በማዕከላዊ እስር ቤት ደበበ እሸቱን ጨምሮ 78 የሽብር ተጠርጣሪዎች ታስረው ይገኛሉ
(ሪፖርተር) — የፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ አንድነት መድረክ (መድረክ) አባል የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳና አቶ በቀለ ገርባን ጨምሮ፣ በሽብር ወንጀል የተጠረጠሩ 78 ግለሰቦች በፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ማዕከል (ማዕከላዊ) መታሰራቸውን ማረጋገጡን የኢትዮጵያ ሰብዓዊነት መብት ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ ኮሚሽኑ መስከረም 19 ቀን 2004 ዓ.ም ለሪፖርተር በላከው ጋዜጣዊ መግለጫ እንዳስታወቀው፣ መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም በዋና ኮሚሽነሩ አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የተመራው ቡድን የምርመራ ማዕከሉን በጎበኘበት ወቅት፣ ከሦስት እስከ 12 የሚደርሱ ተጠርጣሪዎች የሚያርፉባቸው 11 ጠበብ ያሉ ክፍሎችንም ጎብኝቷል፡፡
በቅርቡ በሽብር ወንጀል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉትን ተጠርጣሪዎች የጎበኘው ቡድኑ፣ ተጠርጣሪዎቹ የሚያርፉባቸው ክፍሎች ጠባብ ቢሆኑም፣ መጨናነቅ እንደማይታይና በቂ ብርሃን ማስገባት የሚችሉ መሆኑን መመልከቱንና ከተጠርጣሪዎቹም መረዳቱን አስታውቋል፡፡
ከተጠርጣሪዎቹ መካከል የመድረክ አባል የሆኑትን አቶ በቀለ ገርባና አቶ ኦልባና ሌሊሳን አነጋግሮ እንደተረዳው፣ በፍርድ ቤት መያዢያ በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን፣ በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው የጊዜ ገደብ ፍርድ ቤት መቅረባቸውንና አካላዊ ድብደባም ሆነ የማሰቃየት ተግባር እንዳልተፈጸመባቸው እንደነገሩት አስታውቋል፡፡
የቀድሞው የቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ አመራር የነበረው አርቲስት ደበበ እሸቱ ግን ቤተሰቦቹን በበቂ ሁኔታ እያገኘ እንዳልሆነ መግለጹን ቡድኑ አልደበቀም፡፡
ተጠርጣሪዎቹ የተፋጠነ ፍትሕ እያገኙ እንዳልሆነ ከመግለጻቸውም በተጨማሪ፣ ኮሚሽኑም መሻሻል እንዳለበት መገንዘቡን የኮሙዩኒኬሽን ኢንፎርሜሽን ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተሩ አቶ ብርሃኑ አባዲ ገልጸዋል፡፡
የምርመራው ሒደት መጓተት እንደሚታይበትና መሻሻል እንዳለበት ኮሚሽኑ ገልጾ፣ ከምርመራ ክፍሉ ኃላፊ ኮማንደር ረታ ተስፋዬ ጋር በተደረገው ውይይት አርቲስት ደበበ ያነሳው ቅሬታም ሆነ ሁሉም ነገር እንደሚሻሻል ቃል መገባቱን አቶ ብርሃኑ ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር አምባሳደር ጥሩነህ ዜና የተመራው ቡድን ጉብኝት ሲያደርግ ለምን ጋዜጠኞችን መጋበዝ እንዳልፈለገ አቶ ብርሃኑ ተጠይቀው፣ ‹‹ጋዜጠኛ ይዞ መሄዱ ጥቅም የለውም አይባልም፡፡ የኮሚሽኑ ዓላማ ግን ጉብኝት አድርጎ ለየሚዲያዎቹ ጋዜጣዊ መግለጫ መስጠት በመሆኑ አላስፈለገውም ነበር፤›› በማለት ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
በዕለቱ በተደረገው ጉብኝት ያለፖሊስ ጥበቃ በነፃነት የመጎብኘትና ተጠርጣሪዎችን ማነጋገር መቻሉን፣ ተጠርጣሪዎቹ አጋጠመን ያሉትንና እየተደረገላቸው ያለውን ነገር ሁሉ በግልጽነት ለቡድኑ መንገራቸውን አቶ ብርሃኑ አክለዋል፡፡