ፎኖት- ፌደራላዊ ያልሆነ ፌደራሊዝም – ዶር ኃይሉ አርዓያ
የዚህ ጽሑፍ ዋና ዓላማ የደርግ አሃዳዊነትንና የኢህአዴግ ፌደራላዊነትን በተመለከተ ውይይት ለመክፈት ነው፡፡ ይህን ጉዳይ በተመለከተ እኔ አንድ አቋም አለኝ፡፡ ይህ አቋም የኢህአዴግ ፌደራላዊነት ከደርግ አሃዳዊነት የሚለየው በቅርጽ ብቻ ነው፡፡ በይዘት ወይም በአፈጻጸም ወይም በተግባር ግን ሁለቱም ከሞላ ጎደል ተመሳሳይ ናቸው የሚል ነው፡፡ በሌላ አነጋገር የኢሕዴግ ስርዓት ፌደራላዊ ያልሆነ ፌደራሊዝም ነው ማለት ነው፡፡
በውይይቱ ሂደት ይህ አቋም ትክክል ሆኖ ከወጣ አሁን አለን የምንለው ፌደሬሽን በቅርጽ ፌደራላዊ በይዘት ግን አሃዳዊ መሆኑን እንገነዘባለን ማለት ነው፡፡ እኔ የፖለቲካ ሳይንስ ተማሪ አይደለሁም፡፡ የተግባር ፖለቲካ ግን የዕለት ተዕለት ሥራዬ ሆንዋል፡፡ በተለይ የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን በዚህ ውይይት ላይ በመሳተፍ አሁን የምንከተለው የፌደራል ሥርዓት እውነተኛ ባህሪ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ግልጽ እንዲሆን የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እንደሚያደርጉ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡
ፌዴሬሽን ምንድን ነው? ወደ ዝርዝር ሳይገባና በአጭሩና በተራ ቋንቋ ፌደሬሽን ማለት ሁለት ወይም ከዚያ በላይ የሆኑ በተወሰነ መልክአ ምድራዊ ክልልና በግልጽ በተቀመጠ የመንግሥትነት ባህሪ ባለው የአስተዳደር ሥርዓት ውስጥ የሚኖሩ ሕዝቦች ወይም ስቴቶች ከሉአላዊነታቸው ቀንሰው በመስጠት በሚፈጥሩት ማከላዊና የጋራ የሆነ ሥልጣን አካል የሚተዳደሩበት ሥርዓት ነው፡፡
እነዚህ ሕዝቦች ወይም ስቴቶች እያንዳንዳቸው መሠረታዊ ሉዐላዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ሕገ መንግሥት አላቸው፡፡ የዚሁ ሉዐላዊነት ሌላ መገለጫ የሆነ ሰንደቅ ዓላማም አላቸው፡፡ በቋንቋቸው ይጠቀማሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አጠቃላይና የጋራ ሉዐላዊነታቸውን የሚያረጋግጥ ፌደራላዊ ሕገ-መንግሥትና ሠንደቅ ዓላማም አላቸው፡፡ ስለዚህ ሥልጣን በማዕከልና በፌደሬሽኑ አባላት መካከል የተከፋፈለ ነው፡፡ የፌደሬሽኑ አባላት ለፌደራሉ በፈቃዳቸው ከሰጡት ሥልጣን ውጭ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር ሙሉ ሥልጣን አላቸው፡፡
በአንጻሩ በአሐዳዊ መንግሥት ሥርዓት ሙሉ ሥልጣን የሚያዘው በአንድ ማዕከላዊ አካል ነው፡፡ ክልሎች ሕግ የማውጣትም ሆነ ፖሊሲ የመቅረጽ ሥልጣን የላቸውም፡፡ ሆኖም ማዕከላዊው መንግሥት በሕግ የተመጠነ ሥልጣን ለክልሎች በውክልና ሊሰጠ ይችላል፡፡
በኢህአዴግ አሐዳዊ ሥርዓት የፌዴራሉ መንግሥት አባላት ዘጠኝ ሲሆኑ እነዚህም የትግራይ፣ የአፋር፣ የአማራ፣ የኦሮሚያ፣ የሱማሌ፣ የቤንሻጉል/ጉሙዝ፣ የደቡብብሔሮች/፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች፣የጋምቤላ ሕዝቦችና የሐረሪ ሕዝብ ክልሎች ናቸው፡፡
የደርግ አሐዳዊ ሥርዓት በ5 ራስ ገዝ አካባቢዎችና በ24 የአስተዳደር አካባቢዎች በድምሩ በ29 አካባቢዎች የተዋቀረ ነበር፡፡
አምስቱ ራስገዝ አካባቢዎች
የሚከተሉት ነበሩ፡-
1. ኤርትራ ራስገዝ
2. የትግራይ ራስገዝ
3. የአሰብ ራስገዝ
4. የድሬደዋ ራስገዝ
5. የኦጋዴን ራስገዝ
የአስተዳደር አካባቢዎች፡-
1. የሰሜን ጎንደር
2. የደቡብ ጎንደር
3. የሰሜን ወሎ
4. የደቡብ ወሎ
5. የምስራቅ ጎጃም
6. የምዕራብ ጎጃም
7. የመተከል
8. የአሶሳ
9. የወለጋ
10. የሰሜን ሸዋ
11. የአዲስ አበባ
12. የምዕራብ ሸዋ
13. የደቡብ ሸዋ
14. የምዕራብ ሐረርጌ
15. የመሥራቅ ሐረርጌ
16. የአርሲ
17. የባሌ
18. የጋምቤላ
19. የኢሉባቦር
20. የከፋ
21. የጋሞጎፋ
22. የሲዳሞ
23. የኦሞ
24. የቦረና አካባቢዎች ነበሩ፡፡
ራስ ገዝ የተባሉት 5 አካባቢዎች የጠረፍ አካባቢዎች፣የፀጥታ ችግር ያለባቸውና በጂኦ ፖለቲካዊ ባህሪያቸው ምክንያት ለሃገሪቱ ደህንነትና ሠላም ሲባል ከሌሎቹ አካባቢዎች በተለየ ዓይን ሊታዩና የተለየ ሥልጣን ሊሰጣቸው ይገባል ተብለው የታሰቡ አካባቢዎች ናቸው፡፡
ሆኖም የኢሕዲሪ ሕገ-መንግሥት ፀድቆ ሲወጣ በራስ ገዝና በአስተዳደር ክልሎች መካከል የረባ የመብትም ሆነ የሥልጣን ልዩነት አልነበረም፡፡ የኢህዲሪ ሕገ-መንግሥት ራስ ገዝ አካባቢዎች የሚኖራቸው መብትም ሆነ ሥልጣን በሕግ ይደነገጋል በማለት አልፎታል፡፡ ሆኖም የተባለው ሕግ ሳይወጣ ሥርዓቱ ፈረሰ፡፡
የኢህአዴግ የፌደራል መንግሥት አባላት በወረቀት ላይ ያላቸው መብትና ሥልጣን የደርግ ሥርዓት ራስ ገዝና የአስተዳደር አካላት ከነበራቸው መብትና ሥልጣን እጅጉን የላቀ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡ ሆኖም ሁለቱን ሥርዓቶች አንድ የሚያደርጋቸው አንድ ነገር አለ፡፡ ሁለቱም እጅግ የተማከለ፣የመቆጣጠሪያ መዋቅሩ ከማዕከል እስከ ቀበሌ ድረስ የወረደ የፓርቲ ሥርዓት ሰለባዎች ናቸው፡፡ የደርግ ራስ ገዝና የአስተዳደር አካባቢዎች የኢሠፓ የቁጥጥር ሥርዓት ሰለባዎች ነበሩ፡፡ የአሁኑ የፌደራል መንግሥት አባል መንግሥታትም የኢህአዴግ ቁጥጥር ሥርዓት ሰለባዎች ናቸው፡፡ የደርግ ራስ ገዝና የአስተዳደር አካላት በአሃዳዊ መንግሥት ፈቃድ በውስጥ አስተዳደራቸው ትንሽ ራሳቸውን በራሳቸው የማስተዳደር መብት (autonomy) ቢኖራቸውም ከማዕከል እስከ ቀበሌ የተዋቀረው ኢሠፓ የአለቻቸውን ትንሽ ነፃነት ይወስድባቸዋል፡፡ የራስገዝም ሆነ የአስተዳደር አካባቢዎች የኢሰፓ ከፍተኛ ካድሬዎች ነበሩ፡፡ በአጠቃላይ የራስ ገዝና የአስተዳደር አካባቢዎች እንቅስቀሴ የሚኖሩትና ፕሮግራሞችን ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢሠፓ መሪዎች ነበሩ፡፡ ራስ ገዝና የአስተዳደር አካባቢዎች ተግባራዊ የሚያደርጉት የኢሠፓን ፕሮግራም ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ድሮውንም ሥርዓቱ ከስም (ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ) በስተቀር ዴሞክራሲያዊ ስላአልነበረ በአንድ ፓርቲ ቁጥጥር ሥር መዋሉ አያስደንቅም፡፡
የአንድ ፓርቲ ቁጥጥር አለአግባብ መሆኑ ጎልቶ የሚታየው ከፌደራላዊ ሥርዓቱ ጎን ለጎን ሲታይ ነው፡፡ ፌደራላዊ ሥርዓት በአግባቡ ከተተገበረ ለኢትዮጵያ ተስማሚና ተገቢ ሥርዓት ነው፡፡ ሕገ መንግሥት ጸድቆ ፌደራላዊ ሥርዓት ተመሠረተ ሲባል የኢትዮጵያ ሕዝብ አዲስ ቀን መጣ ብሎ ተስፋው ለምልሞ ነበር፡፡ ሆኖም የተያዘው ተስፋ ሁሉ ከወረቀት ባለፈ በተግባር ወደ ዕለት ተዕለት ሕይወት አልሸጋገር አለ፡፡ በተለይ የፌዴራል ሥርቱ እንደተጀመረ አብዛኛዎቹ ክልሎች በኢህአዴግ የተመደቡ የቅርብ ተመልካቾች ነበሯቸው፡፡ የእነዚህ ተመልካቾች ዋና ሥራ እነዚህ አዳዲስ ባለሥልጣን ክልሎች ከኢህአዴግ ፍላጎት ውጭ እንዳይሄዱ በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ መንገድ መቆጣጠርና የተፈለገውን መሥመር እንዲይዙ ማድረግ ነበር፡፡
ይህ አሠራር አሁንም እንደቀጠለ ነው የሚታመነው፡፡ ምናልባት አሠራሩ ይበልጥ የተራቀቀ ይመስላል፡፡ ዘጠኙ የፌደራሉ መንግሥት ራሳቸውን በራሳቸው ለማስተዳደር የሚያስችላቸው ሙሉ ሥልጣን የሚሰጣቸው ሕገ መንግሥት አላቸው፡፡ ሠንደቅ ዓላማም አላቸው፡፡ በቋንቋቸው ወይም በመረጡት ቋንቋ ራሳቸውን ያስተዳድራሉ፡፡ ሆኖም ይህ ያልተማከለ የአሠራር ዕቅድ፣እጅግ በተማከለና መዋቅሩን እስከ ቀበሌ በዘረጋ የአውራ ፓርቲ አሠራር ሥርዓት ተጠፍሯል፡፡ ስለዚህ ያልተማከለው የፌዴራል ሥርዓት እንደታሰበው በነፃነት ሊሠራ አልቻለም፡፡ ግልጽ ሆኖ የሚታየው የፌደራልና የተማከለ የአውራ ፓርቲ ሥርዓት አብረው ሊሄዱ እንደማይችሉ፡፡
የፌዴራል ሥርዓት የሚሠራው ነፃነትና የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሰፈነበት ሁኔታ ነው፡፡ ነፃነት በሌለበት፣የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት ባልሰፈነበት እውነተኛ የፌዴራል አሠራር ሊኖር አይችልም፡፡ ይህ ብቻ አይደለም፡፡ የፌደራል መንግሥቱ አባላት የፋይናንስ አቅማቸውን አስካላጎለበቱ ድረስ ነፃነታቸውን የማረጋገጥ አቅማቸውም ደካማ ይሆናል፡፡ የሚንቀሳቀሱት ከሞላ ጎደል ከማዕከል በሚሰጣቸው ድጎማ ነው፡፡ በራሳቸው ፋይናንሳቸውን የማጠናከር አቅማቸው ገና አልዳበረም፡፡ ጠባያቸውን ካላሳመሩ፣ እንደ ውሃ በተቀዳላቸው ቦይ ካልፈሰሱ የድጎማቸውን ሁኔታና የክልላቸውን ልማት አደጋ ላይ ከመጣላቸውም በላይ በቁልፍ ቦታዎች ላይ የተቀመጡ የክልል ሹማምንትም ቦታቸውን ሊያጡ ይችላሉ፡፡ በአሁኑ ጊዜ ቁልፍ የሹመት ቦታ ማጣት ደግሞ በተለመደው ባህላዊ አነጋገር “የአንጀራ ገመድን መበጠስ” ማለት ነው፡፡ በአጭር ጊዜ ውስጥ የመበልጸግ ዕድልን ማጣት ማለት ነው፡፡
በሰለጠነውና በበለጸገው ዓለም ሰዎች ብዙውን ጊዜ ለፖለቲካ ሥልጣን የሚወዳደርበት በአጭር ጊዜ ውስጥ ለመበልጸግ አይደለም፡፡ ፖለቲካ ዓለምና ውስጥ የሚገቡት እምነት፣ዓለማና ራይዕይ ስላላቸውና ያንን እምነት፣ዓላማና ራዕይ እውን ሆኖ ማየት ስለሚፈልጉ ነው፡፡ ብዙዎቹ ሚሊየነሮች ናቸው፣ከፖለቲካ ውጭ ሠርተው የሚያገኙትን ገንዘብ በሥልጣን ቦታ ተቀምጠው ከሚያገኙት ገንዘብ እጅጉን ይበልጣል፡፡ እንደ እኛ ባሉ የሦስተኛ ዓለም አገሮች ግን ሰዎች ከጥቂት ሰዎች በስተቀር ለሥልጣን የሚወዳደሩት በሃገራቸው ውስጥ ከሚገኘው የሃብት ዳቦ ላይ የቻሉትን ያህል በጭቀው ለመውሰድና በአጭር ጊዜ ውስጥ ከድህነት ለመላቀቅ ነው፡፡ ስለዚህ የእኛ አገር የፌደራል አካላት ሹማምንት የፌደራሉ ሥርዓት በትክክል እንዲሠራ የሚከፈለውን መስዋዕትነት እየከፈሉ በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ ከመታገል ይልቅ ታዛዥ መሆንንና የራሳቸውን ሕይወት ማመቻቸትን የመረጡ ይመስላሉ፡፡ በዚህም ምክንያት ፌደራሊዝም ፌደራላዊ ሊሆን አልቻለም፡፡
ፌደራሊዝምን ፌደራላዊ አንዳይሆን የሚያደርገው ሌላው ችግር የሰው ኃይል አቅም ማነስ ነው፡፡ ፌደራሊዝም እንደማንኛውም የመንግሥት አወቃቀር ረቂቅ ሥርዓት ነው፡፡ ዕውቀት፣ልምድና ከፍተኛ የሥራ ዲስፕሊንና ቁርጠኝነቱ ያለው ከፍተኛ የሰው ኃይል ይጠይቃል፡፡ የዚህ ዓይነት የሰው ኃይል በብቃት የለም፡፡ ይህ የሁሉም ክልሎች ችግር ቢሆንም በተለይ ተረስተው በነበሩ የጠረፍ አካባቢዎች ይብሳል፡፡ ዕውቀት ያለው የሰው ኃይል በራሱ ይተማመናል፣ ሥራውን በጥራት ይሠራል፡፡ ዕውቀት ያለው፣በራሱ የሚተማመንና ሥራውን በጥራት የሚሠራ የሰው ኃይል መብቱን ያስከብራል፡፡ የማይሆነውን አይሆንም ይላል፡፡ ነፃነትን ይጠይቃል፡፡
በዚች አጭር ጽሑፍ የአገራችንን ፌደራሊዝም በተመለከተ ሦስት ችግሮችን አንሰተናል፡፡ አንደኛው ችግር በመሠረቱ የነፃነት እጦት ነው፡፡ በአንድ በኩል በፌደራሊዝም፣የሥልጣን ክፍፍል ነው፡፡ በሌላ በኩል የዚህ ዓይነት ፌደራሊዝም ክፉኛ በተማከለና መፈናፈኛ በሌለው አምባገነን አውራ ፓርቲ ሥርዓት ውስጥ ነው ለመሥራት የሚሞክረው፡፡ በቅርጽ ፌደራላዊ ነው በተግባር ግን የተማከለ ወይም እንደ ደርግ ኢሠፓ ሥርዓት አሃዳዊ ነው፡፡ በዚህ ዓይነት ሁኔታዎች ሊቀጥሉ አይገባም፡፡ የሚያሳዝነው ግን ኢህአዴግ አሁን በአለው መልኩ በሥልጣን ላይ እስከቀጠለ ድረስ፣ የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ እስካልሰፈነ ድረስ ለውጥ ሊመጣ የማይችል መሆኑ ነው፡፡ ሁለተኛው የፌደራል መንግሥት አባላቱን እጅ የሚያስረው ደግሞ የፋይናንስ አቅማቸው መዳከምና ለድጎማ መዳረጋቸው ነው፡፡ ለድጎማ መዳረግ በኢህአዴግ እጅ ላይ መውደቅ ዓላማ ነው፡፡ ሦስተኛው የቆየ ሰው ኃይል አቅም ማነስ ችግር ነው፡፡ ወደ ውስጥ ሲገባ ደግሞ ሌሎች ችግሮችም ሊኖሩ ይችላሉ፡፡
በሃገራችን ፌደራሊዝም ከተመሠረተ አሥራ ስድስት ዓመት ያህል ሆኖታል፡፡ ሥርዓቱን በተመለከተ ብዙ ምሁራን ብዙ ብለዋል፡፡ በቅርቡ አዲስ አበባችን ፌደራሊዝምን በተመለከተ ዓለምአቀፍ ጉባኤ አካሂዳለች፡፡ በዚህ ጉባኤ ብዙ ጽሑፎች ቀርበዋል፣ብዙ ሰዎች ብዙ ብለዋል፡፡ ኢትዮጵያም በፌደራሊዝም ሞዴልነትም ምስጋናዎች ተችረዋል፡፡ ጥያቄው አመስጋኞቹ እነማን ናቸው? ስለኢትዮጵያ ምን ያህል ያውቃሉ? የሚለው ነው፡፡ ያም ሁሉ ሆኖ፣ተብሎም በሃገራችን በመሬት ላይ ለውጥ የለም፡፡ ድመት እንዳለችው “ያው በገሌ” ነው፡፡ እውነተኛ ፌደራሊዝም በሃገራችን እውን ሆኖ ማየት እንፈልጋለን፡፡ ከፓርቲ ቁጥጥር፣ከፓርቲ ጣልቃ ገብነት ነፃ የሆነ እውነተኛ ፌደራሊዝም ማየት እንፈልጋለን፡፡ ኢህአዴግ በአሁኑ መልኩ ሥልጣን ላይ እስካለ ድረስ ግን ይህ ምኞታችን እውን ሊሆን አይችልም፡፡ ምኞታችን እውን እንዲሆን የመድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲ መኖር አለበት፡፡ መድበለ ፓርቲ ዴሞክራሲን ለማምጣት በሕጋዊና ሠላማዊ መንገድ ጠንክረን መታገል አለብን፡፡
በመጨረሻም ስለመንግሥት አወቃቀር ወይም ቅርጽ ስንነጋገር ዋናው ቁምነገር ያለው ቅርጽ ላይ አለመሆኑን ልብ ልንል ይገባል፡፡ ስለ አሃዳዊነትና ስለፌደራላዊነት አንስተናል፡፡ ብዙ ጊዜ ፌደራላዊነት ዴሞክራሲያዊነት፣አሃዳዊነት ደግሞ ኢ-ዴሞክራሲያዊነት እንደሆነ ይታሰባል፡፡ በዓለማችን አሐዳዊ ሆነው በሚያጠግብ ሁኔታ ዴሞክራሲያዊ የሆኑ ብዙ አገሮች አሉ፡፡ ለምሳሌ ሩሲያ ፌዴራላዊት ነች፡፡ የዴሞክራሲ ተምሣሌት ግን አይደለችም፡፡ አሜሪካ ፌደራላዊ ናት፡፡ እንግሊዝ ደግሞ አሃዳዊ ናት፡፡ ሁለቱም የዴሞክራሲያዊነት ተምሳሌቶች ናቸው፡፡ ኖርዌይ፣ስዊድንና ሆላንድ ለምሳሌ አሃዳዊ ናቸው፡፡ ከዚያም አልፈው ዘውዳዊ ናቸው፡፡ ታዲያ እነዚህም አገሮች በዴሞክራሲያዊነታቸው በአርአያነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
እርግጥ ቅርጽ ለአፈፃጸም ሁኔታዎችን ያመቻቻል፡፡ ሆኖም ቅርጽ ሁሉ ነገር አይደለም፡፡ ታዲያ ቁምነገሩ ያለው ምኑ ላይ ነው? የሚል ጥያቄ ይነሳል፡፡ ቁምነገሩ ያለው የአንድ አገር ሕዝብ የተማረ፣በአስተሳሰብ የሠለጠነ፣በኢኮኖሚ የበለጸገ፣በዴሞክራሲያዊ ባህሉ የዳበረ፣የሰው ልጅ ሕይወት ክቡርነትን የተገነዘበ፣ለሕግ የበላይነት ከፍተኛ አክብሮት ያለው፣እውነትን፣ቅንነትን፣ ታማኝነትን፣ተጠያቂነትን የዕለት ተዕለት ህይወቱ መመሪያ ያደረገ እመሆኑ ላይ ነው፡፡ እነዚህና ሌሎች ተመሳሳይ ባህሪያት ያሉት ሕዝብ የሥርዓቱ ቅርጽ አሃዳዊም ይሁን ፌደራላዊ ሥርዓትን ማደጊያውና መበልጸጊያው ሊያደርገው ይችላል፡፡
ለውይይት መነሻ ይህን ካልኩ ይበቃል፡፡ መድረኩም ይኸው፡፡ እንወያይና የፌደራል ሥርዓታችን እውነተኛ ባህሪ ግልጽ እናድርግ፡፡
ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።