አዉራምባ አይምስ እትም 187 ርእሰ አንቀጽ – ደግመን ደጋግመን ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!›› እንላለን።

«መንግስት በምንም አይነት መልኩ ሊተች አይገባም» የሚል አላማን ለማራመድ ሲባል ብቻ የግል ኤፍ.ኤም ሬዲዮ የተሰጣቸው አንዳንድ ኢትዮ-አሜሪካዊያን፤ ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በአውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ላይ መያዣ መጨበጫ የሌለው የመንደር ፕሮፓጋንዳ በመንዛት የተጠመዱበት ሰሞን ነው።

የጣቢያው ባለቤቶችና አዘጋጆች ነን ባዮቹ ጥንዶች ‹‹የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ›› በሚሉትና አንድም ጋዜጠኛ በማይገኝበት ፕሮግራማቸው፣ ይህቺኑ አውራምባ ታይምስ ጋዜጣን ዋነኛ የመነጋገሪያ አጀንዳቸው አድርገው ጭራና ቀንድ የሌለው አሳፋሪ ፕሮፓጋንዳቸውን ቢያናፍሱ ለዘመናት የተካኑበት ነውና ብዙም አያስገርመንም።

ማንምእንደሚያውቀው የዛሚ 90.7 ሬዲዮ ጣቢያ ባለድርሻዎች፣ የተጠቃሹ ፕሮግራም አዘጋጆች እና አጋሮቻቸው የረዥም ዘመን የመገናኛ ብዙኃን ሥራ ልምድ አለን የሚሉ ናቸው።

ይህም ብቻ አይደለም፤ የፖለቲካ ሳይንስ ዕውቀት አለን፤ የዩኒቨርስቲ መምህራንም ተንታኞችም ነበረን የሚሉ መሆናቸው የአደባባይ ምስጢር ነው። እንደው በጥቅሉ «ሁሉን እናውቃለን» ባይ ናቸው። እነዚህ «ሁሉን አዋቂ» ሰዎች «የጋዜጠኞች ክብ ጠረጴዛ» ብለው በሰየሙት ፕሮግራማቸው ጋዜጣችንን ዋነኛ መነጋገሪያ በማድረግ «ላም ባልዋለበት ኩበት ለቀማ» መውጣታቸውና አጓጉል ሲደክሙ መሰንበታቸው እንድናዝንባቸው ሳይሆን፣ እንድናዝላቸው እያደረገን እንደሆነ ግን ሳንጠቅስ አናልፍም።

የምናዝንላቸው ካለ ምክንያት አይደለም። አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ እንደሁልጊዜው አቋማን በምትገልፅበት ርዕስ አንቀጽ መደመደሚያ «ኢትዮጵያ ለዘላለዓለም ትኑር» ማለቷን ሲያንኳስሱና ሲያጣጥሉ በመደመጣቸው ነው፡

ለመሆኑ «ለዚህች አገር ሰላምና መረጋጋት ጠንቅ የሆኑ ጉዳዮችን እናወግዛለን፤ አመጽን እንታገላለን… ወዘተ» የሚሉ ሰዎች ይህ መፈክር እንቅልፍ የሚነሳቸው ለምን ይሆን፤ የሌላ አገር ዜግነት ቢደርቡም አገራቸውን እጅግ የሚወዱ አያሌ ኢትዮ-አሜሪካዊያንን እኮ እናውቃለን፡፡ በዚህ ደረጃ ስር የሰደደ ጥላቻ ለማን ነው የሚጠቅመው፡፡ «ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር» የሚለውን የጋዜጣችንን ፅኑ ዕምነትና መልካም ምኞት ለማጣጣል «አዶልፍ ሂትለርም – ጀርመን ለዘለዓለም ትኑር ይል ነበር!» ብሎ መሳለቅ፤ለምትበዘብዟት አገር ያላችሁን ስር የሰደደ ጥላቻን ለማንጸባረቅ ካልሆነ ሌላ ምን ይባላል?

ለመሆኑ ይህች አገር ምን በደለቻችሁ? አውራምባ ጋዜጣ ከእነዚህ «ሁሉን አዋቂ ነን» ባዮች «ሁሉን አቀፍ ቅዥት» ጋር የምትባትት አይደለችም። እንዲህ አይነቱ ሁሉን አቀፍ ፕሮፓጋንዳዊ ቅዥት የሕመም እንጂ የጤንነት ነው ብላም አታምንም። ስለዚህም ለፕሮግራሙ አዘጋጆች ታዝንላቸዋለች። መልካም ጤንነትንም ትመኝላቸዋለች፡፡ መልካም ጤንነትን መመኘት የኢትዮጵያውያን ድንቅ መገለጫ ነውና።

እንደእውነቱ ከሆነ መልካም ምኞት መመኘት በራሱ ክፋት የለውም። ሊኖረውም አይችልም። ምኞትን በፀያፍ ተግባር ዕውን ማድረግ ነው ወንጀል የሚሆነው። ሂትለር «መልካም ምኞቱን» ለማሳካት ሲል በሰው ልጆች ላይ ፀያፍ ጭፍጨፋ መፈፀሙ ነው ወንጀለኛ ያሰኘው። ያንን ግፈኛ ተግባር የፈፀመው ደግሞ በሥልጣኑ ተመክቶ፣ በታጠቀው ብረት (ጠብ-መንጃ) ኃይል ልቡ ደንድኖ ነው።

እኛ ደግሞ እኛ ነን። አንደኛ፣ ኢትዮጵያዊ ነን። ከጀርመናውያን እንለያለን። በኢትዮጵያዊ ዕምነት፣ መልካም ባህልና ጨዋ አስተዳደግ ወዘተ በግብረ ገብነት ተቀርፀን የታነፅን፣ በእኛ ላይ እንዲደርስ የማንሻው፣ በሌላውም ሰው ላይ እንዳይፈፀም የምንፈልግ ነን። ኢትዮጵያዊነታችን በራሱ ክፋትን፣ ግፍን፣ በደልን፣ ፀብን ወዘተ ሁሉ ይፀየፋል። ከዚህ ውጭ እኛ ሥልጣንም ኃይልም የለንም፤ አንሻምም። ምክንያቱም ማንም የመንግስትን ስልጣን ይያዝ ለህዝብ በሚጠቅም መልኩ መንግስታዊ ኃላፊነቱን እንዲወጣ በሙያችን መጠየቅ ነው፡፡ የታጠቅነው ብዕር ነው።

በብዕራችን የመዳንን ስብከት ነው የምንሰብከው። የዕድገትን፣ የብርታትን፣ የጥንካሬና የፍቅርን ሀያልነት ወዘተ ነው የምንሰብከው። ስለዚህ ከእነ እንቶኔ ጋር በፍፁም አንመሳሰልን። በፍፁም!! የማይገናኝ ነገርን በማገናኘት የሚለካ ዕውቀት ከየት እንደመነጨ አይገባንም። ዕውቀት ማለት ‹‹ጥላቻ›› ከሆነ፣ እንደዚያ ዓይነቱ ዕውቀት ገደል ይግባ ባይ ነን።

አውራምባ ታይምስ ጋዜጣ ዝግጅት ክፍል ለእንዲህ አይነቱ ቅጥ አምባሩ ለጠፋበት ዕውቀት ቦታ የላትም። የእነ ሂትለር የጭፍጨፋ ተረት ያለቦታው የተጠቀሰ ነውና፤ በመሰረቱ አውራምባ ታይምስ ዘመን ላለፈበት የመጠላለፍ ፖለቲካ፤ ለእከክልኝ ልከክልህ ከንቱ ጨዋታ የምትባዝንም አይደለችም። የጋዜጣዋም ባልደረቦች በሙሉ የአዲሱ ትውልድ ተምሳሌቶች ናቸው። የተስፋ ቀንበጦች ናቸው። የመልካምነትና የቅንነት ውጤቶች ናቸው።

አዲሱ ትውልድ ከመገዳደል፣ ከመጠላለፍ እና ከእርስ በእርስ ሽኩቻ ፖለቲካ መውጣት እንደሚሻ የሚሰብኩ ናቸው። ኃ ላ ፊ ነ ት የሚሰማቸው፤ለልጆቻቸውና ልጅ ልጆቻቸው የሚጨነቁ ናቸውና «እቴሜቴ፣… ምን አለሽ ማታ»ን የሚሰብኩ አይደሉም። ክፋትንና ጥፋትን ሲዶልቱ ጀምበር የሚጠልቅባቸው አይደሉም። በነፈሰበት የሚነፍሱ፣ በበሉበት የሚያጨበጭቡ፣ የባለሥልጣን ፊት እያዩ ያልሆነውን ሆነ በማለት «እከሌ ካልታሰረ» ብለው የሚተጉ አይደሉም፡፡ ንጋት የሚታያቸው፣ መልካም ብስራት የሚሰማቸው፣ በኢትዮጵያዊነታቸው ፍፁም እምነት ያላቸው፣ እውነትንና የእውነትን መንገድ የሚከተሉ ናቸው። የኢትዮጵያን ዕድገት የሚመኙ፣ በኢትዮጵያ ፍቅር እንዲሰፍን የሚሹ፣ የኢትዮጵያ ዕድገትንና ብርታት፣ የእነሱም ዕድገትና ብርታት መሆኑን የሚያምኑ ዜግነቷ የማያሳፍራቸው ባለ ራዕዮች ናቸው። ራዕይ ያለው ደግሞ ክፋትን ለማንም አይመኝም። አውራምባ ታይምስ ጋዜጣም ባለራዕይ መሆኗን የምንናገረው በፍፁም እምነት ነው። ስለዚህ አሁንም ደግመን ደጋግመን ለኢትዮጵያ ሀገራችን መልካሙን
ሁሉ እንመኛለን። አሁንም ደግመን ደጋግመን ‹‹ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!›› እንላለን።

የአዉራምባ አራተኛ አመት እትም 187 እትም ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ