ብርቱካን ሚደቅሳ ከነማንዴላና አንሳ ሱንኪ ምድብ ልትገባ ነዉ – ግርማ ካሳ
መስከረም 18 ቀን 2003
ሐምሌ 27 ቀን 1981 ዓ.ም ነበር። በአደባባዩ የሰፈረዉ በመቶ ሺ የሚቆጠር ሕዝብ የተለያዩ መፈክሮችን ይዞ «እምቢ አምባገነንነትን ! እምቢ የአንድ ፓርቲ ሥርዓትን! እምቢ የሰብዓዊ መብት ረገጣን » እያለ ይጮሃል። ታንኮችንና መትረየሶች የተደቀኑባቸዉ የወታደር መኪናዎችን በማሰማራት፣ የአገሪቱ 27ኛዉ ክፍለ ጦር ህዝቡን ከቧል። ታንኩ እየቀረበ መጣ። አንድ ወጣት ከታንኩ ፊት ቆመ። ታንኩ ጨፍልቆት አለፈ። ድንገትም ተኩስ ተጀመረ። መሳሪያ በታጠቁ በአገራቸዉ ሰዎች በተተኮሰ ጥይት በሺሆች የሚቆጠሩ ወደቁ። የሰዉ ልጆች ደም እንደ ጎርፍ ፈሰሰ።
በሰዉ ልጆች ታሪክ ትልቅ ጠባሳን ጥሎ ያለፈዉ ይህ አሳዛኝ ክስተት የተፈጸመዉ ቤጂንግ ቻይና በሚገኘዉ የቼይናሜን አደባባይ ሲሆን እስከ አሁን ድረስ ለዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ተጠያቂ የሆነ አንድም የቻይና ኮሚኒስት ባለሥልጣን የለም።
የቼይናሜኑ አደባባይ እልቂት፣ ለዴሞክራሲና ለሰብዓዊ መብት የሚደረገዉን ትግል ግን አላቋረጠም። ከዘመኑ የቻያና የዴሞክራሲ ታጋዮች መካከል፣ የቼይናሜን አደባባይ ጭፍጨፋ ተጠያቂ የሆኑት ለሕግ መቅረብ እንዳለባቸዉ በአደባባይና በድፍረት የሚከራከረዉ፣ የህጻን ሴት ልጅ አባት ሁ ጂያ ይገኝበታል።
ሁ ጂያ በርካታ ጊዜ በቻይና ኮሚኒስት አገዛዝ የታሰረ፣ ከፍተኛ ግፍና እንግልት የደረሰበት ሲሆን በአሁኑ ጊዜ፣ ወንጀል ሳይፈጽም፣ ለሰብአዊ መብትና ለሕግ የበላይነት እንዲሁም ለዜጎች መብት መከበር ደፍሮ መናገሩ እንደ ጥፋት ተወስዶ በእሥር ላይ ይገኛል።
ሁ ጂያ ከሁለት አመታት በፊት በ2001 ዓ.ም፣ የአዉሮፓ ሕብረት የሚሰጠዉ፣ ከኖቤል የሰላም ሽልማት ቀጥሎ ትልቅ ቦታ ያለዉ፣ የሳካራቭ ተሸላሚ ለመሆን በቅቷል።
የስድሳ ስምንት አመት አዛዉንት ሴት ናቸዉ። ከቻይና በስተ ደቡብ ምዕራብ የምትገኝ አንዲት ትንሽ አገር ተወላጅ ዜጋ ናቸዉ። በነሐሴ 1980 ዓ.ም በአገሪቱ ወታደራዊ ጁንታ ስልጣን ጨበጠ። እኝህ ሴት በመስከረም 1981 የብሄራዊ ዴሞክራሲ ሊግ የተባለ፣ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለዴሞክራሲ የሚታገል ድርጅት መሰረቱ። በሐምሌ 1981 ዓ.ም የቁም እሥረኛ ተደረጉ። ከአገር ለቀዉ የሚሄዱ ከሆነ እንደሚፈቱ ቢነገራቸዉም «በጭራሽ ሕዝቤን ትቼ አልሄድም» በሚል ከአገር ለቀዉ እንደማይሀዱ አሳወቁ።
በ1981 ዓ.ም ወታደራዊዉ ጂንታ ብሄራዊ ምርጫ ጠራ። እኝህ ሴት የቁም እሥረኛ ቢሆኑም የሚመሩት የፖለቲካ ፓርቲ ከ492 የፓርላማ መቀመጫዎች 392ቱን አሸነፈ። በምርጫ ሽንፈት ቢያጋጠመዉም ወታደራዊው ጁንታ ምርጫዉን ሰረዘ። ስልጣን እንደማይለቅም አሳወቀ። እኝህ ሴት ከእሥር ተፈተዉ ጠቅላይ ሚኒቴር ይሆናሉ ተብሎ ሲጠበቅ በእሥር ቤት እንዲቆዩ ተደረገ። ይኸዉ እስከ አሁን ድረስ እኝህ ሴት በወይኒ ቤት ይገኛሉ።
እኝህ ሴት፣ ቀደም ሲል በርማ ተብላ በምትታወቀዉ በሚያማር የዴሞርካሲና የሰብዓዊ መብት ታጋይ የሆኑት አን ሳን ሱ ኪ ናቸዉ። እንደ ቻይናዉ ሁ ጂምያ፣ አን ሳን ሱኪም በ1982 የሳካሮቭ ሽልማት ሊሰጣቸዉ ችሏል።
ሌላም የሳካራቭ ተሸካሚ ከሆኑት መካከል፣ ለ27 ዓመት በእሥር የተንገላቱት፣ ታላቁ የአፍሪካ አባት ተብለዉ የሚታወቁት፣ ኔልሰን ማንዴላም ይገኙበታል።
በቅርቡ በአዉሮፓ ሕብረት ሁለተኛ ትልቁ ብሎክ የሆነዉና ጀርመናዊዉ ስሹን ማርቲን፣ ጣሊያናዊዉ ዲ ካስትሮስ ፓዉሎ፣ እንግሊዛዊቷ ስትሊኸር ካትሪን፣ ፈረንሳዊዉ ኦንሪ ዌበር፣ ፖርቱጊዟ አና ጎሜዝ የመሳሰሉ 184 የፓርላማ አባላትን ያቀፈዉ፣ Progressive Alliance of Socialists and Democrats የተሰኘዉ ቡድን፣ እንደ አን ሳን ሱኪና ሁ ጂያም በአገራች ያለች አንዲት ታላቅ ኢትዮጵያዊትን የሳካራቭ ተሸላሚ እንድትሆን በኦፌሴል መስከረም 18 ቀን እንደሚጠቁማ በድህረ ገጹ አሳዉቋል። ይች ሴት የዴሞክራሲ ጀግና የሆነችዉ የምንወዳትና የምናከብራት እህታችንና መሪያችን ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት።
http://www.socialistgroup.org/gpes/public/detail.htm?id=134676§ion=NER&category=NEWS&startpos=0&topicid=-1&request_locale=EN
ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለዚህ ለተከበረ የሳካሮቭ ሽልማት ከመቶ አምሳ በላይ የአዉሮፓ ፓርላማ አባላት መጠቆሟ ብቻ፣ በአገራችን ኢትዮጵያ የሚደረገዉ ሰላማዊ የዴሞክራሲ ትግል ትልቅ ድልን እንዳስመዘገበ ሊቆጠር ይችላል።
በኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ እንዳየነዉ ሁሉ አሳሪዎቿ አንገታቸዉን ሲደፉ፣ ምንም እንኳን ከቃሊቲ እንድትወጣ ባይደረግም፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን በአለም አሉ ከሚባሉ ታላላቅ ተቋማት አንዱ በሆነዉ በአዉሮፓ ሕብረት፣ አጀንዳ ለመሆን በቅታለች። አቶ መለስ እርሷን አስረዉና 99.7% የፓርላማ መቀመጫዎች ዘርፈዉ አሸነፍኩ እያሉ ቢሆንም ያሸነፈችዉ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ መሆኑ ግን በገሃድ እየታየ ነዉ።
አቶ መለስ ዜናዊ በገንዘብና በጠመንጫ ኃይል ጥቂቶች ሰዎች ሊከተሏቸዉ ችለዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን ሰዉ ሳታስገድድ፣ አንዲት ሳንቲም ሳትወረዉር በአሥር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ በፍቃዳቸዉ የሚከተሏት ኢትዮጵያዊያያኖችን አፍርታለች።
አቶ መለስ ዜናዊ በሙስና የተዘፈቁ አምባገነን የአፍርካ መሪዎችን ክለብ በመወከል፣ ለልመና ሥራ፣ እንደ ጂ 7 በመሳሰሉ የአንዳንድ የአለም አቀፍ መድረኮች ላይ ስማቸዉ ሲጠራ እንሰማለን። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን እዉነት፣ ዴሞክራሲን፣ ሰላማዊ ቁርጠኝነንት፣ ኢትዮጵያዊነት በመወከሏ ስሟ እየተጠራ ነዉ።
አቶ መለስ ዜናዊ፣ በተለይም ከ547 መቀመጫዎች ዉስጥ 545ቱን አሸነፍኩ በማለታቸዉና፣ እንደነ አርከበ እቁባይ የመሳሰሉ በስራቸዉ ያስመሰከሩ ፣ እንደ አባይ ጸሐዬ ያሉ ትሁት ሰዎች እያሉ፣ ባለቤታቸዉን ወ/ሮ አዜብ መስፍን የሕወሃት ፖሊት ቢሮ አድርገዉ በመሾም፣ ሕወሃትን ከድርጅትነት ወደ ቤተሰብ ጉባዔነት እንዲሸጋገር ማድረጋቸዉ፣ በእርጅናና በጤና ምክንያት ስልጣናቸዉን ለወንድማቸዉ ለራዉል ካስትሮ ካስተላለፉት ከፊደል ካስትሮ ከመሳሰሉ ጋር ለመደመር በቅተዋል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ግን፣ በዘመናችን ታላላቅ ሰዎች ከሚባሉት ከነ ኔልሰን ማንዴላና አንሳ ሱንኪ ጋር እየተመሳሰለች ነዉ። ለሳካሮቭ ሽልማት መጠቆሟም በግልጽ የሚያሳየዉ ይሄንኑ ነዉ።
በጠራ አይምሮ ነገሮችን ለሚመለከት ማንም ኢትዮጵያዊ አቶ መለስ ዜናዊ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን በማሰራችዉ፣ አስረዉም ደግሞ አልፈታም በማለታቸዉ፣ የበለጠ እየተዋረዱ፣ እየቀለሉና እየተጠሉ እንዲመጡ አደረጋቸዉ እንጂ ምንም የጠቀማቸዉ ነገር የለም።
እንደ ዳዊት መደጋገም አይሁንብኝ እንጂ፣ አሁንም አቶ መለስ ዜናዊ ይችን ዳግማዊት ጣይቱ ብጡል ብዬ የምጠራትን ታላቅ ኢትዮጵያዊት ሴት፣ ለራሳቸዉ ሲሉ እንዲፈቱ እጠይቃለሁ። አቶ መለስ ደጋግመዉ እንደሚዋሹት ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሕሊና እሥረኛ እንጂ የፖለቲካ እሥረኛ አይደለችም።
ብርቱካን ሚደቅሳ አሁን ትፈታ !