አዉራምባ ታይምስ – «አሁን የያዝነው ጉዞ እስከ ቀራኒዩ አደባባይ ድረስ ነዉ» አቶ ዳዊት አስራደ የአንድነት አፕርቲ ዋና ጸሃፊ
በቅርቡ መንግስት ከሽብርተኝነት ጋር በተያያዘ የተጠረጠሩ ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኞችን ማሰሩ ይታወሳል። ከእነዚህም እስረኞች መካከል የአንድነት ፓርቲ አመራር አባላት ይገኙበታል። በእነዚህ ጉዳዮች ዙሪያ፣ ከፓርቲው ዋና ጸሐፊ አቶ ዳዊት አስራደ ጋር ባልደረባችን ኤልያስ ገብሩ አጠር ያለ ቃለ-ምልልስ አድርጓል።
የፓርቲያችሁን ሊቀ-መንበር እና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አንዷለም አራጌን ጨምሮ ፣ የብሔራዊ ምክር ቤት አባሎቻችሁ ከታሰሩ በኋላ ያላችሁ የሥራ እንቅስቃሴ ምን ይመስላል?
የጠቀስካቸው የፓርቲያችን አመራርና አባሎቻችን እንደታሰሩና ከታሰሩ በኋላ የታሰሩበት ሁኔታ አግባብ እንዳልሆነ መስከረም 5/2004 ዓ.ም በሰጠነው ጋዜጣዊ መግለጫ ሰፊ ማብራሪያ ሰጥተናል። ያንን ተከትሎ ያለውን ሁኔታ የሚከታተል አንድ ግብረ-ኃይል አቋቁመናል። ግብረ-ኃይሉ፣ በሰብዓዊ መብቶችና በሕግ ሁኔታ፤ በማኅበራዊ፣ በሕዝብ ግንኙነትና በዲፕሎማሲያዊ ዘርፎች ተከፋፍሎ ክትትል ያደርጋል።
ግብረ-ኃይሉ በዋነኝነት ስለታሰሩት የፓርቲያችን አባላት ሁኔታ፤ ስለታሰሩ ጋዜጠኞች፤ ስለታሰሩ ሌሎች የፖለቲካ ድርጅቶች ባላት እና ፖለቲከኞች፤ እንዲሁም የኪነ-ጥበብ ባለሙያዎችንም ጭምር የሚመለከት ነው። በአጠቃላይ፣ እየተደረገ ያለውን እንቅስቃሴ በሀገራችን ባለው የሰላማዊ ትግል ላይ የተነሳ ዘመቻና የፖለቲካ ጉዳይ አድርገን ወስደነዋል፡፡ በጋዜጠኞች ላይ እየተወሰደ ያለው እርምጃም ከዚሁ ጋር ነው የምናያይዘው። መንግሥት ኅብረተሰቡ የፖለቲካ ግንዛቤውን እንዳያሳድግ፣ መብቶቹን እንዳያውቅና ብሎም ጥያቄዎችን እንዳይጠይቅ አፍኖና ዘግቶ እሱ የሚለውን መረጃ ብቻ ደጋግሞ በማውራት ኅብረተሰቡን የፖለቲካ ፕሮፖጋንዳ ሰለባ እንዲሁም፣ ሕዝቡ መሰረታዊ ለውጥ እንዳያመጣ፣ መብቱን እንዳይጠይቅ፣ የዳቦ ጥያቄ እንዳያነሳ፣‹‹እሺ … እሺ›› ብቻ የሚል እንዲሆን እና ‹‹አሜን…አሜን›› የሚል ትውልድ ለመፍጠር የሚያስችል አይነት ሰንሰለት እየሰራ ይገኛል። እነዚያ የታሰሩ ጋዜጠኞች ደግሞ ጠንካራ ብዕር ያላቸው፣ ሰብዓዊ ክብርን የሚሰብኩና የጋዜጠኝነት የሙያ ክብራቸውን ጠብቀው ለሙያው ሥነ-ምግባር ተገዝተው የሚንቀሳቀሱ ጋዜጠኞች እንደሆኑ አውቃለሁ።
እነዚህ ጋዜጠኞች ሁልጊዜም ቢሆን ለአምባገነኖች ስጋት ናቸው። ስለዚህ አምባገነኖች የአምባገነናዊ አስተዳደራቸውን ዕድሜ ለማራዘም ሲሉ እንደዚህ አይነት ጋዜጠኞችን እያፈኑ ያስራሉ፡፡ … ኪነ-ጥበብም የኅብረተሰብን ንቃት-ህሊና የሚያሰፋና የሚያሳድግ ታላቅ መሳሪያ ነው፡፡ ነገር ግን፣ አሁን እየተደረገ ያለው ንቃተ-ህሊናው ዝቅተኛ የሆነ፣ እንደፈለጉ የሚጫወቱበትና የሚቀልዱበት ሕዝብ ለመፍጠር የሚቻልበት ሁኔታ በመሆኑ፣ ኪነ-ጥበብን ለመቆጣጠር፣ ለማጥፋትና ለማቀጨጭ የተያዘ ዘመቻ ይመስላል። በተጨማሪም፣ ብሔራዊ ፍቅር እና ማንነትን የሚገልፁ ጥበቦች እንዲወጡ ያለ ማድረግ ነገር ይታያል። በተለይም የአርቲስት ደበበ እሸቱን እስር ከእዚህ ጋር ነው የማያይዘው። በመሆኑም አሁን አንድነት እያደረገ ባለው እንቅስቃሴ የታሰሩ አባላቱን ሁኔታ ብቻ ይዞ የሚቀጥል አይደለም፡፡ የተቋቋመው ግብረ-ኃይል በአጠቃላይ በኢትዮጵያ ያሉ የፖለቲካ እና የህሊና እስረኞችን ሁኔታ የሚከታተል ነው።
ይህ ያቋቋማችሁት ግብረ-ኃይል እንቅስቃሴ ጀምሯል?
እነአቶ አንዷለም ከታሰሩ በኋላ በሁለተኛው ቀን አስቸኳይ ስብሰባ ተጠርቶ ‹‹ምን ይደረግ?›› በሚለው ነገር ላይ ውይይት ተደርጎ ነበር። መደረግ የሚገባቸውን ነገሮች ስናስቀምጥ፣ አንደኛ በድርጅቱ የተጀመሩ እንቅስቃሴዎች ባሉበት ሁኔታና ይበልጥ በተጠናከረ መልኩ እንዲቀጥሉ የሚያስችሉ እርምጃዎችን መውሰድ ነው። አቶ አንዷለም ከፓርቲው ም/ሊቀመንበርነታቸው ባሻገር የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ እንደመሆናቸው መጠን በተፈጠረው ሁኔታ ክፍተት እንዳይፈጠር ታስቦ በቦታው ተጠባባቂ ኃላፊን መሰየም አስፈልጎ ነበር። በመሆኑም በአጠቃላይ በተቃዋሚዎች ጎራ ብቸኛው የፓርላማ ወኪል የሆኑትን አቶ ግርማ ሰይፉን ቦታው ላይ በተጠባባቂነት ሰይመናል። የሥራ ክፍሎቻችን ሙሉ በመሆናቸው በተጠናከረ መልኩ እየሰራን ነው። የፓርቲያችን ልሳን የሆነችው ‹‹ፍኖተ ነፃነት›› ጋዜጣ ቀጥላ እየወጣች ትገኛለች። ከዚህም በተጨማሪ በተለያዩ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ጥናታዊ ጽሑፎች የሚቀርቡበት ሳምንታዊ ፕሮግራሞች አሉን። አሁንም ቀጥለንበታል። በነገው ዕለትም በዶ/ር አክሎግ ቢራራ አማካኝነት በኢትዮጵያ ሁኔታ ላይ የሚያጠነጥን የውይይት መድረክ አዘጋጅተናል።በተከታታይም እንደዚሁ የምንቀጥልበት ነው የሚሆነው።
እዚህ ላይ ላቋርጥህና፤ በአዲስ ዘመን ጋዜጣ ገፅ ሶስት ላይ በተለይ ጋዜጠኛ አስክንድር ነጋ እናንተ ባዘጋጃችሁት ፕሮግራም ላይ፣ ‹‹ትግሉ ወደ ሰላማዊ ተግባር ይሸጋገር›› በሚል ርዕስ ያቀረበውጥናታዊ ጽሑፍ በስፋት ተተችቷል። ይህ በቀጣይ በፕሮግራማችሁ ላይ የጥናት ስራዎቻቸውን በሚያቀርቡ ሰዎች ላይ ተጽዕኖ ይኖረው ይሆን?
እንግዲህ … በመጀመሪያ ደረጃ አንድነት ቆርጦ እየታገለ ያለው ፍርሃትን ነው። ፈርተን እንቅስቃሴያችንን አናቆምም። ጋዜጠኛ እስክንድር ብቻ አይደለም የታሰረው፡፡ አቶ አንዷለምም ጭምር ነው። ‹‹አቶ አንዷለምም ሆነ እስክንድር ለምን ታሰሩ?›› ለሚለው ጥያቄ እኛ የራሳችን የሆነ ትንታኔ እናቀርባለን። ይኼ ከላይ በገለፅኩልህ ጥቅል ማዕቀፍ ውስጥ የተደረገ ነገር ነው። ሁለቱም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ በጣም ተፅዕኖ ፈጣሪ ሆነው እየመጡ ያሉ ግለሰቦች ናቸው። ተሰሚነትና ተደማጭነትም አላቸው። የኅብረተሰቡን ጥቂት የመረጃ ተደራሽነት ማሳደግ ችለዋል። ስለዚህ እርምጃው የመረጃ ተደራሽነትን ለማቀጨጭ ልክ በጋዜጠኞች ላይ እንደሚደረገው አይነት እንደሆነ እናምናለን። የመረጃ ተደራሽነትን ለማቀጨጭ የተያዘውን ዘመቻ አለማቆም ግን ይኼ ሥርዓት ለሚያደርገው ጠንካራ የአፈና መዋቅር ተባባሪ እንደመሆን ነው። …
በመሆኑም በፍርሃት ምክንያት የምናቆመው እንቅስቃሴ አይኖርም። ከዚህ በፊት የነበሩ እንቅስቃሴዎችንና ትግሉን የበለጠ አጠናክረን እንቅጥላለን። እነሱ ሊያስሩ ይችላሉ። ሆኖም በአንድነት በኩል ሁሉም አመራሮችና አባላት ስለእውነትና ነፃነት ለመታሰር ዝግጁ ነን። በባለፈው ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ እንደገለፅኩት፣ አሁን የያዝነው ጉዞ እስከ ቀራኒዩ አደባባይ ድረስ ሊባል የሚችል ነው። አባጣና ጎርባጣውን ሳትራመድ ድል የሚባል ነገር ሊኖር አይችልም፡፡ የሚከፈሉ ዋጋዎች አሉ። እነዚያን ለመክፈል ዝግጁ ነን። ያ ዋጋ ሲከፈል ነው ነፃነት የሚባለው ነገር የሚመጣው። ያ ዋጋ ሲከፈል ነው፣ ፍርሃትን መቆጣጠር የምንችለው። ስለዚህ የእስር ጉዳዩን ፍርሃት ላይ የተከፈተ ዘመቻ አድርገን ልንወስደው እንችላለን። ምክንያቱም፣ ከአምባገነኑ ሥርዓት ባልተናነሰ መልኩ ትልቁን ችግር እየፈጠረ የሚገኘው የኢትዮጵያን ሕዝብ ሽባ እያደረገውና እንቅስቃሴውን ቋጥሮ የያዘው የፍርሃት ቆፈን ነው። ይሄ የፍርሃት ቆፈን እንዲለቅ መደረግ ያለበትን ዋጋ ሁሉ ለመክፈል ዝግጁ ነን።
ባሳለፍነው ሳምንት ማክሰኞ ዕለት ፓርቲያችሁ ‹‹የታሰሩ አባሎቻችንና ዜጎች ሕገመንግስታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው›› በሚል በአካል በመሄድ ለፕሬዝዳንቱ እና ለጠ/ሚኒስትሩ ጽ/ቤት የጻፋችሁትን ግልፅ ደብዳቤ የሚቀበላችሁ ማጣታችሁ ይታወቃል። ደብዳቤያችሁን በምን መልኩ ልታደርሱ አስባችኋል?
እንግዲህ … ጠ/ሚኒስትሩ ደብዳቤውን ቢቀበሉም ባይቀበሉም እንዳነበቡት ግን ተስፋ እናደርጋለን። አንብበውታል የሚል እምነትም አለኝ፡፡ ቢሆንም
እኛ ዲፕሎማቲክ ስራ መስራትና መከባበር ላይ የተመሰረተ ፖለቲካ በሀገራችን እንዲሰፍንእንፈልጋለን። ስለዚህ ግልፅ ደብዳቤ በመሆኑ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ለመንግስታቸው ክብር ብለን ከትናንት በስትያ በፖስታ አድራሻቸው በአደራና በአስቸኳይ በቀጥታ እንዲላክ አድርገናል።
ግን ይኼንን ደብዳቤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉም ሆኑ የሌሉ ኢትዮጵያውያን በዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እኩል እንዲያነቡት አድርገናል። ዜጎች የሀገራቸውን ሁኔታ ይከታተላሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ። እስከ አሁን ድረስ ግን ምላሽ አላገኘንም።
የታሰሩትን ሰዎች ለመጠየቅ ችላችኋል?
በወቅታዊ ሁኔታ የታሰሩትን ፖለቲከኞች እና ጋዜጠኛ እስክንድርን ለመጠየቅ አልተቻለም። ስለዚህ ጉዳይ ለማናገር እንኳን ዝግጁ የሆነ አካል
የለም። ‹‹ተጠርጣሪዎቹ ፍርድ ቤት የተቀጠሩበትን ቀን፣ ማለትም ጥቅምት 2/2004 ዓ.ም ጠብቁ›› የሚል ምላሽ ተሰጥቷል። እንግዲህ ግለሰቦቹን
ቤተሰቦቻቸው፣ ሕፃናት ልጆቻቸው፣ የኃይማኖት አባቶቻቸው እና የሕግ አማካሪዎቻቸው እንኳን ሊጎበኟቸው አልቻሉም። በነገራችን ላይ ብዙዎቹ እንደአጋጣሚ ሆኖ ሕፃናት ልጆች ያሏቸው ናቸው። የመጠየቅ መብታቸውም መከበር አልተቻለም። እንዲያውም፣ ድንግርግር ያሉ ነገሮች ያሉ ይመስላል። አቅርበነው የነበረው የሕግ አማካሪያችን “መሄድ አልችልም” በሚል እንቅስቃሴ ማቆሙን አሳውቆናል። ይሄ የሚያሳው ሥርዓቱ ሰዎች የሕግ ከለላ እንዲያገኙ፣ የሚያቆሟቸውን ጠበቃዎቻቸውን
እንኳን በማስፈራራት ከሥራቸው እንዲሸሹ የማድረግ ሥራ እየተሰራ መሆኑን ነው። ያም ሆኖ ግን እኛ በፓርቲው ስም የእነዚህን ሰዎች ጉዳይ የሚከታተል
ጠበቃ ለመቅጠር እየተንቀሳቀስን ነው።
ጠበቃው ፈርቶ አቁሟል እያልከኝ ነው?
አዎን። . . . በአጭሩ እስረኞቹ የመጠየቅ መብት በሁሉም መልኩ አልተከበረም። በነገራችን ላይ ይሄ ነገር ሕገመንግስታዊ ጥሰትን የሚያሳይ ነው። ዋና ዋና 31 የሕገመንግሥቱ አንቀጾች፣ አቶ እንዷለም አራጌ ከተያዙበት ጊዜ አንስቶ የተጣሱበት ሁኔታ ነው ያለው። ከእነዚህ ውስጥ መሰረታዊ የሆኑት የሕገመንግሥት ጥሰቶች እና የማን አለብኝነት ለጠቅላይ ሚኒስትሩ በፃፍነው ግልፅ ደብዳቤ ላይ አካትተናል። ከእነዚህ አንፃር ሌሎች ክብደት የሌላቸውን ግን በደብዳቤው አላካተትንም።
በመጨረሻ ማለት የሚፈልጉት . . . ?
… ይሄ ትግል የኢትዮጵያውያን ትግል ነው። ይሄ ትግል የአንድነት ፓርቲ ትግል ብቻ አይደለም። በመሆኑም የኢትዮጵያ ሕዝብ ሰብዓዊ ክብሩን፣ ሕገመንግስታዊ መብቶቹንና ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ራሱን አጠናክሮ እና ተደራጅቶ ከጎናችን እንዲቆም ጥሪ አስተላልፋለሁ።