“ልጄ እንደ አባቱ የነፃነት ታጋይ እንዲሆን ነው የምፈልገው”ስትል ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል መግለጿ ተዘገበ

ዘረኛው የወያኔ አገዛዝ በድህረ ምርጫ 97 የቅንጅት መሪዎችን፤ ጋዜጠኞችንና የስብአዊ መብት ተሟጋቾችን እስር ቤት ባጎረበት ወቅት፤ ዳግም ለወያኔ እስር በተዳረገው ባለቤቷ ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ ጋር እስር ቤት እየማቀቀች የተገላገለቺው ህጻን ልጇ እንደ አባቱ የነጻነት ታጋይ እንዲሆን ምኞቷ መሆኑን ጋዜጠኛ ስርካለም ፋሲል አዲስ ጉዳይ በተባለ መጽሄት ላይ ባሳተመቺው ጽሁፍ መግለጿን ለማወቅ ተችሎአል።

ጋዘጠኛ ስርካለም በአመዛኙ ስለ ባለቤቷ እስክንድር ነጋ ማንነት በገለፀችበት በዚህ ፅሁፏ ባለቤቴን ”ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋን ታውቁታላችሁ። ከቅርብ ቀናት ወዲህ የመንግስት ሰዎች እስክንድር የሚባል ጋዜጠኛ አናውቅም ቢሉም እናንተ ግን ታውቁታላችሁ”በማለት ነበር ጽህፏን የጀመረቺው።

ይሁንና “አናውቅህም”ያሉት ወገኖቹም በበሳልና በደፋር ጋዜጠኝነቱ እንደሚያውቁት እርግጠኛ መሆኗን ሰርካለም ተናግራለች።

እስክንድር ለሰባት ጊዜ ፍርድ ቤት ቀርቦ አንድም ጊዜ መረጃ ሳይገኝበት በነፃ መለቀቁን፤ እንዲሁም ምርጫ 97ትን ተከትሎ የቅንጅት ምክር ቤት አባል ነህ ተብሎ ከተመሰረተበት ክስ በነፃ መሰናበቱን ያስታወሰችው ጋዜጠኛ ሰርካለም፤ የእስክንድር ብዕር መነሻውና መድረሻው እውነት ብቻ እንደሆነ አመልክታለች።

ባለቤቱ ከመሆኗ ጀምሮ በብዙ ምክንያቶች ስለ እስክንድር ስብዕና ለመናገር እንደምትቸገር የተናገረችው ሰርካለም፤ ”ይሁንና ስለ እስክንድ ለመናገር ማስረጃ ማሰባሰብ እንደማያሻ፤ የ እስክንድር ጉዳይ ነጻ ለሆኑ ግለሰቦች ቀርቶ በወንጀለኛነቱ ሊዳኘው ላሰፈሰፉው ፍርድ ቤትም ግልፅ የሆነ ነገር መሆኑን ገልፃለች።

“ሆኖም እስክንድር ዕድለኛ አይመስለኝም። የመረጠው መንገድ ለእርሱም ሆነ ለእኛ ለቤተሰቦቹ አደገኛ ነው፤ እነዚህ ሁሉ እስሮች ወቅት እየጠበቁ እንደሚመጡበት ጠንቅቆ ያውቃል” ያለችው ሰርካለም፦ ”በኔ እምነት እስክንድር ያላወቀውና የተታለለበት ጊዜ የሚመስለኝ፤ሃሳብን በነፃነት የመግለፅ መብት በኢትዮጵያ ተከብሯል” ሲባል፤ የተማረባትንና በምቾት የኖረባትን አሜሪካን ትቶ ወደሚወዳት አገሩ ተመልሶ” ኢትኦጲስ”ጋዜጣን ሲጀምር ” መሆኑን ጠቅሳለች።

ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ “ሽብርተኛ” በሚል ስም በመጠራቱ ከልቧ ማዘኗን የጠቀሰችው ሰርካለም፤” ይሁንና “ሽብርተኛ” ያለው በብዕሩ የሚታገልለት የኢትዮጵያ ህዝብ ባለመሆኑ እጽናናለሁ” ብላለች።

ከመታሰሩ ከወራት በፊት የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ቢሮው ድረስ አስጠርቶት “እርምጃ እንወስድብሀለን”ብሎ ዝቶበት እንደነበር ያስታወሰችው ሰርካለም፤ ”እርምጃ እንወስድብሀለን የሚለውን አባባል እስክንድር ህዝብን ላለማስቆጣት በሚል ለዘብ አድርጎ የፃፈው ነው እንጂ፤ ያሉት እንደዛ አይደለም። ያሉትን ለኔ ነግሮኛል። ያን ቃል እስክንድርና ሀላፊው ያውቁታል። ምንም እንኳ እስክንድር ያመነበትን ከመግለፅ ወደ ሁዋላ ባይልም፤ ሀላፊው የተናገረውን ቃል በቃል ያልፃፈው ፈርቶ ወይም ችግር ይፈጠርብኛል ብሎ ሰግቶ አይደለም። ይልቁንም የተባለውን ነገር እንዳለ ቢፅፈው በህዝቦች መካከል አመፅ ሊያስነሳ፤ ዓመፅ ባያስነሳ እንኳ ቂም ይፈጥራል”በሚል ሀሳብ ነው ያልፃፈው ብላለች።

እስክንድርን ለዘብ እንዲል ብታስገድደውም ሆነ ብትለምነው ከዓለማው ልትመልሰው እንደማትችል የገለፀችው ጋዜጠኛ ሰርካለም፤እንኳን አድጎና ትልቅ ሰው ሆኖ በፍቅር ያገኘሁት ሚስቱ ቀርቶ አንድ እሱን ብቻ የወለዱት እናቱም በቻሉት ሁሉ ሲለምኑት፤ ከቤት ሲጠፋባቸው በየጋዜጣ ቢሮዎች እየሄዱ፦ ”ልጆች እስክንድርን አይታችሁታል?” እያሉ ሲያስሱና ደጋግመው ሲማፀኑት መቆየታቸውን፤ ሆኖም ከዓላማው ሊያቆሙ እንዳልቻሉ አስታውሳለች።

“እስክንድር እኔንም፤ እናቱንም ባይሰማ እንኳን እሱ ለእናቱ አንድ እንደሆነ ሁሉ፤ ለእኔና ለእሱ አንድ የሆነውን የ 5 ዓመት ህፃን ልጁ ናፍቆት በደመ-ነፍስ መማፀኑ ሊሰማው ይገባ ነበር” ያለችው ጋዜጠኛ ሰርካለም፤ በመንፈሱ፦ ”አባባ፤ ለምን እንደ ሰው ሁሉ እርፍ ብለህ ተቀምጠህ አታሳድገኝም?” እንደሚለው ማሰቡ አልቀረም። ይህ ስለሚሰማውም ይመስለኛል የ 5 ዓመት ልጁን አቅፎ እያሻሸው ልክ እንደ ትልቅ ሰው ሲያናግረው እሰማ ነበር”ብላለች።

በተደጋጋሚ፦ “ናፍቆቴ እወድሀለሁ፤ ደግሞ ታሳዝነኛለህ። እንደ አባት ከጎንህ ሆኜ ባሳድግህ ደስ ይለኛል፤ ግን ላሳድግህ የምችል አይመስለኝም…” እያለ ሲያወራው እሰማለሁ ያለችው ሰርካለም፤”ህፃኑ አባቱ ያለው ምን ማለት እንደሆነ ቢገባው፤ ምን ይሰማው ይሆን?” በማለት “እንኳንም አልገባው” ብላለች።

ሰርካለም እንደምትለው፦ እስክንድር ልጁን በሰላም እንደማያሳድገው ያውቅ ነበር፤ ምክንያት፦ ለእስክንድር የሀገሩ ነገርና የህዝቦቿ ነፃነት ጉዳይ ከልጁም በላይ ዋጋ ያላቸው ናቸው።

“ናፍቆት አድጎ ትልቅ ሰው ሲሆን ያኔም ይህች አገር እንዲሁ ከሆነች፤ ታጋይ እንደሚሆን አምናለሁ” ያለችው ጋዜጠኛ ሰርካለም፤” እስክንድር አስመሳይና የተገኘውን በልቶ የሚያድር ልጅ እንዲኖረው አልመኝለትም። እስክንድር በመረጠው መንገድ ሳቢያ ምንም የስቃዩ ሰለባ ብሆንም፤ እሱን የማይተካ ልጂ እንዲኖረው አልመኝለትም” ብላለች።

የተወለደ ልጅ ነው። አሁን ደግሞ በ 5 ዓመቱ አባቱ በፖሊሶች ተከቦ በካቴና ሲታሰርና ሲንገላታ አይቷል። አባቱ- እሱ ወደተወለደበት ወህኒ ቤት መግባቱንም እያየ ነው። ማንበብ ሲችል፤ እነዚህን የሚፃፉትን ፅሁፎች ሁሉ ያነባል። ያኔ አባቱ በህይወት ባይኖርም፤ አለያም እስር ቤት ቢኖርም አለያም ከእስር ተፈትቶ አብሮት ቢኖርም፤ የማን ልጅ እንደሆነ ያውቃል። ከዚህ ልጅ ምን ይጠበቃል?”ስትልም አክላለች-ጋዜጠኛ ሰርካለም ፋሲል።

ሰርካለም አያይዛም፦ ”አባቱን በካቴና አስረው ቪዲዮ ሲቀርፁትና ፎቶ ሲያነሱት፤ ህፃኑ “አባቴን” እያለ መሬት ላይ ወድቆ እየተንከባለለ ያለቅስ ነበር።ያኔ ፖሊሶቹ ገለል ሊያደርጉት ሲገባ፤ አብረው ቪዲዮ ይቀርፁታል። ይህ ዘግናኝ ድርጊት ለየትኛው ሁኔታ መረጃ እንደሚሆን እነሱ ናቸው የሚያውቁት” ብላለች።

እስክንድርን ከዓላማው የምትጎትተው ሰው ባትሆንም፤አንዳንድ ጊዜ ፦ ”አረ እባክሽ ተው በይው!” የሚል ጉትጎታ ሲበዛባትና እግር እግሩን የሚከታተሉት ደህንነቶች አላስኬድ አላስቀምጠው ማለታቸው ሲበዛ ፦ ”እስቲ ለእነሱም እረፍት ስጣቸው፤ አንተም አረፍ በል”ስትለው፤ “አንቺም እንደዚህ ትይኛለሽ? ታዲያ አንቺ እንደዚህ ካልሽን፤ ሌላ ማን አለኝ?” ይላት እንደነበርም ሰርካለም አውስታለች።

“ይህን የምለው ሚስቱ ስለሆንኩና አንድ ልጃችን ስለሚያሳዝነኝ እንጂ፤ዓላማውን ሳልደግፍና ሳልኮራበት ቀርቼ አይደለም”ያለችው ሰርካለም፤” እስሩን፣ ስጋቱንና ፍርሀቱን ለምጀዋለሁ። እስክንድር ከእንግዲህ በሁዋላ ከእስር ቤት ቢወጣ እንኳ፤ ራስ ወዳድ፣ ያየውን እንዳላየ የሚሆን፣ፈሪና ልምጥምጥ እንዲሆን አልፈልግም፤ እኔ ብፈልግ እንኳ እንደማይሆን ስላወቅኩትም ይሆናል ይህን ያልኩት”ብላለች።

ሰርካለም ፅሁፏን ስትቋጭም፡_ የእውነት፣ የፍትህና የነፃነት ጉዳይ እስክንድር ትልቅ ዋጋ ያላቸው ነገሮች ናቸው። ብዙ የተንገላታባቸውና ሁለት መልክ ያወጣባቸው ቁም ነገሮች ናቸው። ጠ/ሚ/ር መለስ የዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን አቋርጠው ጫካ ገብተው እንደታገሉት ሁሉ፤ እስክንድርም ያጣውን አጥቶ ከደረሰበት በላይ መከራ ቢደርስበትም እንኳ፤ እንዳይታገል ማድረግ አይቻልም። የአቶ መለስና የእስክንድር የትግል ስልቶች የሚለያዩት፤ እርሳቸውና አጋሮቻቸው ጠመንጃ አንስተው መዋጋታቸውና እስክንድር ደግሞ ፍፁም ሰላማዊ የሆነውን ትግል መምረጡ ነው” ብላለች።