ፍኖት – የአንድነት ፓርቲ ለመለስ ዜናዊ የጻፈዉ ደብዳቤ

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት)
UNITY FOR DEMOCRACY AND JUSTICE PARTY(UDJ)
ቁጥር፡-አንድነት /437/2ዐዐ4
ቀን 15/01/2004 ዓም
ግልጽ ደብዳቤ
ለኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት ጠ/ሚኒስትር መለስ ዜናዊ
አዲስ አበባ

ጉዳዩ፡- በሽብርተኝነት ስም የታሰሩ አባሎቻችንና ሌሎች ዜጎች ሕገ-መንግሥታዊ መብታቸው እንዲከበርላቸው ስለመጠየቅ፣

በኢትዮጵያ ሕዝብ ዘንድ በግልጽ እንደሚታወቀው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በሕገ-መንግሥቱ በተደነገገው የመደራጀት መብት መሠረት ሕጋዊና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እውን መሆን፣ ለሕገ-መንግሥታዊነትና ለሕግ የበላይነት በጽናት ለመታገል የተቋቋመ የፖለቲካ ፓርቲ ነው፡፡

አንድነት ከሠላማዊ የትግል ስልት ውጭ በሀገራችን ዘላቂ ልማትም ሆነ የተረጋጋ የፖለቲካ ሥርዓት ማስፈን እንደማይቻል ያምናል፡፡ አሁን ባለው አስቸጋሪ የፖለቲካ ምህዳር ውስጥ እንኳ ሠላማዊ ትግል ብቸኛው አማራጭ መንገድ መሆኑን እምነታችን ነው፡፡ አባሎቻችንም ለትግሉ መርሆዎችና ዓላማዎች ተገዢዎች መሆናቸውን እናውቃለን፡፡

ከነዚህ ዓላማዎችና መሠረታዊ እምነቶች በመነሳት አንድነት ሽብርተኝነትን አጥብቆ ያወግዛል፡፡ ሽብርተኝነት የንፁሀንን ህይወት የሚቀጥፍ፣ የሀገርንና የሕዝብን ሀብትና ንብረት የሚያወድም፣ የሀገር ልማትና መረጋጋትን የሚያናጋ ድርጊት በመሆኑ ይህን አስከፊ አደጋ ከመቃወም ባለፈ ለመከላከል በጽናት እንቆማለን፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በፀረ-ሽብርተኝነት ስም ሕግን የሚጥስና በሕዝብ ዘንድ ሽብርና ፍርሀት የሚያሰርጽ ሥርዓትን በጽናት እንቃወማለን፡፡

አሁን በሀገራችን ባለው ሁኔታ መንግሥት በሽብርተኝነት ስም እየወሰደ ያለው እርምጃ ሽብርተኝነትን ከሕዝብ ጋር ሆኖ ከመከላከል ይልቅ በዜጎች ላይ የሚፈጥረው የሽብር፣ የፍርሀትና የመሸማቀቅ ድባብ፣ የበለጠ አመዝኖ ይገኛል፡፡ እየተወሰደ ያለው እርምጃ የፖለቲካ ምህዳሩን ይበልጥ የሚያጠብ፣ ከሕዝብ ጋር መቃቃርን የሚፈጥርና ሽብርተኝነትን ከመቆጣጠር ይልቅ የሕዝብንና የፖለቲከኞችን እንቅስቃሴ ለመቆጣጠር ያለመ ነው የሚል እምነት አለን፡፡

በቅርቡ በተከታታይ በሽብርተኝነት ስም በርካታ ዜጎች መታሠራቸው የሚታወቅ ሲሆን ባለፉት ሳምንታትም የፓርቲያችን ም/ሊቀመንበና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት አቶ አንዱዓለም አራጌ፣ የኦፌዴን ም/ሊቀመንበር የሆኑት አቶ በቀለ ገርባ፣ የኦሕኮ የጽ/ቤት ኃላፊ የሆኑት አቶ ኦልባና ሌሊሳ፣ የመኢዴፓ ዋና ፀሐፊ የሆኑት አቶ ዘመኑ ሞላ፣ እንዲሁም የፓርቲያችን ብሔራዊ ምክር ቤት አባላት የሆኑነት አቶ ናትናኤል መኮንን እና አቶ አሳምነው ብርሃኑ፣ ታዋቂው ጋዜጠኛ እስክንድር ነጋ፣ ጋዜጠኛ ውብሸት ታዬ፣ ጋዜጠኛ ርዕዮት ዓለሙ፣ ጋዜጠኛ ስለሺ ሐጎስ እንዲሁም አርቲስት ደበበ እሸቱ መታሠራቸው ይታወቃል፡፡ አንድነት ፓርቲ በሕገ-መንግሥታዊነትና በሕግ የበላይነት የሚያምን ፓርቲ እንደመሆኑ መጠን ሰዎች በወንጀል ለምን ተጠረጠሩ የሚል ጥያቄ ባይኖረውም ዜጎችን በገፍ ማሰር ለችግሩ መፍትሔ ይሆናል የሚል እምነት የለውም፡፡ ከዚህም ባሻገር በመንግሥት የሚወሰዱ እርምጃዎች ሥርዓትን የተከተሉና ሕጋዊነትን የተላበሱ መሆን ይገባቸዋል፡፡ በሽብርተኝነት ስም በአባሎቻችንም ሆነ በሌሎች ዜጎች ላይ እየተወሰዱ ያሉት እርምጃዎች የዜጎችን ሕገ-መንግሥታዊ መብቶች የሚጋፉና የሚጥሱ በመሆናቸው፡-

ሀ) ሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች በአስቸኳይ እንዲፈቱ፤

ለ) በጥርጣሬ የተያዙት ሰዎች በፍ/ቤት ውሳኔ እስኪያገኙ ድረስ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 19/6 መሠረት የዋስትና መብታቸው እንዲከበርላቸው ፤

ሐ) የሁሉም የፖለቲካና የህሊና እስረኞች ሰብዓዊ-መብት መከበሩ የሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 21 በጥበቃ ሥር ያሉ ሰዎች ከትዳር ጓደኞቻቸው፣ ከቅርብ ዘመዶቻቸው፣ ከጓደኞቻቸው፣ ከኃይማኖት አማካሪዎቻቸው፣ ከሐኪሞቻቸው እና ከሕግ አማካሪዎቻቸው ጋር የመገናኘትና የመጎብኘት መብታቸውን ጨምሮ በአስቸኳይ እንዲከበር፤

መ) በ‹‹ፀረ-ሽብርተኝነት›› ሕግ ስም የሚደረገው የሕዝብ መብት ረገጣና እስራት በአስቸኳይ እንዲቆም፤

ሠ) ህዝብን አፍኖ ለመግዛት ታስቦ የተዘጋጀው ‹‹ የፀረ-ሽብርተኝነት›› አዋጅ ከበርካታ የሕገ-መንግሥቱ አንቀፆች ጋር
የሚጋጭ በመሆኑ ጊዜ ሳይሰጠው እንዲሻሻል፤
ረ) በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 2ዐ/3 መሠረት ማንኛውም ዜጋ በወንጀል ተጠርጥሮ እስካልተፈረደበት ድረስ እንደወንጀለኛ ያለመታየት ሕገ-መንግሥታዊ መብት እንዳለው ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የመንግሥት የመገናኛ ብዙሃን ፍርድ ባልተሰጠባቸው ዜጎች ላይ እንደተፈረደባቸው ወንጀለኞች በመቁጠር የሚያሰራጩትን የሀሰት ፕሮፓጋንዳ በአስቸኳይ እንዲያቆሙ እንዲደረግ፤

ሰ) በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 26 ንዑስ አንቀጽ 2 በተደነገገው መሠረት የዜጎች የግል ሕይወት መከበርና የመጠበቅ መብት በተለይም፤ ማንኛውም ሰው በግል የሚጽፋቸውና የሚፃፃፋቸው ደብዳቤዎች እንዲሁም በቴሌፎን፣ በቴሌ ኮሙኒኬሽን እና በሌሎች በኤሌክትሮኒክስ መሣሪያዎች የሚያደርጓቸው ግንኙነቶች ያለመደፈር መብት እንዲከበር፤ እንዲሁም፤

ሸ) በህገ-መንግሥቱ አንቀጽ 29 በተደነገገው መሠረት የዜጎች የአመለካከትና ሀሳብን በነፃ የመያዝ መብት እንዲከበሩ እንጠይቃለን፡፡

ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር መንግሥትዎ ለእነዚህ ጥያቄዎች የሚሰጠው መልስ ለሀገራችን ሁለንተናዊ ሠላምና መረጋጋት ትልቅ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው እናምናለን፡፡ በመሆኑም የጥያቄዎቻችንን ተፈፃሚነት በቀናነት ተመልክተውና ከየትኛውም ሀገራዊ ጉዳይ ቅድሚያ ሠጥተው እንዲያረጋግጡልን በኢትዮጵያዊ አክብሮት እንጠይቃለን፡፡

ከሠላምታ ጋር

ነጋሶ ጊዳዳ (ዶ/ር)
ሊቀመንበር

ግልባጭ
– ለኢፌዲሪ ፕሬዚዳንት
– ለኢፌዲሪ የሕ/ተወካዮች ም/ቤት
– ለኢትዮጵያ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ
– ለኢፌዲሪ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን
– ለመድረክና ለመድረክ አባል ድርጅቶች
– ለሌሎች የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ሁሉ
– ለሁሉም የፕሬስና የኤሌክትሮኒክስ ሚዲያዎች
– ለሰብአዊ መብት ተከራካሪ ድርጅቶች ሁሉ
– ለዓለም አቀፍ የቀይ መስቀል ማህበር

ሕወሃት ኢሕአዴግ ኢቲቪን፣ ራዲዮዉን በሙሉ ሕገ ወጥ በሆነ መንገድ አፍኖ ይዟል። የአንድነት ፓርቲ በፍኖት ጋዜጣ ሕዝቡን ለመድረስ፣ ለማስተማር እየሞከረ ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማሳተም፣ በአገሪቷ ክፍሎች በስፋት ለማሰራጨት የገንዘብ አቅም ይጠይቃል።፡ለዚህ ኢትዮጵያዊ አላማ የድርሻዎትን ይወጡ ዘንድ አገራዊ ጥሪ እናቀርባለን። በገንዘብዎት አገር ቤት የሚደረገዉን ትግል ይርዱ።

የፍኖት እትም ዘጠን ሙሉዉን ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ