ፍኖት – የኢትዮጵያ ፖለቲካ በአገር ቤት እና በውጭ አገር – ግርማ ካሳ

በሁለተኛው የአለም ጦርነት ወቅት የጀርመን ባህር ኃይል መርከቦች እንግሊዝን ከበዋል፡፡ የአሜሪካ መርከቦች ሲቀርቡ፣ በቀላሉ በጀርመን ሰብማሪንስ (በባህር ላይ ሳይሆን በባህር ውስጥ የሚሄዱ መርከቦች) እየተጠቁ በብዛት ይሰምጡ ጀምር፡፡ ጀርመኖች በባህር ላይ ጦርነት በበርካታ መስፈርቶች የበላይነት ነበራቸው፡፡ አሜሪካኖች ግን መርከቦች በሰጠሙባቸው ቁጠር፣ ሽንፈት ተቀብለውና ተስፋ ቆርጠው አልተቀመጡም፡፡ ሌሎች መርከቦች በብዛት ማሰማራት ጀመሩ፡፡ ወደ እንግሊዝ የሚላኩት የአሜሪካን መርከቦች፣ ጀርመኖች ሊያሰጥሟቸው ከሚችሉት በላይ በመሆናቸው የተወሰኑቱ የእንግሊዝ ወደቦች መድረስ ጀመሩ፡፡

ይሄን ምሳሌ ያነሳሁት ያለ ምክንያት አይደለም፡፡ ምንም እንኳን አሜሪካኖች ከጀርመኖች ጋር ያደርጉት እንደነበረው የባህር ኃይል ወታደራዊ ትንቅንቅ ባናደርግም፣ በአገራችን እኩልነት፣ መልካም አስተዳደር፣ ፍትህ፣ የዜጎች ሰብአዊ መብት መከበር እንዲሰፍንና የኢትዮጵያ አንድነት እንዲጠበቅ የሚደረግ፣ አባታችን ፕሮፌሰር አስራት ወልደየስ፣ እህታችን ሽብሬ ደሳለኝ፣ ወንድሞቻችን ባይሳ ዳባና አረጋዊ ገብረዮሐንስ የመሳሰሉ በርካታ ወገኖቻችን በሕይወታቸው ዋጋ የከፈሉበት ብዙዎች የታሰሩበትና ከፍተኛ መከራና እንግልት የተቀበሉበት፣ የሰላማዊ ትግል ትንቅንቅ አለ፡፡

አዎ ያኔ ጀርመኖች ለተወሰነ አመታት አይለው እንደነበር፣ ሕዝባችንን በዘር ከፋፍለው የመከራ፣ የድህነት፣ የረሃብ ቀንበር የጫኑበት ጥቂት አምባገነኖች ለጊዜው አይለው ሊሆን ይችላል፡፡

የግንቦት ሰባት ምርጫ ከተደረገ ስድስት አመታት አልፈዋል፡፡ ያኔ በአገር ቤት፣ ቅንጅት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ አራት ድርጅቶችን አሰባስቦ ተንቀሳቀሰ፡፡ በነዶ/ር መረራ ጉዲና የሚመራው የኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ኃይሎች ሕብረት በውጭ ያሉትን በአገር ቤት ያሉትን ድርጅቶች አገናኝቶ የሰላማዊ ትግል ዘመቻውን ቀጠለ፡፡ በውጭ አገር ያለው ኢትዮጵያዊ፣ አገር ቤት ካለው ኢትዮጵያዊ ጋር በቅርበት፣ በጋራ የሰራበት፣ በርግጥ የኢትዮጵያውያን ትብብርና አንድነት የታየበት ታሪካዊ ወቅት ነበር፡፡ የኢሕአዴግን የስልጣን አገዛዝ ከፍፃሜ ለማድረስ ጫፍ የተደረሰበትም ጊዜ !

በተለያዩ ማዘናጊያ ታክቲኮች፣ በምእራባውያንም ትልቅ ርዳታ፣ በኋላም ዜጎችን በጥይትና በጭካኔ እንደ ቅጠል በማርገፍ፣ አገዛዙ እስካሁን ድረስ ስልጣን ላይ ተፈናጦ ይገኛል፡፡ የቅንጅት መሪዎች ታሰሩ፡፡ አገር ቤት ያሉ የሕብረት መሪዎች ፓርላማ ገቡ፡፡ ውጭ አገር ያሉት የሕብረት መሪዎች አገር ቤት ባሉት አጋሮቻቸው አኮረፉ፡፡ (ኩርፊያቸው አገር ቤት ካለው ወገናቸው ለይቷቸው ወደ መረሳት አደረሳቸው እንጂ ምንም ያመጣላቸው ነገር የለም) ወደ ቅንጅት ስንመለስ፣ አገር ቤት ያሉ መሪዎቹ በመታሰራች በውጭ አገር ያሉ የድጋፍ ድርጅቶች፣ ትግሉን የመምራት ሃላፊነት ተጣለባቸው፡፡ ከቅንጅት የሰላማዊ ትግል ስልት አማራጭ ውጭ፣ የትጥቅ ትግልን እናራምዳለን ከሚሉ ከኦነግ፣ኦብነግ፣ አርበኞች ግንባርና ከሲዳማ ነፃ አውጭ ግንባር ትብብር ፈጠሩ፡፡ ትኩረቱ ከአገር ቤቱ ትግል ወደ ውጭ አገሩ ትግል ዞረ፡፡

የቅንጅት መሪዎች ከቃሊቲ እስር ቤት ሲፈቱ፣ ዲያስፖራ በቀል በሆኑ ጉዳዮች ዙሪያ፣ በመካከላቸው ልዩነቶች ተፈጠሩ፡፡ የመጀመሪያው ተመራጭ የአዲስ አበባ ከንቲባ፣ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ፣ የቅንጅት ዋና ጸሐፊ አቶ ሙሉነህ እዮኤልን የመሳሰሉ አንጋፋ የቅንጅት አመራር አባላት “ሰላማዊ ትግል አይሰራም” በሚል የስደት ኑሮ ጀመሩ፡፡ ግንቦት ሰባት የተሰኝን ድርጅት አቋቁመው፣ ያዋጣል በሚሉትና በሚያምኑበት ትግል መስክ ተሰማሩ፡፡ የግንቦት ሰባት መሪዎች አገር ቤት መዋቅር እንዳላቸው ይናገራሉ፤ ግን እስከ አሁን፣ በሕዝብ የሚታየው እንቅስቃሴያቸው፣ ከሞላ ጎደል በውጭ አገር ሰብሰባዎች መጠራት ላይ ብቻ ያተኮረ ይመስላል፡፡

በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ይመራ የነበረውና አብዛኛውን የቅንጅት ከፍተኛ አመራር ያቀፈው ቡድን፣ ገዢው ፓርቲ የቅንጅትን ስም ለአየለ ጫሚሶ ቡድን፣ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ ስለሰጠ፣ የአንድነት ለዲሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ በሚል ስም መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ድርጅቱ በሕዝብ ያለው ተቀባይነት በአጭር ጊዜ ውስጥ ከፍ እያለ ሲመጣ የአንድነት ሊቀመንበር ወ/ት ብርቱካን በግፍና በጭካኔ ወደ ቃሊቲ ተወሰደች፡፡ በነፍስ ገዳዮች ላይ ያልታየ ቶርቸር ደረሰባት፡፡ ለስድስት ወራት ጨለማ ቤት ውስጥ እንድትቀመጥ ተደረገ፡፡

በርካታ የሕብረትና የቅንጅት ደጋፊ የነበሩ፣ በውጭ አገር የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን “አገዛዙ በሰላም አይወርድም” የሚል አቋም መያዝ ጀመሩ፡፡ ብዙዎች ተስፋ የመቁረጥ ሁኔታ ታየባቸው፡፡ በመሆኑም በአገር ቤት የሚደረገውን ትግል ለመርዳት ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረው አይነት ትጋትና ፍላጎት እየመነመነ መጣ፡፡ ይልቅስ “ከሰላማዊ ትግል ውጭ ሊኖር የሚችል ሌላ አማራጮች ካለ?” በሚል “የትጥቅ ትግል እናደርጋለን” የሚሉ ቡድኖች አካባቢ የመሄድና ስብሰባዎቻቸውን የመሳተፍ ሁኔታ ተጀመረ፡፡ አብዛኛው የዲያስፖራ ኢትዮጵያው ትኩረቱን አገር ቤት ከሚደረገው ትግል አንስቶ በውጭ አገር ባሉ ድርጅቶች ላይ ያውም ደግሞ በአስመራ ላይ እያደረገ መጣ፡፡

በአገር ቤት የአንድነት ለዲሞከርሲና ለፍትህ ፓርቲ የተለያዩ ኃይሎችን በአንድ ላይ በማምጣት፣ ትግሉ አገር አቀፍና ሥር የሰደደ እንዲሆን ጥንቃቄ፣ ብስለት፣ ትእግስትና ቁርጠኝነት በተሞላበት ሁኔታ ትግል እያደረገ ነው፡፡ በቅርቡ በአንድነት ፓርቲ የሕዝብ ግንኙነት ክፍል፣ አገር ውስጥ የሚታተም፣ የጠለቀ የፖለቲካ ይዘት ያላቸው ፅሁፎችን ያዘለ፣ ሕዝቡን የሚቀሰቅስና ገዢው ፓርቲ እያደረገ ያለውን የስልጣን መባለግ የሚያጋልጥ፣ ሳምንታዊ ጋዜጣ አውጥቶ ለሕዝብ እንዲደርስ እያደረገ ነው፡፡

ይህ ጋዜጣ ቢያንስ ቢያንስ ለማተሚያ ብቻ 11 ሺህ የኢትዮጵያ ብር (ወደ 640 ዶላር) ያወጣል፡፡ ጋዜጣው ከአዲስ አበባም አልፎ በሌሎች ግዛቶች ለማዳረስ ትልቅ እቅድ አለ፡፡ ይህም ሕዝቡን ለማንቃትና ለማደራጀት ትልቅ ሚና ሊጫወት የሚችል ቁልፍ የሕዝብ ግንኙነት መሳሪያ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡

የአንድነት ፓርቲ አባል የሆነበት፣ መድረክ ከአራት አምስት ወራት በፊት በመቀሌ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ያሉበት ሕዝባዊ ስብሰባ ማድረጉ በሰፊው ተዘግቧል፡፡ ለስብሰባው ወደ 16000 ብር (950 ዶላር) ነበር የተከፈለው፡፡ “ከመቀሌው ስብሰባ ውጭ ሌሎች በርካታ ሕዝባዊ ስብሰባዎች በስፋት ለምን አይደረግም?” የሚል ጥያቄ ለአመራር አባላቱ ሲቀርብላቸው በዋናነት እንደምክንያት የሚያቀርቡት የገንዘብን ችግር ነው፡፡

አረና ትግራይና አንድነት ፓርቲ በጋራ ሆነው ስድስት ጽ/ቤቶች በትግራይ ነበሯቸው፡፡ አሁንም በገንዘብ ችግር ምክንያት በማይጨውና በሽሬ የሚገኙ ጽ/ቤቶች ተዘግተዋል፡፡ “ለመታገልና መስዋእትነት ለመክፈል ሕዝቡ ዝግጁ ነው፡፡ የሰው ኃይል ችግር የለንም፡፡ ችግራችን ገንዘብ ነው” ይላሉ የአረና አመራር አባላት፡፡

በውጭ የሚገኘው ኢትዮጵያዊ ደገፈም አልደገፈም፣ አገር ቤት ያሉት ወንድሞቻችንና እህቶቻችን ሕይወታቸውን አሳልፈው በመስጠት አምባገነንነት እየታገሉ ነው፡፡ ጠንካራ ናቸው? ጠንካራ አይደሉም፡፡ ብዙ ይቀራቸዋል ? አዎን ብዙ ይቀራቸዋል፡፡ አገዛዙን መቋቋም ይችላሉ ? አሁን ባሉበት ሁኔታ መቋቋም አይችሉም፡፡ ነገር ግን መልካም ጅማሬ ላይ ነው ያሉት፡፡ ተጨባጭ የሆኑ ሥራዎች እየሰሩ ነው፡፡ ሕዝቡን ባላቸው የገንዘብ አቅምና መጠን እያደራጁት ነው፡፡ ከሕዝቡ ጋር ሆነው ብሶቱን በድፍረት እያሰሙለት ነው፡፡ ዛሬ አንድ ተብሎ ነው ነገ ሁለት የሚባለው፡፡

በውጭ አገር የምትኖሩ ውድ ወገኖቼ፡

እንግዲህ በውጭ አገር የምንኖር እኛ፣ በአገር ቤት ያሉ ወንድሞቻችን እና እህቶቻችን እየታሰሩ፣ እየተደበደቡ፣ ከሥራ እየተባረሩ፣ እንግልትና ወከባ እየደረሰባቸው ተስፋ ሳይቆርጡ ትግሉን ተያይዘው ባሉበት ሁኔታ፣ እኛ በአንጻራዊነት ሲታይ በምቾት የምንኖር፣ ተስፋ ቆርጠን ፊታችንን ልናዞርባቸው ይገባልን ? በጭራሽ አይገባም!!!

የኢሕአዴግ ትልቁ የአፈና ስትራቴጂ በአገር ቤት ጠንካራ ተቃዋሚ እንዳይኖር ማድረግ ነው፡፡ የአሜሪካ መርከብ እንግሊዝ እንዳይደርስ ማድረግ ነው፡፡ ነገር ግን መርከቦች አብዝተን ልናሰማራ ያስፈልጋል፡፡ በሌለላ አባባል ተስፋ መቁረጥ የለብንም፡፡ በዘጠና ሰባት፣ እንደጠበቅነው ውጤት ባይገኝም፣ ከኛው ጋር የነበሩ መሪዎቻችን የምንላቸው አንገታችንን ቢያስደፉንም፣ ፊታችንን ውጤት ሊያመጣ ከሚችለው ከሰላማዊው ትግል ማዞር የለብንም፡፡ የበለጠ እንዳውም በእልህና በብርታት መነሳት ያለብን ጊዜ ነው፡፡ ትኩረታችን ወደ ኢትዮጵያ መሆን አለበት፡፡ በዚያ ያሉ ወገኖቻችን ጎን መሰለፍ አለብን፡፡

የፈለገ የተለያዩ ስብሰባዎች በውጭ አገር ብናደርግ፣ የፈለገ ሰልፎች ብንወጣ፣ የፈለገ ጠዋትና ማታ ገዢውን ፓርቲ እየረገምን ብንጽፍ፣ የፈለገ ከውጭ አገር በራዲዮና በቴሌቪዥን ዜናዎች ብናሰራጭ፣ የኢትዮጵያ ሕዝብ ከፍርሃት ካልወጣና በራሱ መተማመን ካልጀመረ በቀር ለውጥ ሊመጣ አይችልም፡፡ ለዚህም ሕዝቡን ማደራጀት ያስፈልጋል፡፡ ኢሕአዴጎችን በውጭ ያለነው ኢትዮጵያውያን ለብቻችን በባዶው የምናሰማቸው ጫጫታዎች ያሰቃቸዋል እንጂ አያስፈሯቸውም፡፡ የሚያስፈራቸው የኢትዮጵያ ህዝብ ቀና ማለት ብቻ ነው፡፡ትላንት ወድቀን ቆስለናል፡፡ ግድ የለም “እህ” እያልን፣ እያማረርን፣ ቁስላችንን እያሻሸን አንቀመጥ፡፡ እንነሳ፣ እንንቀሳቀስ፡፡ ነገም ተመልሰን ልንወድቅ እንችላለን፡፡ ነገር ግን እየወደቅን፣ እየተነሳን የፍትህ አምላክ የሆነው የእግዚአብሄር መልካም እርዳታ ተጨምሮበት ለድል መብቃታችን አይቀርም፡፡

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።


የፍኖት እትም ዘጠን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ

http://www.abugidainfo.com/amharic/wp-content/uploads/2011/09/finote-nesanete-issue-no-9_092711r.pdf