የፍኖት ጋዜጣ እትም 8 ርእሰ አንቀጽ – ማሰር መፍትሄ አይሆንም !
ከጥቂት ወራት ወዲህ ገዢው ፓርቲ ስርዓቱ ላይ የሠላ ሂስ በመሠንዘር የሚታወቁ የፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞችን የማሠር ዘመቻውን ጀምሯል፡፡ የእስራት ዘመቻው ማቆሚያ የት ጋ እንደሆነ የታወቀ ነገር እስካሁን የለም፡፡ የእስር ዘመቻው ያነጣጠረው ግን ከኢህአዴግ አቋም በተቃራኒው የቆሙ ግለሰቦች ላይ መሆኑ የአገራችንን የወደፊቱን የፖለቲካ አቅጣጫ አሳሳቢ አድርጎታል፡፡
ከታሪክ እንደምንማረው በዓለም ላይ በርካታ አምባገነን መንግስታት ኖረው አልፈዋል፡፡ አውሮፓን ሲያምሱት የነበሩት አምባገነኖቹ ሂትለርና ሙሶሊኒ የሚቃወሟቸውን በሙሉ አስረዋል፣ አሣድደዋል ሲከፋም ገድለዋል፡፡ ሕጋዊና ሠላማዊ ተቃውሞን በጉልበት አፍኖ ማቆየት ስለማይቻል እነዚያ አምባገነኖች ከሚወዱት ወንበራቸው በኃይል ተባረዋል፡፡ በታሪክም በነውረኛ ድርጊታቸው ሲታወሱ ይኖራሉ፡፡
ከዚህ የታሪክ ሃቅ የምንማረው ቁምነገር ቢኖር አመፅ ሌላ አመፅን የሚወልድ መሆኑን እንጂ፣ በጭራሽ ህዝብን ዝም ለማሠኘት የማይቻል መሆኑን ነው፡፡ አመጽ ደግሞ የልማትና የዕድገት ፀር ነው፡፡ ስለዚህ ይወገዛል፡፡
በአገራችን የእስር ፖለቲካ አዲስ አይደለም፡፡ የቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ መንግሥት የሚቃወሙትን ከማሠር አልተመለሰም፡፡ ለአስራ ሠባት ዓመታት አገራችንን በጠመንጃ ኃይል ያስተዳደረው የደርግ ወታደራዊው መንግስትም ስልጣኑን በጉልበት ለማቆየት የቻለው ለተወሰኑ ዓመታት ብቻ ነበር፡፡ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ የደርግን ያህል የተቃወሙትን ዜጎች በማሳደድ ብዙ ሰው ያሠረና በጭካኔ ህዝብን የፈጀ አንድም ስርዓት አልነበረም፡፡
የተለያየ ስም እየተሠጣቸው በርካታ እስረኞች ወደ ወህኒ ይጣሉ ነበር፡፡ “ስርዓት አልበኝነትን ለማስወገድ” በሚል ደርግ ወደ ሥልጣን በመጣበት ሠሞን ከፍተኛ የእስር ዘመቻዎችን አካሂዶ ነበር፡፡ በዚህ ህጋዊ በሚመስል አካሄድ የተጀመረው የጅምላ እስር ወደ “አብዮታዊ ርምጃ” ተሸጋግሮ እንደነበር የሚታወስ ነው፡፡ እንደሚታወቀው ግን የተወሰደው “ርምጃ” በሙሉ የደርግን ስልጣን ዘላቂ ሊያደርገው አልቻለም፡፡ የጉልበት አማራጭ ሊሠራ የሚችለው እስከተወሰነ ጊዜ ድረስ ብቻ በመሆኑ ስልጣኑን ለማጣት ተገዷል፡፡ የደርግም ዘመን እንደ ሄትለርና እንደ ሙሶሊኒ ዘመን በአሳሪነቱ ከዚያም አልፎ በጨፍጫፊነቱ ሲዘከር ይኖራል፡፡
ከደርግ መውደቅ በኋላ በርካታ የፖለቲካ ፓርቲዎች የስልጣን ሽግግር በሠላማዊ መንገድ መሆን እንዳለበት በማመን በአገር ውስጥ በመደራጀትና ሠላማዊ ትግል በማድረግ ላይ ይገኛሉ፡፡ እነዚህ የፖለቲካ ኃይሎች በአንድም ሆነ በሌላ መንገድ በሥልጣን ላይ ያለውን ፓርቲና የአገዛዝ ሥርዓቱን መከታተልና ችግሮች ካሉ እንዲስተካከሉ መገዳደራቸው አይቀሬ ነው፡፡
አሁን ኢሕአዴግ የሚገጥሙትን ተግዳሮቶች ለመቋቋም በሽብርተኝነት ስም እየወሰደ ያለው የማሰር ዘመቻ ለአገራችን የፖለቲካ ሁኔታ የማይጠቀም ከዚያም አልፎ አደገኛ በመሆኑ ከአሁኑ መታረም አለበት፡፡ በመጀመሪያ ደረጃ ለሠላማዊ ትግል ቆመው በአገር ውስጥ እየተንቀሳቀሱ ባሉ የፖለቲካ ፓርቲዎችና የሠላማዊ ትግል አራማጆች ላይ ከፍተኛ ስጋትን የሚፈጥር ነው፡፡ ሠላማዊ ዜጎችም ሆኑ ድርጅቶች በአገራቸው የሕግ ሥርዓት እንዳይተማመኑና የሕግ ከለላ አለን ለማለት እንዳይችሉ ያደርጋቸዋል፡፡ ይህም በአገራችን የሕግ ሥርዓት ላይ መጥፎ ጥላ የሚያጠላ መሆኑ አያጠራጥርም፡፡
በዚህ ዘመን የምናያቸው የመንግሥት የማሠር ርምጃዎችን ተከትለው በተለይ በፖለቲካ ተቀናቃኞቹ ላይ የሚነሱ የፍርድ ቤት ክሶች እጅግ የተጋነኑ ሆነው ይገኛሉ፡፡ ቀደም ብሎ ይነሱ የነበሩ ክሶች “የአገር ክህደት፣ የዘር ማጥፋት” የሚሉ ነበሩ፡፡ የእነዚህ ዓይነት ከባድ ክሶች በተቀናቃኝ ፖለቲካ ፓርቲ መሪዎችና ጋዜጠኞች ላይ መከፈታቸው አሳዛኝ ነበር፡፡
ምርጫ 97ን ተከትሎ የወጣው የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ደግሞ ጠንካራ የፖለቲካ እንቅስቃሴዎችን የሚያደርጉ ፓርቲዎችን ወንጀለኛ የሚያደርግ ነው፡፡ የፀረ ሽብርተኝነት አዋጁ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዳይስፋፋ ከማገዱም በላይ ገዢው ፓርቲ አዋጁን እንዳሻው በመተርጎም ለራሱ ፍላጐት ማራመጃነት እንዲጠቀምበት ዕድል ይሠጠዋል፡፡ ይህን አዋጅ በመጠቀም አሁን የተጀመረው የእስርና የፕሮፓጋንዳ ዘመቻ በአገራችን ላለው የፖለቲካ ችግር መፍትሄ መሆን አይችልም፡፡
የአገራችን የፖለቲካ ችግሮች ሊፈቱ የሚችሉት በቅድሚያ ከበጎ መንፈስ በመነሳትና ከዚያም በመነጋገር፣ በመደራደርና በመወያየት እንጂ አሁን በተያዘው የእስርና የፕሮፓጋንዳ መንገድ አይደለም፡፡ ዛሬም ቢሆን ከታሪክ መማር አለብን፡፡ ቀደም ሲል እንደተገለጸው በአገራችን ውስጥ እንኳ የቅርብ ጊዜ ታሪካችን እንዳሣየን ከደርግ በላይ ብዙ ያሠረና የገደለ አልነበረም፡፡ የጅምላ ግድያውና እስራቱ ግን ደርግን ከስልጣኑ ከመውረድ አላዳኑትም፡፡ አሁንም ቢሆን አበክረን የምናሳስበው ነገር የተጀመረው እስር ለሁላችንም የማይበጀን መሆኑን ነው፤ ኢሕአዴግንም ጨምሮ፡፡
በተደጋጋሚ እንደምንመለከተው ኢሕአዴግ ይናገራል፤ ስለተናገረው ነገር ጥሩነት ራሱ ይመሰክራል፡፡ ሌላውን ለማድመጥ ፍቃደኛ አይደለም፡፡ የህዝብ ረሃብ፣ ሥራ አጥነት፣ የመልካም አስተዳደር እጦት፣ ሙስና፣ እየተገነባ ያለው ኢ-ዲሞክራሲያዊና ኢ-ሰብአዊ ሥርዓት አይታየውም፡፡ በኢህአዴግ እይታ ይህንን ማወቅ፤ ይህንን መናገር፤ ይህንን ማውገዝ ሽብርተኝነት ነው፡፡
ዛሬ በአገሪቱ ላይ ያለውን የፍትህ እጦት፣ የሰፈነውን ሙስና ማውገዝ የተጫነብንን የመሣሪያ አገዛዝ መቃወም ሽብርተኝነት አይደለም፡፡ ትግሉ የነጻነት ትግል ነው፡፡ በሕግ ጽንሰ ሐሳብ “ህጐች ሁሉ ፍትሐዊ አይደሉም” ይባላል፡፡ አንድ ሕግ ሕግ ስለተባለ ብቻ ሕግ አይደለም፡፡ ሂትለርም የሚገዛበት ህግ ነበረው፡፡ ቦካሳም፣ ኢዲያሚንም ህግ ነበራቸው፡፡ የደቡብ አፍሪካ አፓርታይድም ሕግ ነበረው፡፡ በዓለማችን በቅለው የከሰሙ አምባገነኖች ሁሉ ህግ ነበራቸው፡፡ ህጎቻቸው ግን ፍትሐዊ አልነበሩም፡፡
በአገራችን ካሉት ህጐች ውስጥ የሚገኘዉ የሽብርተኝነት ህግ ፍትሐዊ ህግ አይደለም፡፡ ህጉን ከረቂቁ ጀምረው ምሁራን፣ የሕግ ባለሙያዎች፣ አዛውንትና ፖለቲከኞች ለዚች ሀገር እንደማይበጃትና ራሱ ሽብር ፈጣሪ በመሆኑ እንዲሻሻል በወቅቱ መክረዋል። የምክራቸው ስጋት ዛሬ ገሀድ እየወጣ ነው፡፡ ንፁሀን ዜጎች በሽብርተኝነት ህግ ለእስር እየተዳረጉ ነው፡፡
ይህ ዜጎችን በሽብርተኝነት ሰበብ የማሰር እርምጃ መፍትሔ አይሆንም፡፡ ማሰር፣ መግደል፣ ማሳደድ ማዋከብ መፍትሔ ቢሆን ኖሮ አምባገነኖች ለዘላለም በኖሩ ነበር፡፡ መፍትሔው በመጀመሪያ ወደ ህሊና መመለስ ነው፤ መፍትሔው ተቀምጦ መወያየት ነው፡፡ መፍትሔው ያለው በጠረጴዛ ዙሪያ ነው፡፡ መፍትሔው ህዝብን ማድመጥ ነው፡፡ መፍትሔው ከጠመንጃ አፈሙዝ መላቀቅና ለሕዝብ ፍላጎት ተገዥ መሆን ነው፡፡
ደግመን ደጋግመን ኢሕአዴግን ለማሳሰብ የምንፈልገው ወደ ሕሊናው ተመልሶ በሰከነ መልኩ የመጣበትን መንገድ እንዲያስብ ነው፡፡ በደርግ ጊዜ ኢሕአዴግ ላይ ይሰነዘሩ የነበሩትን በርካታ ተለጣፊ ስሞች ማስታወስ የግድ ይላል፡፡ ሕዝብን ማስጨነቅ፣ ሕዝብን ማሰቃየት ፣ ሽብርተኝነትን እዋጋለሁ እያሉ በሕዝብ አእምሮ ውስጥ ሽብር መልቀቅ ለጊዜው የሠራ ሊመስል ይችላል፡፡ አሳሳች ነው፡፡
አሁን ኢህአዴግ እየወሰደ ያለው ርምጃ ስህተት ብቻ ሳይሆን ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ነው፡፡ ይዘገያል እንጂ ለውጥ መምጣቱ አይቀሬ ነው፡፡ ኢሕአዴግ እርምጃውን አስክኖ በሰላማዊ መንገድ ለዉጥ እንዲመጣ መሥራት አለበት፡፡ መፍትሄው ይሄ ብቻ ነው፡፡ በማንኛውም መመዘኛ ማሠርና ንፁሀን ዜጎችን እያዋከቡ ጥላሸት መቀባት መፍትሄ አይሆንም፡፡ የምናከብረው መንግሥት እንዲኖረን እንፈልጋለን፡፡
ፍኖት ነጻነት ለስላምና ለዲሞክራሲ በቆሙ ዜጎች ገንዘብ እርዳታ የሚታተም ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማተም፣ በስፋት በአገራቷ ክፍሎች ለማሰራጨት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃንልና የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆች ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል ።
ፍኖት እትም ስምንት በመሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ