አዉራምባ- የታሰሩ ጋዜጠኞች በዓለምአቀፍ ጋዜጠኞች ፌደሬሽን ልኡካን እንዲጎበኙ መንግስት ፈቀደ፤ የሲፒጄ ልኡካን አልተፈቀደላቸውም
ከሽብር እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው የታሰሩትን ጋዜጠኞች ሁኔታ ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን (IFJ) ተወካዮች በአካል ተገኝተው እንደጎበኙ የኢትዮጵያ መንግስት መፍቀዱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ የጋዜጠኞች ህብረት (ኢብጋህ) አስታወቀ።
ዋና ጽህፈት ቤቱ በቤልጂየም ብራሰልስ ያደረገው ይኸው ፌዴሬሽን ልኡካኑን ወደ ኢትዮጵያ የሚልክበት ዋንኛ ዓላማ ከሽብርተኝነት እንቅስቃሴ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው በፖሊስ ቁጥጥር ስር የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና አውሮፓውያን ጋዜጠኞች የሚደረግላቸውን አያያዝና የታሰሩበትን ትክክለኛ ምክንያት ማጣራት ሲሆን፣ ተወካዮቹ እስረኞቹንም ጭምር አግኝተው ሊያነጋግሩ እንደሚችሉ መንግስት ፈቃደኝነቱን አሳይቷል።
በጉብኝቱ ወቅት በሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ያለውን አጠቃላይ ድባብ ለመገንዘብ እንዲረዳ አንዳንድ የመገናኛ ብዙሀን ተቋማትንና ጋዜጠኞችን፣ የእስረኞችን ቤተሰቦች እንዲሁም የህግ ባለሙያዎችንና የመሳሰሉትንም ማነጋገር እንዲችሉ ኢብጋህ የማስተባበር ሥራ እየሰራ እንደሚገኝና አቅም በቻለ መጠንም በጉዳዩ ላይ ውሳኔ ለመስጠት የሚችሉ የመንግስት ባለስልጣናትም ከተወካዮቹ ጋር ተገናኝተው እንዲወያዩም ለማድረግ እቅድ መያዙን ለዝግጅት ክፍላችን በላከው መግለጫ ጠቁሟል፡፡
በቅርቡ ከሽብር ተግባራት ጋር በተያያዘ ፖሊስ የጠረጠራቸውን ሰዎች በሚያስርበት ጊዜ ጋዜጠኞችም ጭምር ለእስር መዳረጋቸው በተቀሩት ጋዜጠኞች ዘንድ ሥጋትን የፈጠረ ሲሆን፣ የብሔራዊ ጋዜጠኞች ህብረትም የጉዳዩን አሳሳቢነት ከግምት ውስጥ በማስገባት ለጉዳዩ የማያዳግም እልባት ለመስጠት እንዲቻል ከሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ጋር ተባብሮ በመስራት ላይ እንደሚገኝ በላከው መግለጫአስታውቋል።
‹‹ከ1997 ዓ.ም ወዲህ በኢትዮጵያ መንግስት ላይ የተለሳለሰ አቋም ይዟል፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ጋዜጠኞች ሲታሰሩና የፕሬስ ነጻነት አደጋ ላይ ሲወድቅ ምንም አይነት መግለጫ ከመስጠት ተቆጥቧል›› ተብሎ ሲተች የቆየው ‹‹ዓለም አቀፍ የጋዜጠኞች ፌዴሬሽን›› ተወካዮቹ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጡ ቢፈቀድላቸውም፣ በጋዜጠኞች ላይ በሚደርሰው እንግልትና እስር የተነሳ መንግስትን በፅኑ የሚተቹ የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋች ተቋማት በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ሁኔታ ለማየት እንዲፈቀድላቸው ያቀረቡት ጥያቄ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
‹‹ሲፒጄ›› የተሰኘው የጋዜጠኞች መብቶች ተሟጋች ቡድን የምስራቅ አፍሪካ ተጠሪ ቶም ሩድስ፣ የቡድኑ ወኪሎች ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ መከልከላቸውን ለአውራምባ ታይምስ አረጋግጠዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪ፣ በኢትዮጵያ ያለውን አጠቃላይ የፖለቲካና የሰብዐዊ መብት አያያዝ ለማጥናት ከመንግስት ፈቃድ አግኝተው ወደ ኢትዮጵያ ገብተው የነበሩት የአምንስቲ ኢንተርናሽናል ወኪሎች ጥናታቸውን ሳያካሂዱ መባረራቸው ይታወሳል፡፡
የቡድኑ አባላት በመንግስት የተባረሩበትን ምክንያት ‹‹ስላለው ሁኔታ የመንግስት ባለስልጣናትን ካነጋገርን በኋላ የታሰሩ ጋዜጠኞች ቤተሰቦችንና ተቃዋሚ ፖለቲከኞችን ማነጋገር በመጀመራችን ነው›› በማለት ገልፀው ነበር፡
ከቡድኑ አባላት መባረር ባሻገር፣ ለቡድኑ መረጃ የሰጡ የመድረክ አመራሮችም መታሰራቸው የሚታወስ ነው፡፡
የአለም አቀፍ ጋዜጠኞች ፌዴሬሽን ልኡካን ከአንድ አመት በፊትም ወደ ኢትዮጵያ በመምጣት የሲሚንቶ ፋብሪካዎችንና ሌሎች መሰል የመሰረተ ልማት ተቋማትን ጎብኝተው መመለሳቸው ይታወሳል፡፡
ይህ ጽሁፍ ከአውራምባ ታይምስ 4ኛ ዓመት ቁጥር 186 የተወሰደ ነው!