ፍኖት ጋዜጣ – የአደባባይ ምስጢሮች -ለፈገግታ

አካባቢው አንድ ገጠር መንደር ነው፡፡ የዘመኑ የአካባቢው ገዢ ሕዝቡን ሰብስቦ ሲናገር ይውላል፡፡ ሕዝቡም ዝም ብሎ ያዳምጣል፤ እርሱ ያወራል ሕዝቡን ያዳምጣል። መናገር ሲስለቸው «አሁን ተራው የእናንተ ነው፤ ሐሳብ መስጠት ትችላላችሁ» ይላቸዋል፡፡

ሁሉም ዝም ይላል፡፡ «ተናገሩ» ይላል አሁንም በመደጋገም ። አሁንም ሕዝቡ ዝም አለ፡፡ “ጊዜው የዴሞክራሲ ነው ፤ የፈለጋችሁትን መናገር ትችላላችሁ፡፡ ተርበን፣ ሞተን፣ ቆስለን፣ ጓደኞቻችን ሞተው እዚህ የደረስነው ለእናንተ ፣ ለዴሞክራሲ መብት ነው፡፡ ምንም ሳትፈሩ ተናገሩ” ይላል፡፡

ከተሰብሳቢዎቹ ከኋላ ወንበር፣ አያ ሙሄ የሚባል አንድ ሰዉ እጁን ያወጣና “እኔ ልናገር” ይላል፡፡ «ተናገር፤ አዎ ተናገር፣ ቀጥል የፈለክውን ተናገር ይለዋል»

“እናንተ ውሸታሞች፣ እናንተ . . . እንዲህ እያደረጋችሁን፣ እንዲህ በደልና ግፍ እየፈፀማችሁብን … ዛሬ ትዋሹናላችሁ፡፡ ውሸታችሁ፣ ማጭበርበራችሁ ዛሬም አይበቃም፡፡ ዛሬስ አታፍሩም!” ብሎ ቁጭ ይለል፡፡

ሌላው መሐል ከተቀመጡት አንዱ እጁን ያወጣል፡፡ «እህ እህ» ብሎ ድምጹን አጸዳድቶ የለበሰውን ኩታ እያጠፈ ቆም ካለ በኋላ፣ ንግግሩን ይጀምራል ። “መቼም ቅድም አያ ሙሄ እንዳለው” ብሎ ፣ አያ ሙሄ ወደአለበት ቦታ ዞር ሲል፣ አያ ሙሄ በአራት ሰው ተንጠልጥሎ ሲወሰድ ያያል፡፡ ደንግጦ ወደ ቀኝ ዞር ሲል ሁለት የሰው ልጅነታቸው ወደ አውሬነት የተቀየሩ የሚመስሉ ሁለት ሰዎች ፊታቸውን ክስክስ አድርገው ቆመዋል፡፡ «እነዚህ ደግሞ ለሚቀጥለው የተዘጋጁ አይደለም፡፡ ይልና “አያ ሙሄ እንዳለው ዴሞክራሲ ዴሞክራሲ ነው” ብሎ ቁጭ አለ፡፡

ፍኖት ነጻነት ለስላምና ለዲሞክራሲ በቆሙ ዜጎች ገንዘብ እርዳታ የሚታተም ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማተም፣ በስፋት በአገራቷ ክፍሎች ለማሰራጨት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃንልና የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆች ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል ።
ፍኖት እትም ስምንት በመሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !