ፍኖት ጋዜጣ – የኢሕአዴግ የግፍ ቀንበር ያረፈባቸዉ አቶ ዘመኑ ሞላ ማን ናቸዉ ?
ዘመኑ ሞላ ተወልዶ ያደገው ከዚሁ አዲስ አበባ ሲሆን፣ ባለትዳርና ያንዲት ሴት ልጅ አባት ነው፡፡ ልጁ ጎበዝ ተማሪ ስለሆነች በዚህ ዓመት ዩኒቬርስቲ እንደምትገባ በቅርብ የሚያውቋት ይናገራሉ፡፡
ዘመኑ ሞላ ነባር የሰላማዊ ትግል ታጋይ ሲሆን የኢዴፓ ነባር አባል በመሆኑ በ92 ዓ.ም በተደረገው ሁለተኛው አገራዊ ምርጫ አ.አ ክልል ተወዳድሮ ነበር፡፡
ቆይቶ ደግሞ ኢዴፓ የሚሄድበት መንገድ ስላላማረውና ስላልጣመው ከዚያ ወጥቶ ከመሰል ጓደኞቹ ጋር በመሆን መኢዴፓን ከመሠረቱት ውስጥ አንዱ በመሆን በ97 ዓ.ም በተደረገው 3ኛው አገራዊ ምርጫ መኢዴፓን ወክሎ ለተወካዮች ም/ቤት ተወዳድሯል፡፡
ዘመኑ ሞላ በቁጥጥር ሥር እስከዋለበት ድረስ የፓርቲው (የመኢዴፓ) ዋና ጸሐፊ ነበር፡፡ እንዴት በቁጥጥር ሥር እንዳዋሉት ድራማውን የትግል ጓዶች እንደሚከተለው ይገልፁታል፡-
“የያዙት ከፓርቲው ጽ/ቤት በሥራ ላይ እንዳለ ነው፡፡ ከመያዙ በፊት አንዲት ወጣት እየደጋገመች ስልክ በመደወል የአ.አ.ዩ የፖለቲካል ሣይንስ ተማሪ እንደሆነችና በተቃዋሚ ፓርቲዎች ዙሪያ ጥናታዊ ጽሑፍ በመጻፍ ላይ መሆኗን ገልፃለት ከመረጠቻቸው የተቃዋሚ ፓርቲዎች ውስጥ አንዱ መኢዴፓ በመሆኑ እንዲተባበራት ትለምነዋለች፡፡ 10 ሰዓት እንደሚመቻትም ትነግረዋለች፡፡ እሱም በቀናነት እንድትመጣ ፈቃደኛ ይሆናል፡፡
በተጠቀሰው ሰዓት ትመጣለችና ወደ ቢሮም ትገባለች፡፡ አምስት ደቂቃ ባልሞላ ጊዜ ውስጥ አንድ ግለሰብ ይገባል፡፡ ይሄኔ ወጣቷ እየሳቀች ወጥታ ሄደች፡፡ ያግለሰብም በኋላ ጠይቀን እንዳረጋገጥነው የወረዳው የደህንነት ሰው መሆኑን ለማወቅ ችለናል፡፡
“ይህ ግለሰብ በምን ምልክት እንደ ጠራቸው ባናውቅም ወዲያውኑ እሱን ተከትለው 15 የሚሆኑ ወታደሮች ተከታትለው በመግባት እጅ ወደ ላይ በማለት ይዘውት ወደ ቤቱ በመሄድ ቤቱን መፈተሻቸውን ሰምተናል፡፡ አብረን ስላልሄድን ምን እንዳደረጉና ምን ንብረት ይዘው እንደ ሄዱ አላወቅንም” ሲሉ ገልፀውልናል፡፡
ፍኖት ነጻነት ለስላምና ለዲሞክራሲ በቆሙ ዜጎች ገንዘብ እርዳታ የሚታተም ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማተም፣ በስፋት በአገራቷ ክፍሎች ለማሰራጨት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃንልና የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆች ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል ።ፍኖት እትም ስምንት በመሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !