላት በጽሁፍ አቅርበዋል።
በኖርዌይ ሰላማዊ ሰልፉን ያስተባበሩት ኢትዮጵያዊያን ተወካይ ሰላማዊ ሰልፉ ላይ ለተገኙት አገር ወዳዶች ባደረጉት ንግግር ወያኔ ወገኖቻችን ላይ ጥቃት ባደረሰ ቁጥር ሰላማዊ ሰልፍ አዘጋጅቶ ማውገዝ ብቻውን በቂ እንዳልሆነ ገልጸው፤ ይልቁንም “የችግራችን ምንጭ የሆነውን ይህንን ዘረኛ አገዛዝ ከሥልጣን ለማስወገድ በሚደረገው ትግል ውስጥ እያንዳንዳችን ጉልህ ድርሻ መጫወት ይኖርብናል” ብለዋል። አያይዘውም “ሁላችንም በሚመስለንና አላማውና ፕሮግራሙ ከምንጋራው ድርጅት ጋር ተቀላቅለን ለነጻነታችን ለሚደረገው ትግል አስተዋጾ ማድረግ ይጠበቅብናል ፤ በትግሉ ሂዴት የወያኔ ሰለባ የሆኑ ወገኖቻችንንና ቤተሰቦቻቸውንም በገንዘብና በማቴሪያል ለመደገፍ ከጎናቸው መቆም ግዴታችን መሆን ይኖርበታል” ብለዋል።
በመጨረሻም “መለስ ዜናዊ የፊታችን ሰኞ መስከረም 29 በኦስሎ በሚያደርገው ግብኝት ነፍሰ ገዳይነቱንና ሽብርተኝነቱን በጋበዙት ምዕራባዊያን አጋሮቹ ፊት ለማጋለጥ እንድንችል ታላቅ የተቃውሞ ሰልፍ እያዘጋጀን ስለሆነ ሁላችሁም በዚያ ስልፍ ላይ በመገኘት ወገናዊነታችሁን እንድትገልጹ ጥሪ እናቀርባለን” በማለት ንግግራቸውን አጠናቀዋል። በሰልፉ ላይ የተገኙት ኢትዮጵያዊያንና የኢትዮጵያ ወዳጆችም ቀደም ሲል ያራ የተባለው የማዳበሪያ አምራች ድርጅት ለዘረኛው መለስ ዜናዊ በኦስሎ ከተማ ላይ አዘጋጅቶ በነበረው የገንዘብ ሽልማት ላይ ተገኝተው ዘረኛውን የወያኔ ቁንጮ እንዳዋረዱ ሁሉ በፈረንጆች አቆጣጠር ኦክቶበር 10 ለሚደረገው ስልፍ ተዘጋጅተው እንደሚጠብቁት በመዛት ፕሮጋራማቸውን አጠናቀዋል።
በተመሳሳይ ዜና በሎንዶን በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ የአገራችንን የነጻነት አርማ የሆነውን ባንድራችንን ሲያዋርድ የኖረው መለስ ዜናዊና ድርጅቱ ህወሃት፤ ዛሬ ድርሶ የባንድራ አፍቃሪ ለመምሰል የባንድራ ቀን እንዲከበር አዋጅ ከማውጣት አልፎ በባንድራ ቀን ከቤታችሁ ደጃፍ ባንድራ አላውለበለባችሁም በሚል ሰበብ በፖለቲካ ባላንጣነት የሚፈርጀውን ወገን በገንዘብና በእስር መቅጣት መጀመሩ እንደሚያንገበግባቸው ገልጸው፤ ተቃውሞዋቸውን ለመግለጽ ወያኔ በባንድራችን ላይ የለጠፋትን የአንባሽ ምስል በመቀስ በማውጣት በዕሳት እንዳጋዩት ለማወቅ ተችሎአል።
የሎንዶኑን ሰልፍ ያዘጋጀው የኢትዮጵያዊያን ስብስብ አስተባባሪ በዕለቱ ባደረጉት ንግግር የመለስ ዜናዊ ሽብርተኛ አገዛዝ በህዝባችን ላይ እያደረሰ ያለውን በደልና ሰቆቃ ለማስቆም ሁላችንም ጸንተን ልንታገለው እንደሚገባ ገልጸው ይህ ግፈኛ አገዛዝ ተገርስሦ በምትኩ ህዝብ ያስተዳድረኛል ብሎ የሚመርጠው የመንግሥት ሥርዓት በአገራችን እስኪገነባ ድረስ ትግሉ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ሁሉም ኢትጵያዊ የበኩሉን አስተዋጾ እንዲያደረግ ጥሪ በማቅረብና በመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ ምክንያት ጥቃት ላይ የወደቁትን ዜጎቻችንን ቤተሰቦች ለመርዳት እንደሚተባበሩ በመግለጽ ለ ዕለቱ የተጠራው ሰላማዊ ሰልፍ ተበትኖአል።
በውጪ የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን የሚያደርጉት ሰላማዊ ስልፍ በሌሎች የአውሮጳ፤ የሰሜን አሜሪካና አውስትራሊያ የተለያዩ ከተሞች በተከታታይ እንደሚደረግ እየደረሱን ያሉ መረጃዎች ያመለክታሉ።