የፍኖት ርእስ አንቀጽ – ፀረ-ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ከሰማይ የወረደ የተቀናቃኝ ማጥቂያ መሣሪያ ነዉ !

ሽብርተኝነት ከ20ኛው ክፍለ ዘመን ሁለተኛው አጋማሽ ጀምሮ እየጎላ የመጣ አደገኛ ክስተት ነው፡፡ አደገኛነቱ በግልጽ የታየው እ.ኤ.አ መስከረም 11 ቀን 2001 ዓ.ም በኒውዮርክ ከተማ የንግድ ማዕከል ላይ በደረሰው ጥቃት ነው፡፡ በዚህ ጥቃት በሺዎች የሚቆጠር ህይወት ጠፍቷል፡፡ በቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሟል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዓለም ሕዝብ ላይ ይህ ነው የማይባል ድንጋጤና የመንፈስ ጭንቀት ፈጥሯል፡፡

ተንታኞች ሽብርተኝነትን በተለያየ መንገድ ገልጸውታል፡፡ የሥልጣኔዎች ግጭት ውጤት ነው ብለውታል፡፡ የምዕራቡ ሥልጣኔ በምሥራቅ ሥልጣኔ ላይ በአሳደረው መንፈሳዊ፣ ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ ጥቃት ምክንያት ብሶት የወለደው ነው ብለውታል፡፡ በአንድ በኩል የራስን እምነት፣ የራስን ፍላጎት በሌላው ላይ በግድም ሆነ በውድ ለመጫን ከመፈለግ የሚመነጭ አምባገነናዊና አረመኔአዊ ድርጊት ነው ብለውታል፡፡ በሌላ በኩል የተነፈገ መብትን ለማስመለስ የሚጠቀሙበት የትግል መሣሪያ ነው የሚሉም አሉ፡፡

የሽብርተኝነት ጥቃት ዋና ኢላማዎች የምዕራቡን ዓለም ይወክላሉ የተባሉ ታላላቆቹና የለሙት አገሮች ናቸው፡፡ ለምሳሌ አሜሪካ፣ እንግሊዝና ከእነዚህ አገሮች ጋር የቅርብ ንኪኪ አላቸው የተባሉ አገሮች የሽብርተኝነት ሰለባ ሆነዋል፡፡ የሽብርተኝነት ዋና ሰለባዎች የለሙና የክርስትና ዕምነት ተከታይ የምዕራብ አገሮች ይሁኑ እንጂ ሌሎችም አገሮች በተለያየ ምክንያት በተለያየ ደረጃ የሽብርተኝነት ሰለባ ሆነዋል፡፡

የሽብርተኝነት ተጠቂ የሆኑ የምዕራብ ሀገሮች ሽብርተኝነትን ለመቋቋም የተለያዩ ርምጃዎችን ወስደዋል፤ በመውሰድ ላይም ናቸው፡፡ ለምሳሌ በአሜሪካ አስተባባሪነትና በሰሜን አትላንቲክ ስምምነት ድርጅት (NATO) ጃንጥላ ሥር ተሰባስቡ ሌሎች አገሮች የሽብርተኝነት ምንጭ ነህ ብለው በፈረጁት አገርና አካባቢ ሄደው የማጥቃትም ይባል የመከላከል ጦርነት ከፍተዋል፡፡ ከዚያም በተጨማሪ እነዚያ የ “ኔቶ” ሃገራት የፀረ -ሽብርተኝነት ጦርነታቸውን ለማሳካት እንዲያግዛቸው ከሌሎች በርካታ አገሮች ጋር የፀረ -ሽብርተኝነት ቃልኪዳን ተገባብተዋል፡፡ ሁለንተናዊ አቅማቸውን በማስተባበር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ተስማምተዋል፡፡ ከአሜሪካ ጋር በመተባበር ሽብርተኝነትን በጋራ ለመዋጋት ከተስማሙት ሀገሮች አንዷ ሃገራችን ኢትዮጵያ ናት፡፡

እነዚህ የሽብርተኝነት ሰለባ የሆኑ አገሮች የወሰዱት ሌላው ርምጃ ሽብርተኝነትን ለመከላከል የሚረዳቸውን ልዩ የፀረ -ሽብርተኝነት ሕግ ማውጣት ነው፡፡ የዛሬው ትኩረትታችንም እዚህ ላይ ነው፡፡ ሕግን በተመለከተ ሁለት አስተሳሰቦች አሉ፡፡ አንደኛው አስተሳሰብ ሽብርተኝነትን አገሩ በአለው መደበኛ ሕግ መከላከል ይቻላል፤ ስለዚህ ሌላ የተለየ ሕግ ማውጣት አያስፈልግም የሚል ነው፡፡ ሁለተኛው አመለካከት ሽብርተኝነት ከዚህ በፊት ከተለመዱት ተራ ወንጀሎች የተለየ ባህሪ ስላለውና የተለየ አካሄድ፣ አያያዝና አሠራር ስለሚጠይቅ ልዩ ሕግ ያስፈልገዋል የሚል ነው፡፡ ለማንኛው ሁለተኛውን አመለካከት በመከተል የፀረ -ሽብር ሕግ ያወጡ በርካታ አገሮች አሉ፡፡

ዴሞክራሲ በሰፈነበትና ዴሞክራሲያዊ ሥርዓቱ አደጋ ላይ እንደይወድቅ እንደቆቅ ነቅተው የሚጠብቁ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም የነቃ ሕዝብ በአለበት፤ የመከላከያና የደህንነት ኃይሎች የገለልተኛና የዓለም አቀፍ ሰብአዊ ሕግ የዘለቃቸው በሆኑበት ሁኔታ የፀረ -ሽብርተኝነት ሕግ መውጣት ብዙም አያሰጋም፡፡ የተሳሳተ ርምጃ እንኳን ቢወሰድ ነፃነቱ፣ የሙያ ብቃቱና ገለልተኝነቱ ያለው የፍርድ ሥርዓት ርቆ ሳይሄድና ጉዳት ሳይደርስ ያስተካክለዋል፡፡

ፀረ -ሽብርተኝነት ሕግ አደገኛ የሚሆነው በአምባገነን ሥርዓቶች በሚመሩ አገሮች ውስጥ ነው፡፡ በዳበረ የዴሞክራሲ ሥርዓት በሚመሩ አገሮች ፀረ -ሽብርተኝነት ሕጉ የሚያተኩረው የውጭ አደጋን በመከላከል ላይ ነው፡፡ ከሥርዓቱ አሳታፊነትና ፍትሐዊነት የተነሳ በዘላቂነት የሚፈራ አደገኛ የውስጥ ጠላት የሚሉት ኃይል አይኖራቸውም፡፡ ስለዚህ ሕጉ ሲወጣ የዜጎቻቸው ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች ያለአግባብ እንዳይነኩ ከፍተኛ ጥንቃቄ ያደርጋሉ፡፡ በአምባገነን ሥርዓት በሚመሩ አገሮችን ግን አምባገነኖቹ ኃይሎች የውጭ ብቻ ሳይሆን የውስጥ ጠላትም እንዳላቸው ያምናሉ፡፡ በሕጋዊ መንገድ ተመዝግበው ሕጋዊ እንቅስቃሴ የሚያደርጉ ተቃዋሚ ፓርቲዎችንና ነፃ ጋዜጦችን የሚያይዋቸው እንደጠላት ነው፡፡ ማንኛውም ቆንጠጥ የሚያደርግ ትችት እንደ ጠላትነት መግለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፤ ለአደጋም ያጋልጣል፡፡ ስለዚህ አዋጁን የሚያወጡት የውጭ ጠላትን ብቻ ሳይሆን የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውንም ለማጥቃት በሚያመቻቸው መልክ ነው፡፡ አምባገነን መሪዎች የሚቀርፁት ሕግ ለደህነትና ለፖሊስ ከሞላ ጎደል ያልተገደበ የመያዝ፣ የመፈተሸ፤ የማሰር ሥልጣን ይሰጣል፡፡ አንቀጾች ለገዢዎች በሚያመች መልክ ለመተርጎም እንዲያመቹ አሻሚ ባህሪ የሰጣቸዋል፡፡ አንድ ድርጊት የሚያስቀጣ ወይም የማያስቀጣ መሆኑ በእርግጠኝነት አይታወቅም፡፡ ስለዚህ ፓርቲዎች፣ ጋዜጦች ሕዝቡ በአጠቃላይ ዘወትር በስጋት ላይ ይሆናሉ፡፡ የፍርድ ሥርዓቱ በቁጥጥራቸው ሥር ስለሆነ የተፈለገውን የርምጃ ትዕዛዝ ለመስጠት ወይም ሥርዓቱ በሚፈልገው መንገድ ለመፍረድ ታዛዥ ይሆናል፡፡

ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ሁለት ጥቅም ያስገኝላቸዋል፡፡ አንደኛ በፀረ- ሽብርተኝነት ስም ከምዕራባውያን ኃያላን ጎን በአጋርነት በመቆማቸው በጥሬ ገንዘብም ሆነ በዓይነት (ለምሳሌ በመሣሪያ፣ በፖለቲካ ድጋፍ) ዳጎስ ያለ ጥቅም ያገኛሉ፡፡ ሁለተኛ ሽብርተኝነትን በመዋጋት ስም የሚያወጡት ሕግ የውስጥ የሥልጣን ተቀናቃኞቻቸውን ለማጥቃት የሚያስችላቸውን ሕጋዊ ሽፋን ይሰጣቸዋል፡፡ ስለዚህ ነው ፀረ -ሽብርተኝነት ለአምባገነኖች ከሰማይ የወረደ የተቀናቃኝ ማጥቂያ መሣሪያ ነው የምንለው፡፡

ሽብርተኝነትን በጽናትና በቁርጠኝነት እንቃወማለን፤ እናወግዛለን፡፡ በፀረ -ሽብርተኝነት ሽፋን ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን የሚሰጥ አገዛዝንም በተመሳሳይ ጽናትና ቁርጠኝነት እንቃወማለን፤ እናወግዛለን፡፡

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።

የፍኖት እትም ዘጠን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ
.pdf