ፍኖት – የአገዛዙ ኢፍትሃዊ በትር ያረፈባቸዉ አቶ ስለሺ ሐጎስ ማን ናቸዉ ?

ስለሺ ሐጎስ የተወለደው መቂ ከተማ በ1972 ዓ.ም ነው፡፡ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ በዚያው በመቂ ከተማ በካቶሊክ ት/ቤት ተምሯል፡፡ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርቱን ያጠናቀቀው በዝዋይ ከተማ ነው፡፡

ስለሺ ሐጎስ በኮተቤ መምህራን ኮሌጅ በመግባት በሥነ ጽሑፍ በዲፕሎማ ተመርቋል፡፡ እንዲሁም በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ በመግባት በቴአትር ጥበብ የመጀመሪያ ዲግሪውን አግኝቷል፡፡

ስለሺ ሐጎስ በሰላማዊ መንገድ ለውጥ ለማምጣት ከሚጥሩ ወጣቶች አንዱ ነው፡፡ በሚያቀርባቸው ግጥሞች ካነባበብ ስልቱ ጋር ተዳምረው ቀልብን የመሳብ ተሰጥኦ ነበረው፡፡

ስለሺ ሐጎስ በቴአትር ጥበባት ዲግሪውን ያግኝ እንጂ የሥነ ጽሑፍ ትኩሳት ስለነበረው “ቼንጅ” ወይንም ለውጥ የሚል መጽሔት ማሣተም ጀምሮ ነበር፡፡ በሁኔታዎች አስገዳጅነት ግን ርቆ ሊራመድ አልቻለም፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ መሥረዳድር የኤፍ ኤም 96.3 የሬዲዮ ፕሮግራም ላይ የአየር ሰዓት በመውሰድ የመዝናኛ ፕሮግራም ያዘጋጅ ነበር፡፡ በዚህም በርካታ ደንበኞችን ለማፍራት ችሏል፡፡

ስለሺ ሐጎስ በምን ምክንያት በቁጥጥር ሥር እንደዋለ የቅርብ ጓደኛው የሆነውን ወጣት ሀብተማርያምን አግኝተን ስለ ሁኔታው ጠይቀነው ነበር፡፡ “እኔ ጓደኛየን የማውቀው በቁምነገረኛነቱ ነው፡፡ ካልሆነ ቦታ ይገኛል የሚል እምነት የለኝም፡፡ ለጊዜውም በምን ምክንያት በቁጥጥር ስር እንደዋለ አላውቅም፡፡ በመንግሥት በኩል እስካሁንም በሽብር ተጠርጥሮ የሚል መግለጫ አልሰማሁም፡፡ ያላንዳች ምክንያት ተይዞ መታሰሩ ግን አሳዝኖኛል” ብሏል፡፡ ሌላው ጓደኛው ወርቅነህ የተባለው “የስለሺ መታሰር ገርሞኛል፡፡ ጓደኛዬን የማውቀው በቁምነገረኛነቱና በሰላማዊ መንገድ ለውጥ እንዲመጣ መፈለጉን እንጂ ከዚህ ውጭ ሌላ ፀባይና ክፋት አላውቅበትም ” ሲል በመታሰሩ ማዘኑን ገልፃልናል፡፡

እንግዲህ ርእዮት ዓለሙና ስለሺ ሐጎስ እነማን እንደ ሆነ ላንባቢያንና ለሚታገሉለት ሕዝብ በመጠኑ ለመፈንጠቅ ሞክረናል፡፡

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።

የፍኖት እትም ዘጠን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ