ሁላችንም አንዱዓለም አራጌዎች ነን!!!
ዛሬ የምንገኝበት እውነታን አቶ አንዱዓለም አራጌ በመለስ ዜናዊ ችሎት በተናገራቸው ሁለት ዓረፍተ ነገሮች አጠቃሎታል፤ እንዲህ በማለት።
ለመጀመርያና ለመጨረሻ ጊዜ የምለው አለኝ፤ በኢትዮጵያ የተያዘው ነገር የፖለቲካ ተቃውሞ አፈና ስለሆነ ፍርድ ቤቱ እስከ ሞት ድረስ መወሰን ይችላል፡፡ ከዚህ በኋላ ምንም ነገር አልናገርም።
በመለስ ዜናዊ ዘረኛና አፋኝ ህግ መሠረት ህጋዊና ሰላማዊ ትግል በሽብርተኝነት ያስከስሳል። አቶ አንዱዓለም እንዳለውም ለዚህ ችሎት ሃቅን መናገር ፋይዳ የለውም። ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ እንደታየው በችሎት ላይ የተቀመጡ “ዳኞች” እንደማንኛውም ሰው “ለፍ/ቤቱ” ውሳኔዎች እንግዶች ናቸው። ስለሆነም ችሎቱ ላይ ለተቀመጡ ግዑዛን ፍጥረቶች ማብራሪያ መስጠት – ሰሙም አልሰሙም – በሚያነቡት ውሳኔ ላይ የሚያመጣው ለውጥ የለም። በዚሁ ሁሉ ምክንያት እችሎት ተብዬው ውስጥ መከራከር ዋጋ የለውም።
ከዚህ በፊት አንድ ታዋቂ ኢትዮጵያዊ ከሰው የሰማሁት ቀልድ ነው ብለው የሚከተለውን ተናግረው ነበር።
የኢትዮጵያ ሕዝብ በሦስት ይከፈላል – ታስረው የተፈቱ፣ የታሰሩ እና ወደፊት የሚታሰሩ
ከላይ የተባለው ቀልድ ነው። እውነታው ግን ሁላችንም የታሰርን መሆናችን ነው። ዛሬ ሁላችንም አንዱዓለም አራጌዎች፣ ሁላችንም እስክንድር ነጋዎች፤ ሁላችንም ደበበ እሸቱዎች፤ ሁላችንም ውብሸት ታዬዎች፣ ሁላችንም ርዕዮት ዓለሙዎች፣ ሁላችንም ስለሺ ሀጎሶች፣ ሁላችንም በቀለ ድሪባዎች፤ ሁላችንም ኦልባና ሌሊሳዎች ነን። ዛሬ እያንዳንዳችን በኢትዮጵያ እርስ ቤቶች ከሚማቅቁ ወገኖቻችን እንደ አንዱ ወይም እንደ አንዷ ነን። ሁላችንም እስረኞች ነን።
ከፊት ለፊታችን የተደቀነውም ጥያቄ እንዲህ የሚል ነው።
ለመሆኑ የታሰርንበትን እስር ቤት ሰብረን ለመውጣት ዝግጁዎች ነን? … …. ወይም በእስር ለመማቀቅ ፈቅደናል?
አሳሪዎቻችን ጥቂቶች መሆናቸውን እናውቃለን። እኛ ታሳሪዎቹ ግን ብዙሃን መሆናችንን የታወቀ ጉዳይ ነው። እንደምን ጥቂቶች ብዙሃንን አስረው እንዲንደላቀቁ እንፈቅዳለን?
የታሰርንበት ወህኒ ቤት የበሰበሰና ገፋ ቢደረግ የሚደረመስ መሆኑን እናውቃለን። የብረት አጥር ይመስሉ የነበሩ የቱኒዚያ፣ የግብጽና የሊቢያ እስር ቤቶችም ተደምሰው ህዝቦቻቸው የነፃነት አየር መተንፈስ መጀመራቸውን አይተናል። እናስ የታሰርንበትን አሮጌ እስር ቤት የመደርመስ አቅም እንዴት እናጣለን?
ቆርጠናል። ሁላችንንም እንደ አቶ አንዱዓለም አራጌ መሮናል። ነፃነት ዋጋ እንደሚያስከፍል እናውቃለን። የነፃነት ዋጋ ህይወትም ሊጨምር እንደሚችል እናውቃለን። ነፃነታችን የሚጠይቀንን ዋጋ ለመክፈል ደግሞ ዝግጁዎች ነን።
የመለስ ዜናዊ ዘረኛ አገዛዝ መወገድ ይኖርበታል። የመለስን አገዛዝ በቶሎ መላቀቅ፤ አዲሲቷን ውብ ኢትዮጵያን በቶሎ ያስገኝልናል።
በ2004 ዓ.ም. ይህ መልካም አጋጣሚ እንዲያመልጠን አንሻም። በዚህ ዓመት እስር ቤቶቻችንን ሰባብረን በመውጣት የነፃነት አየር መተንፈስ እንፈልጋለን፤ ለዚህም ተነስተናል።
አዎ !!! አሁን ሁላችንም አንዱዓለም አራጌዎች፣ ሁላችንም እስክንድር ነጋዎች፤ ሁላችንም ደበበ እሸቱዎች፤ ሁላችንም ውብሸት ታዬዎች፣ ሁላችንም ርዕዮት ዓለሙዎች፣ ሁላችንም ስለሺ ሀጎሶች፣ ሁላችንም በቀለ ድሪባዎች፤ ሁላችንም ኦልባና ሌሊሳዎች ነን። አሁን ሁላችንም እስረኞች ነን። በቅርቡ ግን እስር ቤቶቻችንን ሰብረን ነፃ እንወጣለን!!!
ድል ለኢትዮጵያ ህዝብ!!!