ፍኖት ጋዜጣ – በሽብርተኝነት ተጠርጥረው የታሰሩትን ቤተሰብ መጠየቅ አልቻለም!

በቅርቡ “በሽብርተኝነት”ተጠርጥረው የታሠሩትን እስረኞች «በምን ሁኔታ ላይ አንደሚገኙ ማወቅ አልቻልንም» ሲሉ ቤተሰተቻቸውና የሥራ ባልደረቦቻቸው ለዝግጅት ክፍላችን ገለጹ፡፡

የአንድነት ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት የአቶ አንዱዓለም አራጌ ወንድም ወጣት አብርሃም አራጌ እንደሚለው “ወንድሜ የታሠረበትን የእስር አያያዝ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ በተደጋጋሚ ለመጠየቅ ሄጄ ምግብ ተቀብለው ዕቃ ከመመለስ ውጪ በአካል አግኝቼው አላውቅም”፡ ብሏል፡፡

የፓርቲው ማዕከላዊ ም/ቤት አባላት የሆኑት የመ/ር ናትናኤል መኮንን ባለቤት ወ/ሮ ፍቅርተ እንደሚሉት “ባለቤቴ ለመጠየቅ በየዕለቱ እመላለሳለሁ ምግብ ተቀብለው ይመልሱኛል፡፡ አንዳንድ ቀን ምግቡ አንዳለ ተመልሶ ሲደፋ አይቿለሁ፡፡ ለምን አልበላም ስላቸው ተያቸው አነሱ ጥጋበኛ ናቸው ፤ ምግቡን አምጡት ሌሎች ይበሉታል» ሲል ጥበቃው ላይ ያለ ፖሊስ መልስ ሰጥቶኛል” በማለት ቅሬታዋን ገልጻለች፡፡

የመ/ር አሳምነው ብርሃኑ አህት ወ/ሪት መሳይ ብርሃኑ በተመሳሳይ ሁኔታ “ወንድሜ ከታሠረ ቀን ጀምሮ ለማግኘት ሞክሬ አላገኘሁትም፡፡” ብላለች

የታዋቂው ጋዜጠኛና የፖለቲካ ተንታኝ እስቅንድር ነጋ ባለቤት ወ/ሮ ሰርካለም ነጋ አንደምትለው “ለመጠየቅ በየጊዜው ብሄድም ምግብ ተቀብለው ዕቃ ከመመለስ ውጪ ያለበትን ሁኔታ ማወቅ አልቻልኩም፡፡ የአገሪቱ ሕገ-መንግሥት አንድ እስረኛ ሲታሰር በቤተሰቦቹ በሕግ አማካሪው በጓደኞቹ የመጐብኘት መብት አለው ይላል፡፡ ፖሊስ ግን ለህግ ቆሜአለሁ፣ ሕግ አስከብራለሁ አያለ ራሱ ሕግ አያከብርም፡፡ አስረኛው ከማንም ሰው እንዳይገናኝ አድርገዋል፡፡” ብላለች ።

የአርቲስት ደበበ እሸቱ ባለቤት ወ/ሮ አልማዝ ደጀኔ በተመሳሳይ ሁኔታ “ባለቤቴን ለመጠየቅ ሞክሬ ከልክለውኛል፡፡ በጽ/ቤት በኩል ሄጄ አገናኙኝ ብላቸውም ሥራ ላይ ስለሆንን አንችልም ብለውኛል” በማለት ተናግረዋል፡፡

የጋዜጠኛ ስለሺ ሀጐስ ቤተሰቦችም እንደገለጹት ልንጠይቅ ሞክረን ተከልክለናል ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትህ ፓርቲ ም/ሊቀመንበርና የውጪ ጉዳይ ኃላፊ እ/ር ግዛቸው ሽፈራው የፓርቲው የፓርቲው ዋና ፀሐፊ አቶ ዳዊት አስራደ የፓርቲው ሥራ አስፈጻሚና የሕግና የሰብአዊ መብት ጉዳይ ኃላፊ አቶ ሽመልስ ሀብቴና ሌሎች የትግል አጋሮቻቸው ለመጠየቅ ሄደው መከልከላቸውን የፓርቲው ጽ/ቤት ለዝግጅት ክፍላችን ገልፀዋል፡፡

ፍኖት ነጻነት ለስላምና ለዲሞክራሲ በቆሙ ዜጎች ገንዘብ እርዳታ የሚታተም ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማተም፣ በስፋት በአገራቷ ክፍሎች ለማሰራጨት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃንልና የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆች ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል ።
ፍኖት እትም ስምንት በመሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !