ፍኖት- የአንድነት ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተል ግብር ኃይል መቋቋሙ ተገለፀ

– እስካሁን እስረኞች ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አልቻልንም (አንድነት ፓርቲ)
– ቤተሰብ፣ የትግል አጋሮቻቸውና የህግ አማካሪ እንዲያገኛቸው ተከልክለዋል (ቤተሰብ)
– የእስር አያያዛቸው አሳስቦናል

በእስር ላይ የሚገኙት የአንድነት ፓርቲው ም/ሊቀመንበርና የህዝብ ግንኙነት ኃላፊው አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የብሔራዊ ም/ቤቱ አባላት የሆኑት መ/ር ናትናኤል መኮንንና መ/ር አሳምነው ብርሃኑ እንዲሁም ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና ጋዜጠኛ ስለሺ ሀጐስ የመኢዴፓ ዋና ፀሐፊ አቶ ዘመኑ ሞላ ከታሰሩ በኋላ ቤተሰብ፣ የትግል አጋሮቻቸውን የሕግ አማካሪዎቻቸው ለማግኘት ሞክረው በመከልከላቸው የእስር አያያዛቸው አሳስበናል ሲል የፓርቲው ጽ/ቤት ለዝግጅት ክፍላችን ገለፀ፡፡ ጉዳዩን የሚከታተል በፓርቲው ሊቀመንበር በዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ የሚመራ አራት ኮሚቴዎችን ያቀፈ የእስረኞችን ጉዳይ የሚከታተል አንድ ግብረ ኃይል መቋቋሙን ከህዝብ ግንኙነት ክፍል አስታውቀዋል፡፡

ከፓርቲው ህዝብ ግንኙነት ክፍል በደረሰን መረጃ መሠረት በእ/ር ግዛቸው ሽፈራው የሚመራ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ኮሚቴ፣ በተከበሩ አቶ ግርማ ሴይፉ የሚመራ የህዝብ ግንኙነት ጉዳዮች ኮሚቴ፣ በወ/ሮ ላቀች ደገፉ የሚመራ የማህበራዊ ጉዳዮች ኮሚቴ በአቶ ሽመልስ ሀብቴ የሚመራ የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ኮሚቴ ተቋቁሞ ኃላፊነትና ተግባሩን በዝርዝር ከተገለፀለት በኋላ ሥራቸውን እያከናወኑ ናቸው ተብሎአል፡፡ ስለ ጉዳዩ አጠቃላይ ሁኔታ እንዲያብራሩልን የጠየቅናቸው ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ እንደገለጹልን “እስረኞች ከታሠሩበት ጊዜ ጀምሮ ማንም ሰው እንደገለጹልን “እስረኞች ከታሠሩበት ጊዜ ጀምሮ ማንም ሰው እንዳያገኛቸው በመደረጉ የእስረኞቹ አያያዝ አሳስበናል፡፡ ህገመንግስታዊ መብታቸውን ለማስከበር ጉዳዩን የሚከታተል አንድ ግብረ ኃይል አቋቁመን እየተንቀሳቀስን ነው፡፡ እስረኞቹ ተጠርጥረው በተሰሩበት ፍ/ቤት ቀርበው ተመስክሮባቸው ሳይረጋገጥ የመንግስት ሚዲያዎችና ከመንግስት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ያላቸው አንዳንድ ሚዲያዎች ወንጀለኛ እንደሆኑ አስመስለው የፕሮፓጋንዳ ሥራ እየተከናወነባቸው ነው፡፡ ይህ በአስቸኳይ መቆም አለበት፡፡ የአገሪቱ ህገ መንግስት አንቀጽ 19 ስለ እስረኞች አያያዝ የሚደነግገው አንቀጽ እየተጣሰ ነው” ብለዋል፡፡

በመቀጠልም ዶ/ር ነጋሶ ሲናገሩ “እስከ አሁን ድረስ ከእስረኛ ቤተሰቦች ባለኝ መረጃ መሠረት ስንቅ ከማቀበልና ዕቃ ከመቀበል ውጪ እስረኞቹ ያሉበትን ሁኔታ ማወቅ አለመቻላቸውን ገልጸውልኛል፡፡ በውጪ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንና የድጋፍ ሰጪ ፓብተሮቻችን ጉዳዩን በንቃት ከመከታተላቸውም በላይ ከፍተኛ እንቅስቃሴ እያደረጉ ናቸው፡፡ አንዳንድ ኢንባሲዎችም ስለ ጉዳዩ ከጠየቁን በኋላ ጠ/ሚኒስትሩን እንደሚያነጋግሯቸው ገልፀውልናል፡፡ የፍርድ ሂደቱንም በቅርብ እንደሚከታተሉት ለየመንግስታቸውም ያለውን ሁኔታ እንደሚያስታውቁ አረጋግጠውናል፡፡ አምንስቲ ኢንተርናሽናል ሂውማን ራይትዎች በአገሪቱ ውስጥ እየተፈፀመ ያለውን ሁኔታ ጠይቀውን አስረድቼአቸዋለሁ፡፡ የሽብርተኝነት ህጉን በመጠቀም ህጋዊና ሠላማዊ ታጋዮችንና ጋዜጠኞችን የማፈን ሥራ እየተከናወነ ነው፡፡ ፀረ -ሽብር ህግ ህገመንግሥቱን የሚቃረን ስለሆነ አዋጁ ውድቅ መደረግ አለበት፡፡ ህዝብ ብሶቱን በነፃነት የሚገልጽበት ሁኔታ መፈጠር ይኖርበታል ፓርቲው በዚህ በተጀመረው የእስር ዘመቻ ላይ አባላቱን በየደረጃው ለማወያየት እቅድ ይዟል፡፡ በመቀጠልም ህዝባዊ ስብሰባዎችን ለማከናወን እያስብን ነው፡፡ የአገራችንን ወቅታዊ የፖለቲካ ሁኔታ ውጪ አገር በአማርኛ ቋንቋ ከሚተላለፉ ሬዲዮኖች ውስጥ አውስትራሊያ አትላንታና ካናዳ የሚገኙ ሬዲዮ ጣቢያዎች አነጋግረውን ዘግበውታል” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡

ከተቋቋሙት ኮሚቴዎች መካከል የህግና ሰብአዊ መብት ጉዳዮች ኮሚቴ ስብሳቢን አቶ ሽመልስ ሀብቴን ኮሚቴያችሁ እስከ አሁን ድረስ ምን ምን ተግባራትን አከናወናችሁ ወደፊትስ ምን ለመስራት አቅዳችኃል በማለት ጠይቀን በሰጡን መልስ “እስከ ዛሬ ድረስ እስረኞቹን ለመጠየቅ በተደጋጋሚ ሞክረን ተከልክለናል፡፡ አሁን ለሚመለከተው የመንግስት አካል በጽሑፍ ለማወቅና በህግ ለመጠይቅ እየተንቀሳቀስን ነው” ብለውናል፡፡ በተያያዘ ዜና ባለፈው ሳምንት እስረኞችን ለመጠየቅ ሄደው የተከለከሉት የፓርቲው አመራሮች ኢ/ር ግዛቸው አቶ ዳዊት አስራደ፣ አቶ ሽመልስ ሀብቴና ጠበቃ ዳንኤል ካፌ መሆናችን ይታወቃል፡፡ ሆኖም ግን አብረዋቸው ከሄዱት ውስጥ አቶ አስራት ጣሴ አቶ ሰለሞን ታደሰ የሚገኙበት ሲሆን በአሁኑ ሳምንት ደግሞ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚውና የብሔራዊ ም/ቤት አባላት ሄደው መከልከላቸውን መረዳት ተችሎአል፡፡

በተያያዘ ዜና የቀድሞ የኢህዲሪ ፕሬዝዳንትና የወቅቱ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ /አንድነት/ ሊቀመንበር የሆኑት ዶ/ር ነጋሶ ጊዳዳ ከትላንት በስቲያ እስረኞችን ለመጠየቅ ሄደው መከልከላቸውን የመረጃ ምንጮቻችን ግልፀዋል፡፡ በዕለቱ ከተወሰኑ ግለሰቦች ጋር በመሆን በፌዴራል ፖሊስ ወንጀል ምርመራ እስር ቤት እንደደረሱ በእስር ላይ የሚገኙትን የፖለቲካ አመራሮችንና ጋዜጠኞችን ማግኘት እንደሚፈልጉ ገልጸው ጠይቀዋል መዝጋቢ ፖሊሶች በስም ማንን ብለው ሲጠይቁ ዶ/ር ነጋሶ አቶ አንዱዓለም አራጌን ሲሉ መዝጋቢ ፖሊሶች አንድ የፖሊስ ኃላፊን ጠርተው አቶ አንዱዓለምን እንጠይቅ እያሉ ናቸው ብለው ሲያመለክቱ ፖሊሱ በንዴትና በቁጣ “ዋ አይቻልም፡፡ እዚህም መቆም አይቻልም በግቢው ውጡ” በማለትና በማመናጨቅ ለማስወጣት ሞክሮአል፡፡ ለምን እንድጠይቅ አይፈቀድልኝም ብለው ሲጠይቁ ፖሊሱ የከለከለው የበላይ አካል ነው፡፡ በማለት መልሷል፡፡ የከለከለው የበላይ አካል ማነው በማለት ዶ/ር ነጋሶ ሲጠይቁ ፖሊሱ አላውቅም በማለት መልሷል፡፡ በሥፍራው የነበሩት እ/ር ዘለቀ ረዲ ፖሊሶችን ኃይለ ቃልና ማመናጨቅ ለምን ያስፈልጋል፡፡ እኚህ ሰውዬ ቢያንስ በአንድ ወቅት የአገሪቱ ፕሬዝደንት የነበሩ ናቸው፡፡ በዕድሜም አዛውንት ናቸው፡፡ እየጠየቁ ያሉት ህጋዊ ጥያቄ ነው፡፡ እስረኛ መጠየቅ እፈልጋለሁ ለምን ትከለክሉኛላችሁ? ነው ያሉት፡፡ “ቁጣን መወራጨትን ምን አመጣው”? ሲሉ ፖሊሶቹን ሲያነጋግሩ ተደምጧል፡፡ “የምናውቀው ነገር የለም፡፡ ይውጣ ይውጣ” ሲሉ ፖሊሶች በቁጣ እና በኃይለ ቃል መልሰዋል፡፡ በመጨረሻም እንደ ማንኛውም ጠያቂ ያመጡትን ስንቅ ላይ የተጠያቂውን ስምና ያመጡትን ሦስት ሰዎች ስም በመጻፍ ስንቁን ሲያስረክቡ የሌሎች ጠያቂዎች ሲገባ የዶ/ር ነጋሶ የእ/ረ ዘለቀና አብሮአቸው ያለው አንድ ጠያቂ ስም ያለበትን ወረቀት ፖሊሱ ተቀብሎ የጠያቂዎቹን ስም ቀዳዶ ጥሎታል፡፡ እነ ዶ/ር ነጋሶም ግቢውን በመልቀቅ ወጥተዋል፡፡

ስለነበረው አጠቃላይ ሁኔታ አስተያየታቸውን እንዲሰጡን የጠየቅናቸው እ/ር ዘለቀ ረዲ እንዳሉት “እኔ በዜግነቴ ካዘንኩባቸው ቀናቶች ዛሬ አንዱ ነው፡፡ ፖሊሶቻችን የተገነቡበት ሥነ ምግባር በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ አንድ ሰው ወንጀል እስካልሠራ ድረስ ህጋዊ መብቱን መጠየቅ ጥፋት አይደለም፡፡ ሰው በዕድሜው በትምህርቱ በኃላፊነቱ ይከበራል፡፡ የማታውቀውን ሰውም ታከብረዋለህ እዚህ የምትመለከተው ግን ያሳፍርሃል፡፡ ጥላቻን ምን አመጣው? ቁጣን ድንፋታ ለምን አስፈለገ? በትህትና በኢትዮጵያዊ ጨዋነት መነጋገርን ምን ከለከለን፡፡ ፖሊሶች ዜጐችን በጥላቻ፣ በጠላትነት መንፈስ ለምን ይመለከቱናል? የቆሙትም ለአገርና ለህዝብ አይደለምን? አገልጋይነታቸውስ ለማነው? በእውነት እኔ እንደግለሰብ በእጅጉ አዛኜአለሁ” በማለት ቅሬታቸውን በሀዘን ገልፀዋል፡፡ ከፍተኛ ሁኔታ የማመናጨቅ ተግባር የተፈፀመባቸው ዶ/ር ነጋሶ በተረጋጋ መንፈስ ወጥተው ሲሄዱ መመልከት ተችሎአል፡፡

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።

የፍኖት እትም ዘጠን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ