ሉሉ በየት ዞራ መጣች?በይነጋል በላቸው

ስለሉሉ የማያውቅ እንደማይኖር ተስፋ አለኝ፡፡ ሉሉ የአፄ ኃይለ ሥላሤ ድንክ ውሻ ናት ወይም ነበረች – አፈሩ ይቅለላት ነፍሷም በየማነ ብፁዓን አክልብት ይቀመጥና፡፡ ያቺ ድንክዬ የጠቅል ውሻ ታሪከኛ ነበረች አሉ፤ ተራ ውሻ አልነበረችም፡፡ ሥልጣንና ማዕረጓ ራሱ ከንጉሡ በታች ከመኳንንትና መሣፍን በላይ እንደነበር በወቅቱ ለንጉሡ ቅርበት የነበራቸው አረጋዊ ዜጎች ያስታውሳሉ፡፡ የማንንም እግር እየሄደች ብትዘነጥል ከመብቶቿ አነስተኛው ነበር፡፡ ለአፄው ትልቅ ሥራ ትሠራላቸው ስለነበር በተለዬ ሁኔታና ከፈጣሪያቸው ባልተናነሰ ያመልኩባት እንደነበርም ይታወሳል፡፡ ከመኪና ወይ ከአውሮፕላን ቀድማ የምትወርደውና የአካባቢውን ሰላም አረጋግጣ ለንግሡ የምታበስረው እርሱዋ ነበረች – ከፀጥታና ደኅንነት ባለሙያዎች በፊት፡፡ እርስዋ ቀድማ ካልወረደች ንጉሡም ንቅንቅ አይሉም ነበር፤ ጉብኝቱም ይሁን ሌላው ሥራ ሁሉ ጥንቅር ይበል እንጂ እሳቸውና ጂሪያቸው ወደቤተ መንግሥታቸው ይመለሳሉ – እርሱዋ ያላጸደቀችው ጉብኝት ነገር አለዋ! በመተትና በጥንቆላ የሚያምንና በነዚህ ግብኣቶች ዋና ሥራውን የሚያከናውን ሰው እንግዲህ እንዲህ ነው፡፡ ሉሉዬ የነከሰችው ወይም ፊቷን ያዞረችበት ሰው የንጉሡ ጠላትና ተንኮል አሳቢም እንደሆነ ይቆጠርና አሣር ይደርስበት ነበር – አሉ፤ ደግሞ ለአሉ፡፡ ትንግርተኛ ነበረች ይቺ ውሻ፡፡ ስትሞትም ብሔራዊ ሀዘን ታውጆላት ነበር አሉ – እውነት ይሁን ውሸት ይሄኛው አሁን ትዝ አይለኝም፡፡ የሉሉ የሥራ ኃላፊነት ከነቢሾፍቱና ከጣታቸው ከማይለየው ምሥጢራዊ ቀለበት እንዲሁም ከሌሎች ተጓዳኝ የድግምትና የጥንቆላ ሥራዎች ጎን ለጎን መሆኑ ነው፡፡ ሁሉም ግን የመጨረሻ ወድቀትን እንዳላዳነ መገንዘብ ይቻላል፡፡ ከላይ ሲፈረድ መቶ ጠንቋይና መቶ ደብተራ አያድንም፡፡ ‹ጠንቋይ ለራሱ አያውቅ› የሚለውን አሳሳች ብሂል ለጊዜው እንተወውና – ለተወሰነ ምድራዊ ጊዜ ሰይጣናዊና እርኩሳን መናፍስትን በደጀንነት ይዞ በሰዎች ላይ የሚጫወተው አሉታዊ ሚና ስላለው ማለት ነው – አፄውም ሆኑ ሌሎች መሰል ሰብኣዊ ፍጡራን ሥልጣናቸውን ለማቆየት ወይም ሀብት ለማከማቸት ጥንቆላንና መተትን እንደሚያዘወትሩ ነገር ግን በመጨረሻው ሁሉንም – በጊዜ ንስሃ ካልገቡ ነፍሳቸውን ጭምር – እንደሚያጡ ለመረዳት በግድ ዐውደ ምሕረት ዙሪያ ተኮልኩሎ ከልብ ያልመነጨና በራስ ሕይወት ላይ ለመተግበሩ እርግጠኛ መሆን የማይቻልን ስብከተ ወንጌል ማዳመጥ አይሻም፤ የክፉ ነገር መጨረሻው ክፉ መሆኑን ሕይወታችን ራሱ በቂ ምሥክር ነውና፡፡

በዚህ በጥንቆላና መተት ዙሪያ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ብዙ ጓደኞቻችን የት ይደርሳሉ ሲባል በምቀኞቻቸውና በጠላቶቻቸው ስንክልክል ብለው ቀርተዋል፤ ተሸመድምደው የመሬት አጫዋች ሆነዋል፤ ደህይተው ለማኝ ሆነዋል፤ ከመነሻቸው ደንቁረው ማይም ሆነዋል፤ ታውረው አለመሪ ቀርተዋል፤ ባጭሩ ያልሆኑት የለም፡፡ ይህን ብዙዎቻችን እናውቃለን፡፡ አንዳንዶቻችን ግን ይህን አናውቅም ሳይሆን ለማወቅም ፍላጎቱ የለንም፡፡ ምናልባት ፋራ እንዳንባል ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ሞኞች ሆነንም ሊሆን ይችላል፡፡ ምናልባት ያልተማሩና ያልሰለጠኑ እንዳንባል ሊሆንም ይችላል፡፡ ምናልባትም እኛው ራሳችን እንዳንታማ የሸፍጥ ሥራችንን ለመሸፋፈን ከጅለንም ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን የዲያቢሎስን ምድራዊ ሥልጣን መካድ የፈጣሪንም ሥልጣን እንደመገዳደር ይመስላልና ከፍጹማዊ ተጠራጣሪነት ወጥቶ አካባቢን ማጤን ጥሩ ነው፡፡ ዘመናዊ መሆን ጥሩ ነው፤ የተማረ መሆን ወይም መምሰል ደግ ነው፤ መለስ ዜናዊ ከነዚህም ሁሉ በላይ እሳተ መለኮታዊ የዓለምን ዕውቀትና ሥራዬ ቤታዊ ትንታግ ምላስን ይዞ ሲያበቃ በዓለም የመጀመሪያው የሰይጣናዊ ኃይልና ሥልጣን ተጠቃሚ መሆኑን ስንገነዘብ እውነታን መሸምጠጥ የትም እንደማያደርሰን እንረዳለን – መረዳት ለቻልን፡፡ አስመታቾችና አስጠንቋዮች ደግሞ የተጠራጣሪዎችን መጠራጠር እንደመልካም ጎን ይጠቀሙበታል፤ ይህ ለነሱ ሲሳይ ነው፡፡ (They make use of the benefit of the doubt. በፈረንጅኛው ‹ሥልጡን› አገላለጽ!)

ሰሞኑን የታዘብኩትን አንድ ነገር ለመተንፈስ ነው የላይኛውን መንደርደሪያ ያስቀደምኩት፡፡ በከተራ ዕለት ጧት ሦስት ሰዓት አካባቢ እስጢፋኖስ ቤተ ክርስቲያን ልሳለም ስገባ መስቀል አደባባይ ከቦሌ የሚመጣውን አውራ ጎዳና ተከትሎ በሚገኘው መስቀልኛ መንገድ ላይ አንዲት ድንክዬ ውሻ በአራቱም አቅጣጫ እየተሯሯጠች የትራፊክ ፍሰት ክፉኛ ስታውክ የትራፊክ ፖሊሶችና የፌዴራል ወታደሮች አንዳቸውም ሊነኳት ወይም እውክታዋን ሊያስቆሟት አልደፈሩም፤ እጅግ በጣም ይገርማል፡፡ የዚያን ቀን ማታም ሆነ ከዚያን ዕለት ወዲህ ያ አስገራሚ ክስተት የዜና ሽፋን አልተሰጠውም፡፡ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተገትሬ እንደጉድ እየተመለከትኩ ሳለ ባለመኪኖች ናቸው እየተሳቀቁ በፍሬናቸው ሲጥሲጥታ እየተከላከሉ ሲያልፉ ያየሁት፡፡ ያን የመሰለ እንደሃሊዮ ኮሜት በ76 ዓመታት አንዴ እንኳን የማይገኝ አጋጣሚ ሳያመልጠኝ እንደጅል ቆሜ ለብዙ ደቂቃዎች ተከታተልኩ – (ይቅርታ ጅል አይደለሁም ብዬ ስለማስብ ነው)፡፡ ከግማሽ ሰዓት በላይ ከወሰደብኝ ጸሎቴ ተመልሼ ስወጣም እዚያው ነች – ሥራዋ ቅድም እንደገለጽኩት በአራቱም አቅጣጫ ነፍሱዋን ስታ መራወጥና በተለይ ባለመኪናን ቀልቡን መግፈፍ ነው፡፡ ይህቺ ውሻ ባለቤት የላትም? ባለቤት አይኑራት ግዴለም፡፡ ለበርካታ ሰዓታት እንዲያ ዋናውን የትራፊክ ፍሰት ስታውክ ሃይ የሚላት ሊኖር አይገባም? ደግሞስ በመኪና አትገጭም? የሚያስደንቅ ነገር ነው፡፡

ወያኔም ሆነ በሕዝብ ምርጫ ሥልጣን ላይ የማይወጣ ማንም ሰው በዚህ በጥንቆላ ልክስክስ ሥራ የመታማቱና በኃይል የያዘውን ሥልጣንና ሀብት ለማጽናትም ወደዚያ የነውርና የኃጢያት ሥራ በተግባር ማምራቱ የነበረና ያለ ነው፡፡ ሰይጣን ደግሞ ሞኝ አይደለም፡፡ ቤተ መንግሥቱን የሚያደምቁለትን የሰው ዘር ምዕመናኑን የሚመለምለው እዚሁ መሬት ላይ ነው፡፡ በወዲያኛው ዓለም – ማለትም ከሞት በኋላ ሕይወት መኖሩን – የምታምኑ ሰዎች የምለውን እንደምትረዱ ተስፋ አደርጋለሁ፡፡ ብዙ ሰዎች በተለይ በአሁኑ ዘመን ተስፋ ሲቆርጡና ሰማይ ምድሩ ሲደፋባቸው ምርጫቸው ዛሬን መኖር ብቻ ይሆንና ከዛሬ በኋላ ያለውን ጊዜ ምንተዳዬ ብለው እርግፍ አድርገው ይተዋሉ – በ‹ዛሬ ከምሞት ነገ ልሙት› ዓይነት እንስሳዊ ፍልስፍና በመመራት፡፡ በዚያም ምክንያት የሚሠሩት ነገር ሁሉ በዕለቱ ቁር ላለችዋ ጀምበር ብቻ ሥጋዊ ሕይወታቸውን ያድልበው እንጂ ስለነገ መጨነቅ አይፈልጉም፡፡ ዛሬ በሀብትና በሥልጣን ጫፍ ላይ ይቀመጡ እንጂ እንዴት ወደዚያ ሥፍራ እንደተጓዙና እየቆዬ ደግሞ በምድርም ይሁን በሰማይ ማለትም በቀጣዩ ኅልውናቸው ምን ሊደርስባቸው እንደሚችል ለአፍታም ቢሆን ሊያስቡ አይፈልጉም – ያ ዓይነቱ የጤናማ ሰው አስተሳሰብ የቀን ዕረፍትና የሌት እንቅልፍ ይነሳቸዋልና፡፡ ለዚህ ይመስላል ኢትዮጵያ ውስጥ በአሁኑ ወቅት በተለይ ሩሕን በሳተ የሀብትና የሥልጣን ማግበስበስ ሩጫ ብዙ ሰዎች ከቀናው መንገድ እየወጡ ሕዝብን በሚያስለቅሰው ሰፊው ጎዳና ላይ የሚገኙት፡፡ አንጎል ሲደበቅ እንዲህ ነው፡፡

እውነት ነው ኢሕአዲግ የሥልጡን አሰለጦች ስብስብ ይመስላል፡፡ ግን እንዳይመስላችሁ – ውስጡን ለቄስ ነው፡፡ መለስና ክብርት ባለቤቱ አዜብ አቅላቸውን ስተው በቢሊዮን የሚገመት ሀብትና ንብረት ሊያከማቹ በሥልጣንም ይሄን ሁሉ የኢትዮጵያ ሕዝብ በመተታቸውና በሸፍጠኛ አገዛዛቸው አነሁልለው እስከወዲያኛው በሚመስል አያያዝ ሊገዙ ያቆበቆቡት በዕውቀታቸውና በጥበባቸው ሳይሆን በሌላ ዛሬ በዚህ ጽሑፍ በማነሳው ነገርም ተራዳኢነት ነው፡፡ እኛና ማኀበረ ኢኮኖሚያዊ አወቃቀራችንም ለዚህ ሥራቸው የተመቸን በመሆናችን ይሄውና አብረናቸው እያጨበጨብን ለሃያ ዓመታት ዘለቀን፤ እነሱ እየከበሩ – እኛ ሙልጭ እየወጣን፡፡ እነሱ እያጭበረበሩና እያምታቱን እኛ እየተጭበረበርንና እየተቀለደብን፤ እነሱ በዘርና በቀየ እየተሰባሰቡና የላሚቷን ወተት ለብቻቸው እየተጋቱ እኛ በዘውግና በወንዝ እየተደራጀንና በባዶው እየጮኽን፡፡ ሌላው ሁሉ ይቅርና ‹ባንዲራ ምን ይሠራል – የነፍጠኞች የመግዣ መሣሪያ ነው› እንዳላሉን ሁሉ ማኅደር ክፍል አቧራ ሲጠጣ የቆዬ የፀጋዬ እሸቱን ዓይነት የሰንደቅ ዓላማ ዘፈን እያወጡ ማዘፈንና ሕዝቡን በቁስሉ በኩል ገብተው መቀስቀስ የቻሉበትን ሁኔታ ፈጥረዋል – ለነሱ የሚገዳቸው ነገር የለም፡፡ ሲፈልጉ ያጣሉናል፤ ሲፈልጉም አጣልተውን ሲያበቁ በአስታራቂ ሽማግሌነት መሃል ገብተው ያገላግሉናል፡፡ አልፎ ተርፎም የባንዲራ ቀን እያሉ የማያምኑበትን ሃይማተ ባንዲራ ለይስሙላና ለሥልታዊ ጠቀሜታ መስበክ ከጀመሩ ዋል አደር አሉ፡፡ ቀልዱና ትብተባው ገና ይቀጥላል፡፡ ሊጠነቆልበት የተዘጋጀ ገልቱ ሰው እስካለ ተብታቢ ሞልቷል፡፡ የቅርቡ ደብተራ ቢከሽፍበት ወይም ቢሰንፍ ከሩቅ ካለበት ይመጣል – ገንዘብን ይጭነቀው፡፡ በገዛ ገንዘባችን የመግደያ መሣሪያ ይገዛል፤ ጠንቋይ ይቀለባል፤ ማኀበራዊ ሕይወትን ያላጣጣመ ልጅ እግር፣ በቋንቋም ሆነ በሥነ ልቦና ረገድ ከአብዛኛው ሕዝብ ጋር የማይግባባ ድንጉጥ፣ በአዛዦቹ የሚነገረውን ብቻ የሚፈጽም ግዑዝ ዜጋ ከገጠሩ የሀገራችን ክፍል ይመለመልና ከመተኮስ በስተቀር በይሁንታና ለዓላማ ሲባል አንዳችም ዘመናዊ ትምህርት እንዳይኖረው ተደርጎ በገዳይ ፌዴራል ወታደርነት ይቀጠራል፤ ግንባር ግንባር እዬለዬ የወጣበትን ሕዝብ እንዲመታ ልዩ ሥልጠና በባዕዳን ጭምር ይሰጣል፡፡ እስካሁን ግሩም ነው – እንደአካሄድ፡፡ ይሄንንስ ማን አየበትና? ከምር ግና ይህንን ጉድ ሳያዩ የሞቱ ብፁኣን ናቸው – በጤንነት ካባ የተሸፈነ ዕብደት ሳያገኛቸው በጊዜ ተገላግለዋልና!

የጋዳፊን የትብተባ ታሪክ ሰሞኑን በአልጀዚራና በቢቢሲ ተመልክተናል፡፡ የአዲሱ መንግሥት ተዋጊዎች የጋዳፊን የትውልድ ሥፍራ የሊቢያን አድዋ – ስርጥን ሊይዙ በሚያደርጉት ፍልሚያ ላይ በዐረብ ደባትር የተደገመበትና በሟርት የዐረብኛ ጽሑፍ የተጠቀለለ የእባብ ራስ አግኝተዋል – በአልጀዚራ ዐይተነዋል፤ እነሱ ‹ብላክ ማጂክ› ይሉታል፡፡ የጋዳፊ የድግምትና የጥንቆላ አገዛዝ በማክተሙ ግን ከእንግዲህ ወዲያ ትብታቡ የሚሠራ አይመስልም – ሰንኮፉ እስኪነቀል ግን አዲሱ መንግሥትና አጋዡ ኔቶ ጥቂት መድከማቸው አይቀርም፡፡ የሰይጣንን ኃይል መናቅ አይገባም፡፡ በምድር ትልቅ ሥልጣን እንደተሰጠው መረዳት ከአጉል ጀብደኝነትና ከመዘዙ ያድናል፡፡ ማፍረሻ ግን አለው፡፡ እመለስበታለሁ፡፡

ወያኔዎች ከመግባታቸው ጀምሮ በዚህ የመተትና ጥንቆላ ልክፍት የተመረዙ ናቸው፡፡ በዚህ ረገድ በተለይ የሱዳን ጠንቋዮች ትልቁን ሚና እየተጫወቱላቸው እንደነበርና እንደሆነም እንሰማለን፤ ብዙዎቻችንም እምናምን ይመስለኛል፡፡ ለወያኔዎች የጥንቆላና መተት ስኬት ሲባል በርካታ የሀገራችን አህዮችና ፍየሎች እንዲሁም ሌሎች የቤትና የዱር እንስሳት (ከቀንድም ከጋማም) አልቀዋል፤ ዐይናቸው በጉጠት እየተመነጠቀ ወጥቶ ዕውራን ሆነው በየቤተ መንግሥቱና በየአደባባዮች ተበትነዋል፡፡ ‹ሕዝቡንም እንዲሁ ዐሳውርልን፤ ዐይናቸውን እንዳልገለጡ ቡችሎች አርመስምስልን› ነው የመተቱ ትርጓሜ፡፡ እባካችሁ አንባቢያን ለዛሬ ‹ፋራ› ሁኑልኝና በሚገባ ተገንዘቡኝ፡፡ የኃጢያቱን ቀኖና እኔ ልቀበል – የአሚተኛነቱን ጠንቅም እኔው ልግባበት፡፡ ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ እኔ ላሞኛችሁና ወያኔ መተታምና ደንቃራም መሆኑን እንደልቤ ግን ምንም ሳልዋሽ ልግለጽ፡፡ ለነገሩ ገለጽኩ እኮ፡፡ ምን ቀረኝና?

ሱዳኖች በዓለም የታወቁ ጠንቋዮች አሏቸው፡፡ ጦሳቸው ለኛም ተረፈ፡፡ ለነገሩ እኛም ቀላል አልነበርንም፡፡ የባሰ ሰይጣን ገጠመንና ተሸነፍን መሰለኝ፡፡ መጫኛ የሚያቆሙ የመንዝ ደባትር በሱዳን ሽርጣሞች ተዞረባቸውና ዕጃቸውን ሰጡ፡፡ የሱዳን ጠንቋይ ያሠረውን ሊፈታ የሚችል አንድ ነገር ብቻ ነው፡፡ እመጣበታለሁ፡፡ ከሱዳን ቀጥሎ ወይም ጎን ለጎን ሕንዳውያንም አይቻሉም፡፡ የናይጀሪያና በጥቅሉ የምዕራብ አፍሪካ መታቾችም በቀላሉ የሚታዩ አይደሉም፡፡ ምን አለፋችሁ በየሀገሩና በዬአህጉሩ የተሰገሰገው የዲያሎስ መንጋ ለጥንቆላና ለመተት ቦዝኖ አያውቅም – አፍሪካ ደግሞ የባሰባት የጥንቆላና የሟርት አህጉር ናት፤ እናም በዚህ ምክንያት መቼም የሚያልፍላት አትመስልም፡፡ ‹ላወቀበት› እነሱ ጋር ሄዶ በመሞዳሞድ ከአነስተኛው ቁሳዊ ግብር ከሰንደልና ከሽቱ ጀምሮ የእንስሳትን አልፎ የሩቅ ሰውንና የቅርብ ዘመድን የሰው ጭዳ ተሻግሮ የሚወዱትን የገዛ ልጅንና ሚስትን ወይም ባልን ከመጨረሻው ምዕራፍ በፊት ባለው ምዕራፍ አካትቶ በመጨረሻው መጨረሻ ላይ የራስን ሕይወት እስከመውሰድ ይደርሳል – የአጋንንት ዝምድና፡፡ ኣ! እዚህ ላይ በአብነት ልጠቅሳቸው የሚገቡኝ ስንትና ስንት ተሞክሮዎች ነበሩ – ቦታ ይፈጃሉ እንጂ፡፡ ስለአሟሟት ሲነሳ ከዚህ ዓለም ማለፉ ብቻውን ባልከፋ፡፡ የጥንቆላ መዘዙ ብዙ ነው፡፡ ሰው ሞተ የሚባለው ነፍስና ሥጋው ስለተለያዩ ብቻ አለመሆኑን ልብ አድርጉልኝ፡፡ ሰው ሞተ እሚባለው ክፉ እንደሠራ ነፍሱ ልትድን በማትችልበት ሁኔታ ሲሞት ነው፡፡ ይህ ዓይቱ ሰው በልማዳዊው የአማርኛ ቃል ‹ዐረፈ› አይባልም፡፡ የሚያርፍ ደህና ሰው ሲሞት ነው፡፡ ክፉ ሰው ሲሞት አያርፍም፡፡ ወደዚያም አልገባም፡፡ ለምን ሺህ ዓመት ሲንቀዠቀዥ አይኖርም፡፡ መጀመሪያስ ምን አቀበጠውና ሰፊውን ጎዳና ተቀላቀለ፡፡ ፈጣሪ ምርጫችንን ይጠብቃል ጎበዝ! የመለስን በቦርቃቃ መንገድ የመጓዝ መብትንም እንዲሁ ይጠብቅለታል – ለመመለስ ግን የጊዜ ገደብ የለውም፡፡ ፈጣሪ እንደኔ ምቀኛና አሲድ ባለመሆኑ፡፡

ብዙ መሪዎችና ብዙ ሀብታሞች አስመታቾችና አስጠንቋዮች ናቸው፡፡ ቢቻለን በነሱ አንቅና – ዋጋቸውን ማግኘታቸው አይቀርምና፡፡ እንዲመለሱ ግን እንጸልይላቸው፡፡ በይደር ላስቀመጥኳቸው ጉዳዮች መልስ ልስጥና ሃሳቤን ላጠቃልል፡፡

አንድን የመተት ወይም የጥንቆላ ሥራ የምናሸንፍበት ብልሃት ምንድነው? በእኔ ዕይታ መተትን ለማክሸፍ ወይ እንዳይሠራ ለማድረግ ሁለት አዋጭ መንገዶች ያሉን ይመስለኛል፡፡ አንደኛው ልባዊ ጸሎትና ምህላ ነው፤ ልቦናን ሙሉ በሙሉ ወደፈጣሪ መልሶ ከኃጢያትም ነጽቶ ከአንጀት መለመን፡፡ ሌላኛውና ብዙም የማያዋጣው እሾህን በእሾህ ነቅሶ ለማውጣት መሞከር ነው፡፡ ለኃይለኛም ኃይለኛ አለውና ትንሹ ዲያቢሎስ የጠመጠመውን ትልቁ ዲያቢሎስ እንዲፈታው በማድረግ እዚያው በዚያው እነሱን በነሱ ማሰርና መፍታት ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ዘዴ የጠገበውን የአጋንንት መንጋ በማስወጣት የተራበውን ሌላ የአጋንንት መንጋ ማስገባት ማለት ነው – ደርግ ወጥቶ ወያኔው እንደገባው መሆኑ ነው፡፡ በዚሁ አንቀጽ ውስጥ ከፍ ሲል እንዳልኩት ይሄኛው ዘዴ ብሉያዊ የጥርስ ለጥርስና የዐይን ለዐይን ተካካይ ክፋታዊ የብቀላ መንገድ ነው፡፡ መነሻውም ምድራዊ ሆኖ መድረሻው ገሃነማዊ ሊሆን እንደሚችል መጠርጠር ይቻላል፡፡ ይህ ዓይነቱ ክፉን በክፉ የመቃወም መንገድ ደግሞ ለማንም አይመከርም፡፡

በመጀመሪያው ማለትም በጸሎት ሰይጣናዊ መተትንና የዛር ውላጅ ደንቃራን በማስወገዱ ረገድ በታሳቢነት የሚገቡ ሁለት ያህል ሃይማታዊ ይትበሃሎች አሉ፡፡ አንደኛው ንጹሕ የኀሊና ጸሎት ነው፡፡ ሁለተኛው መጽሐፍ ቅዱሳዊ ድጋፍ ባላገኝበትም በሥርዓታዊ የድጋም ጸሎቶች ሰይጣንን ለማስደንገጥና የተንኮል ዕቅዱን ለማስጨንገፍ መሞከር ነው፡፡ እንደ አባቶች አነጋገር የመዝሙረ ዳዊት 150 ንጉሦች በሦስት ዋና ዋና ክፍሎች ይመደባሉ፤ እነሱም ሃምሳው ለጸሎት፣ ሃምሳው ለመድሐኒትና ሃምሳው ደግሞ ፀላኤ ሠናያትን ለማባረር በአስማተ መለኮትነት የሚያገለግሉ ሆነው በጥንታውያን አባቶች መመደባቸው ነው፡፡ ለምሳሌ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ሃይማኖት ከተቀበለቻቸው የኋለኛ ዘመን መጻሕፍት መካከል ድርሳናትና ገድላት እንዲሁም መልኮችና ውዳሴያተ ጻድቃን ወመላእክት ይገኙባቸዋል፡፡ በነዚህ መጻሕፍት ውስጥ በተለይ በቅዱሣን መላእክቱ ክንፎች ሥር በፈጣሪ ተጽፈው ለመላእክቱ እንደተሰጡ የሚነገሩ ትርጉማቸው ግን ለማንም በተለይ ለሀገራችን ማዕምራን ግልጽ ያልሆኑ ቃላትን እናገኛለን፡፡ ለምሳሌ በድርሣነ ሚካኤል ውስጥ – ‹ኤኮስ አሴዕ …. ፌኤ ወአርናኬ ኤቦካኪሮም…፣ ጸ… ጸ… ጸ… ጸ… ጸ… ጸ… ጸ… › የሚሉና በድጋም መልክ ለፀላኤ ሠናይ ማባረሪያነት እንደሚጠቅሙ የተጠቆሙ የጸሎት አስማት አሉ፡፡ ‹አሃ! አንተስ ዋናው ተብታቢ ደብተራ አይደለህ እንዴ?› ብላችሁ እንዳታሙኝ አደራችሁን – ትኮነናላችሁ፡፡ በጥራዝ ነጠቅ ግንዛቤ ነው እንዲህና እንደቀጣዩም የምላችሁ፡፡ እናም ‹እክህደክ ክርስቶስ› ብለው በክሂዶተ ክርስቶስ ላይ በመመርኮዝና ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተጸዳድተው የፈጣሪን ቤት በማርከስ ለባሕርይ አባታቸው ለሰይጣን ያላቸውን ታማኝነት በማረጋገጥ የለዬለት የአንደርብና የጥላ ወጊ ድግምት ከሚያከናውኑ ደባትር ጎን ለጎን ፈጣሪ ይፍቀደው አይፍቀደው በውል ለይቼ በማላውቀው ሁኔታ ‹እክህደከ ሰይጣን› በሚል መነሻነት ድጋም የሚያደርሱና በጠላት ላይ ጉዳት የሚያደርሱም እንዳሉ ዐውቃለሁ፤ ምሥጢሩን አንድዬ ይወቀው፡፡

ዋናው የተነሣሁበት ጉዳይ ወያኔ ትብታባም መሆንዋን ለመግለጽና ከዚህ ትብታብም ለመውጣት ብርቱ ሁለገብ ትግል ማድረግ እንደሚያስፈልግ ለመጠቆም ነው፡፡ ሰማንያ ሚሊዮን ሕዝብን ማነሁለልና በስማም እንደተባለበት ሰይጣን ማፍዘዝ፣ ተቃዋሚን እንዳለ ማናከስና እዚያና እዚህ እንደቅርጫ ሥጋ መድቦ ገና ባልተገኘ ሥልጣን ማወራከብ በምናባዊ ጦርነትም ማተጋተግ፣ በማከያው የራስን ኅልውና ማደላደል በመለሳዊ ዕውቀትና ‹ጥበብ› የሚቻል ይመስላችኋል? በኔ ይሁንባችሁ በፍጹም! እርግጥ ነው ሌሎች ግብኣቶችም ሞልተዋል፡፡ የምላችሁ የትብታብ ጉዳይ ግን በዋናነት ሊጠቀስ የሚገባው ነው፡፡ ለምን እናፍርበታለን? በዋይት ሀውስና በክሬሚሊን አብያተ መንግሥትም የተለመዱ ናቸው እኮ እንኳንስ በኛ በደናቁርት ገዢዎቻችን ዘንድ፡፡ የኛን ከሌሎቹ የሚያከፋው የጭካኔያችን ደረጃ ነው፡፡ ወያኔ እንዲህ ያለ ነገር አይነካካትም የሚል ሰው ካለም መብቱ ነው፡፡ ይህ እምነቱም ወያኔን በጣም ያስደስታታል፡፡ ደግነቱ ትብታባምነት በተለይ ብዙ ማይማን በሚኖሩበት ሀገር የተለመደና በዚህ በሽታ የመለከፍ አባዜም ከሀገራችን ነባር ‹ዕሤቶች› አንዱ በመሆኑ እስከዚህም የሚያስወቅስ ላይሆን መቻሉ ነው፡፡ ድግምትና ጥንቆላ በብዛት የሚታየው በተለምዶ ሦስተኛው ዓለም በሚል ታርጋ በሚታወቁ ሀገሮች ውስጥ መሆኑ በነዚህ ሀገሮች ውስጥ ለሁለቱም – ለእግዜርና ለሰይጣን – የሚያሸረግደው ዜጋ ቁጥር ከእኩል በእኩልነት የማይተናነስ እንዲያውም ለጨለማው ንጉሥ የሚንበረከከው ብዙ መሆኑን ያመላክታል፡፡ ከመስቀያው የተበላሸ ነገር ደግሞ ከግርጌም የሚበላሽ መሆኑ ይታመናል፡፡ እናም ያላደጉ ሀገሮች ችግር ውስብስብ የሆነበት ምክንያት አንዱ ለዚህ ይመስለኛል፡፡ ጧት ቤተክሲያን፣ ማታ እነአዶከብሬና እነደብተራ ስም አይጠሬ ቤት የመገኘት ዳፋው በሃያ ዓመት ቀርቶ በመቶም አይነቀል፡፡ ስለዚህ አስተሳሰብንና አመለካከትን ወደቀናው ሰውኛ አስተሳሰብና አመለካከት መለወጥ ይገባል፡፡ በዚህ ክፉ መንገድ የሚጓዘውን ብዙውን ሕዝባችንን ነጻ ለማውጣትም መጣር ይገባናል፡፡ ፈተናችን ብዙ፣ትግላችንም ፈርጀ ብዙ መሆኑን መረዳት ይኖርብናል፡፡ ታምራት ገለታን ማሠሩ ጥቅምና ዋጋ የለውም፤ ደግሞስ አሣሪውስ ማን ነውና? በሺዎች የሚቆጠሩ ታምራቶችና አውገረዶች በመላዋ ሀገራችን ተበትነው ሕዝቡን የሚያሰናክሉ ዜጎች አሉ፡፡ በሺዎች የሚቆጠሩ ደብተራዎችና ስኒ ተመልካቾች፣ አባይ ጠንቋዮችና መታቾች አሉን፡፡ ብዙ ጠቃሚ ዜጎቻችን በዚህ መጥፎ ባህል ተመርዘውብን ከልሂቅ እስከ ደቂቅ ለዚያ ለታላቁ ጠላት ሎሌ ሆነውብናል፡፡ ጳጳስ የለ ቀሲስ፣ ዲያቆን የለ አወዳሽ ቁጥሩ የሚያሰደነግጥ ወገናችን በከተማም በገጠርም የዲያቢሎስ ምርኮኛ ሆኗል፡፡ በደጁ ምናምን የማይቀብር ባለሆቴል፣ ደንቃራ የማይጥልና የማያስጥል ባለሀብት፤ የሰው ደም በግብር መልክ የማያፈስ ባለወፍጮ(በተለይ በገጠር)፣ እንዲያሸንፍ አንዱ አበጋር ዘንድ ሄዶ የማያፈነድድ ታዋቂ ሯጭ፣ በድምጹ መረዋነት ሕዝቡን በማማለል ካሤቱን ለመሸጥ ሲል በየደብተራውና በየጠንቋዩ እግር ሥር የማይደፋና የጫት ቱፍታውን እንደዜኒት ቅባት የፊቱን የማይቀባ የሙዚቃ አቀንቃኝ፣ በከራማና በአውሊያ ወዳጃ ወረቱ እንዲበዛለት የማይጎናበስ ነጋዴ፣ መጽሐፍ ሳያስገልጥ ወደፍርድ ቤት የሚሄድ ተሟጋች፣ ሥራ ሥር የማያስበጥስ ባለጠጅ ቤት፣ ጠጠር ወርዋሪና ኮከብ ቆጣሪ ዘንድ ቀርቦ ‹አንተው ቅበረኝ› የማይል የድግምት ተስፈኛ፣ ምናምንዋን ያላስነቀሰች ወይም መስህብ አሸንክታብ ጉያዋ ውስጥ ያልወተፈች ሴተኛ አዳሪ፣ ጠልሰሙን በብብቱ ያላገነደረ ነጋዴ፣ በፓጀሮው፣ በፕራዶው፣ በቪታራው …ና በሐመሩ አርሲ ፈረቀሣና ሌሎች ‹ቅዱሣን› ሥፍራዎች በመሄድ ለ‹ሙታንሳዋ› የአርሲዋ እመቤት ወይም ለ‹ደጋጎቹ መጀን› የማያጎበድድ ዲታ፣ በየጉራንጉሩ በተመሰጉ የውሸትና አንዳንዴም የእውነት ድቤ መቺዎች ቤት እየሄደ ‹መጀን በናንተ› የማይል ህልመኛ እንዳይኖር ለማድረግ ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል – ሰይጣን በሰይጣንነቱ እንዲታወቅ የምፈልግ መሆኔ እንደተጠበቀ ሆኖ አልፎ አልፎ እውነተኛ ጠንቋዮች ሊኖሩ እንደሚችሉ የክሬን መሥከር እፈልጋለሁ፡፡ ከፍ ብዬ ለመግለጽ እንደሞከርኩት ሰይጣን በምድር እርሱን ለሚፈቅዱ ከፈጣሪ ሥልጣን ተሰጥቶታልና፡፡ … በሀገራችን የሚሰማው ጉድ እኮ ግን እጅጉን ይዘገንናል እናንተዬ . . . ብቻ ከእነዚህና እነዚህን ከመሰሉ ጎታች የደንቃራና የሟርት የአመፃ ተግባራት ነጻ የሆኑ ዜጎችን ማግኘት ከባድ እየሆነ እንደመጣ በተለይ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት ዕየተነገረ ይገኛል፡፡ ፈጣሪ በኪነ ጥበቡ ይታደገን እንጂ እንደሥራችንስ ከሆነ እርቦንና ጠምቶን ታርዘንም ቢሆን ውለን ማደራችን የሚገርም ነው፡፡ እኛ መለስን እናማለን፤ መለስ ምን አጠፋ? የማንን ይያዝ? ከማን ማሕፀን ተፈጠረ? እርሱ ለብቻው እንዴት ብፁዕ እንዲሆን እንጠብቃለን? እኛስ የማንን ጎፈሬ እናበጥራለን፡፡ ሁለት ምርጫ አለን ለማንኛውም፡- አንድም እንደርሱው የለየለት ሰይጣን ሆኖ ሀገር ምድሩን የአጋንንት መፈንጪያ ማድረግ፡፡ አንድም ወደየኅሊናችን በመመለስ ወደፈጣሪ ዞረን በትክክለኛው መንገድ መጓዝ፡፡ ያኔ ሰሚ እናገኛለን፡፡ በሁለት ቢላዎ እየቆሸመዱ ግን አውርድልን ወይ ውረድልን ቢሉ አይሆንም፡፡ እኛ በተስተካከልን ማግሥት ሁሉም ነገር እንደሚስተካከል መገንዘብ ይኖርብናል፡፡ በአሁኑ ወቅት የፈጣሪን በረከት ማግኘት የሚያስችለን የብፅዕና ደረጃ ላይ የምንገኝ አይደለንም፡፡ ሁሉም ውጥናችን ዜሮ የሚሆንብን በመለስ ብርታትና በዘረጋው ሥርዓት ጥንካሬ ሳይሆን እያንዳንዳችን በምንሠራው ሥራ ነው፡፡ ቆም ብለን እናስብ፡፡ ሌባ ጣታችንን ቀስረን ሰውን ስናስጠነቅቅ ሦስቱ ጣቶቻችን ወደኛ መዞራቸውን እናስተውልና በቶሎ እንስተካከል፡፡ በፖለቲካው ዙሪያ ብዙና ብዙ ተብሏል፡፡ በዚህ በዛሬው ርዕሰ ጉዳይ ግን ሰዎች በባላገርነት እንዳይፈረጁና መሳቂያና መሳለቂያ እንዳይሆኑ በመሥጋት ይመስለኛል ብዙ ሰው ሲያነሳው አላስተዋልኩም፡፡ ቁልጭ ብሎ የሚታይን ችግር ለመግለጽ መሞከር በባላገርነትም ይሁን በማይምነት ሊያስፈርጅ አይገባም፡፡

የሀገራችንን የወቅቱን ጉዳይ በሚመለከት አሁንም አንድዬ ይወቅ፡፡ ሰው ግን በቁሙ እየተበላላ ነው፡፡ ወዴት እየሄድን እንደሆነ ከመገመት በስተቀር ማወቅ ወደማይቻልበት ደረጃ ደርሰናል፡፡ ይህን አደገኛ አካሄድና የሀገራችንን የበሸቀጠ ሁኔታ በገሃድ መመሥከር ይቻላል፡፡ በተለይ ነጋዴው የገንዘብ ፍቅር እንደጉድ አራዥቶታል፡፡ ገንዘብ ለወዲያኛው ዓለም በስንቅነት የሚያገለግል ይመስል ብዙው ሀብታም አቅሉን ስቶ በማጭበርበርና ከንግድ ሕግ ውጪ ትርፍ በማግበስበስ ድሃውን ሕዝብ እያስጨነቀ ባንኮችንም እያጨናነቀ ነው፡፡ አብዛኛው ሕዝብ ድንቡሎ አጥቶ በርሀብ እያለቀ ነው፡፡ …. ቢበቃኝስ? ቅናት አስመሰለብኝ እኮ ጃል! ኤዲያ – ምን ዓይነት የተረገመች ሀገር ውስጥ ተፈጠርን በእግዚኣብሔር? ሰው አይውጣብሽ ተብላ ተረግማ ይሄውና የዓሣማና የጅብ መንጋ በቤተ አምልኮቶቿና በቤተ መንግሥቷ እንደጉድ ይርመሰመሱባታል፡፡ …