ፍኖት ጋዜጣ – ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር (በአቶ ሙሉጌታ በሪሁን ከአዲስ አበባ)

ክቡር ጠ/ሚንስትር የሰው ልጅ የአገሩን የአስተዳደር መረጃ ካለማጤን ስህተት መፈጠሩ አይቀሬ ቢሆንም በተጓደኝ የተፈፀመውንና የተደረገውን በማስታወስ የተሠራ ጥፋት መታረም ይቻላል፡፡ ከዚህ አንፃር ባገራችን የሚታየውንና እየተፈፀመ ያለውን ግዙፍ ስህተት ቅኝ ገዥዎች እንኳን ይሠሩታል ብሎ ለመናገር የሚከብድ ይመስለኛል፡፡ ይህንን ጽሑፍ ለመዳፍ ያነሳሳኝ ሀገራዊ ስሜትና ፍቅር እየቆጠቆጠኝ አላስቆም አላስቀምጥ ስላለኝ ሰሚ ባይኖርም የድርሻዬን ልወጣ በሚል ነው፡፡

ኢሕአዴግ ሥልጣን ከተቆናጠጠበት ጀምሮ የአገራችን ሕዝቦች የተረጋጋ ማኀበራዊ ሰላም የላቸውም፡፡ ሁሉም ዜጎች የሚኖሩት በሥጋት እየበረገጉ ነው፡፡ የኑሮ ዋስትና የላቸውም፡፡ የኔ የሚሉት ቁራጭ መሬት የላቸውም፡፡ የከተማም ሆነ የገጠር መሬት በመንግሥት ቁጥጥር ሥር ነው፡፡ መንግሥት በጥርጣሬ የሚያያቸውን ይነቅላል፤ የኔ የሚላቸውን ደግሞ ይተክላል፡፡ ከዚህ በከፋ መልኩ ደግሞ የከተማንም ሆነ የገጠርን መሬት ለኢንቬስተር ተብየዎች ለ99 ዓመት በኮንትራት እየቸበቸበ ይገኛል፡፡ ይህ ድርጊት በእጅጉ አሳሳቢ ነው፡፡ ባንድ በኩል “ሕዝብ ለአምስት ዓመት መርጦ ኮንትራት ፈርሞ አገር እንዳስተዳድር ሰጥቶኛል” የሚለው ኢሕአዴግ በሌላ በኩል ደግሞ ከሥልጣኑና ከውክልናው ውጭ ለ99 ዓመት ለውጭ ዜጎች መሬት የመሸጡ ጉዳይ አጠያያቂ ነው፡፡

ዛሬ ለኢሕአዴግ መንግሥት መሬት ከእንቁ የበለጠ ሸቀጥ ሆኗል፡፡ ዜጎች ከቀያቸውና ለረጅም ጊዜ ከኖሩበት ሠፈር እየተፈናቀሉ መሬት በሊዝ እየተቸበቸበ ነው፡፡ አራት ኪሎንና ልደታን የሚመለከት ዜጋ ምን ስሜት እንደሚፈጠርበት መገመቱ ከባድ አይሆንም፡፡ የዜግነት ትልቁና ዋና መለኪያው ያፈሩ፣ የቀየው ያገሩ፣ እኩል ተጠቃሚና የመብት ባለቤት ሲሆን ነው፡፡ ዜጎችን ከመኗሪያቸው እያፈናቀሉ የውጭ ዜጎችን በኢንቬስተር ስም ለ99 ዓመት ማስፈር ግን ለሕሊና የሚከብድ ጉዳይ ነው፡፡

ወደፊት የሕዝብ ቁጥር እየጨመረ ሲሄድና የተማረ የሰው ኃይል እየተበራከተ ሲመጣ እጣ ፈንታው ምን ሊሆን ነው? በገዛ ሀገሩ ለነዚህ የባዕዳን ኢንቬስተሮች ተቀጣሪ አገልጋይ ሊሆን ነው? ይህም ቢሆን እነሱ ፈቅደው የሚቀጥሩት ከሆነ ነው፡፡

ክቡር ጠ/ሚንስትር

በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን መንግሥት የዚችን አገር ዕድገት ለማፋጠን የጊዜው ንቃተ ሕሊና በሚፈቅደው መጠን ቤት ሠርቶ ማከራየት፣ በንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ እንዳቅምና እንደ ገቢው መጠን ነግዶ ማትረፍ ተገቢ ስለነበር ዜጎች የተነቃቁበት ዘመን ነበር ማለት ይቻላል፡፡ ከዜጎች ጎን ለጎንም ዘመናዊውን የንግድ ሥርዓት ያስተዋወቀ የውጭ ዜጎች ነበሩ፡፡

እነሱም፡-ዐረቦች፣ ግሪኮች፣ አርመኖች፣ ሕንዶች፣ ባንያኖች ነበሩ፡፡ ክቡር አቶ መኮንን ሀብተወልድ የአገሪቱ ኢኮኖሚ በተለይም የንግዱ ዘርፍ ከውጭ ሰዎች ጫናና ተጠቃሚነት ተላቆ ሙሉ በሙሉ ባገር ሰዎች እጅ መያዝ አለበት በሚል ቅን ሐስተሳሰብ ተነሣስተው፣ ለንግዱ ክፍለ ኢኮኖሚ ቅርበት ያላቸውን የሕብረተሰብ ክፍሎች ማለትም ነገደ ጉራጌዎችን በሀገር ፍቅር ቲያትር አዳራሽ ሰብሰባው፣ ሰፋ ያለ ስሜትን የሚቀሰቅስ ንግግር ካደረጉ በኋላ የገንዘብ አሰባሰብ ዘዴ በመቀየስ ያኑ እለት ኮሚቴ አቋቁመው የገንዘብ አቅም የሌላቸውን ለማገዝ ሲባል እቁብ፣ እድር የመሳሰሉትን በመመሥረት አቅማቸውን ማጎልበታቸውን የዚህ ጽሁፍ አዘጋጅ ያይን ምስክር ነበር፡፡ በርግጥም እስከ አብዮቱ ፍንዳታ ድረስ የተረጋጋ ማኀበራዊ ሕይወት ነበር፡፡

ክቡር ጠ/ሚንስትር

የታሪክ አጋጣሚ ሆኖ የርስዎ ሲንየሮች ቢሆኑም ያንድ ዘመን ወጣቶች በመሆናችሁ ግንዛቤው እንዳለዎ እረዳለሁ፡፡ በመሆኑም ጥላሁን ግዛው፣ ዋለልኝ መኮንን፣ ማርታ መብራቱ፣ እና የሌሎቹም ሕይወት የተቀጠፈው “መሬት ላራሹ !” እያሉ በመጮህ መሬት የሌለው ዜጋ የሚያደርሰው መሬት እንዲኖረው፣ ከተሜው እንዳቅሙ የሚኖርበት የጎጆ መቀለሻ ቁራጭ መሬት እንዲያገኝ ነበር፡፡

ከዚህ ባለፈም ዘውዳዊው ፈላጭ ቆራጭ ሥርዓት አክትሞ በእኩልነት የሚኖርበትን ሥርዓት በማምጣት እንጂ ድሆች ቤት ንብረታቸው እየፈረሰ ከሚኖሩበት ቀየ እየተፈናቀሉ ለውጭ ኢንቬስረሮች ለ99 ዓመት የሚቸበችብ ሥርዓትና መንግሥት እንዲመጣ አልነበረም፡፡ ይህ ድርጊትም መንግሥተዎንና ሥርዓተዎን በከፋ መልኩ ወደ ፊት ሲያስወቅስ የሚኖር ነው፡፡

የከተማ ቦታ አዋጅ ቁጥር 47/67 ንዑስ አንቀጽ 3 ይህ አዋጅ ከፀናበት እለት ጀምሮ፣ የከተማ ቦታና ትርፍ ቤት የመንግሥት ሆኗል ይላል፡፡ ንዑስ ቁጥር 2/ ማንኛውም ቤተሰብ ግለሰብ ወይንም ድርጅት የከተማ ቦታን በግል በባለቤትነት መያዝ አይችልም፡፡ በዚህ አዋጅ አንቀጽ 8/ የከተማ ቦታ የያዘን ቤተሰብ፣ ግለሰብ ወይንም ድርጅት ለአገር ጥቅም አስፈላጊ ነው በተባለ ጊዜ መንግሥት አስፈላጊውን ካሣ ሰጥቶ (ትክ) ይወስዳል እንጂ ቦታውን አሳልፎ እንደፈለገ ለባእዳን ኢንቬስተሮች ይሸጣል አይልም ፡፡

እንዲሁም ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊት ሬፐፕሊክ (ኢፌዲሪ) ሕገ መንግሥት አንቀጽ 40 ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ የግል ንብረት ባለቤት እንደሚኖረው ይገልፃል፡፡ በዚህ አንቀፅ ቁጥር 3 የገጠርም ሆነ የከተማ ቦታ፣ የተፈጥሮ ሀብት ባለቤት መንግስትና ሕዝብ ብቻ ናቸው ይልና መሬት የማይሸጥ፣ የማይለወጥ የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰቦች የጋራ ንብረት ነው ይላል፡፡ ይህንን መብት መሠረት አድርገው ይመስላል የጋምቤላ፣ የቤኒሻንጉል ዜጎች መሬታችን ለሕንዶች፣ ለአረቦች፣ ለቻይናውያን አይሸጥብንም እያሉ ቅሬታቸውን በተለያዩ መንገዶች እየገለፁ ያሉት፡፡

ክቡር ጠ/ሚንስትር መለስ

አገርን ማልማትና ማበልጸግ እንዲሁም የታሪክ ባለቤት መሆን የሚቻለው ዜጎችን ከቀያቸው እያፈናቀሉና እያንበሳቆሉ፣ መሬትን ለውጭ ባለሀብቶች ለ99 ዓመት እየሸጡ አይደለም፡፡ ሕዝብን የአገሩ፣ የመብቱ ባለቤት አድርጎ፣ ከሕዝብ ሣይርቁ ቀረብ ብሎ በመመካከርና ለእድሜ ባለጸጎች ዋጋ እየሰጡ በመወያየት ነው፡፡ ሕዝብን አርቆ ወይንም ከሕዝብ በስተጀርባ አሸምቆ ለውጭ ቱጃሮች ስም የሆነውን መሬት በመሸጥ በምንም መመዘኛ አገርን ማልማት አይቻልም፡፡ ቢያንስ የድህነትን ጎዳና ይዘን እያሸቆለቆልን ያለንበትን ሁኔታ ሊያጤኑት በተገባዎት ነበር፡፡

የዓባይን ድልድይና የዓባይን ግድብ እኛው በኛ እንወጣዋለን እየተባለ እንደሚነገረው ለም መሬታችንስ እኛው በኛ እንዳናለማው ምንድን ነው ችግሩ? ምን ዓይነት ክፋት ነው የተጠናወተን? ዜጎችን እየነቀልን የባእዳንን ኢንቬስተሮች የምንተክልበት ምክንያቱ ምንድን ነው? ለምን ነገንና ከነገ ወዲያን አናስብም? የቀጣይ ትውልድ እጣ ፈንታ ምን ሊሆን ነው? ቢያንስ እየተራበ የሚኖርባት አገር ማሣጣት ታሪክ ይቅር የማይለው ጥፋት ነው እየተሠራ ያለው፡፡ ወጣቱ አገር አጥቶ አርፎ ይቀመጣል? አገሩ የባእዳን ቱጃሮች እየበለጸጉባት እያየ ትእግሥት ይኖረዋል፡፡ ትንሽ ችግር እናስወግዳለን ሲባል የከፋ ችግር እያጠመድን መሆናችንን ልብ ሊሉት ይገባል፡፡

ክቡር ጠ/ሚንስትር

ከላይ የዘረዘርኩለዎትን ሳስታውስ ባንድ ወቅት እስዎ የተናገሩት ትዝ አለኝ፡፡ “ከእንግዲህ አዲስ አበባ የሚኖሩት ገንዘብ ያላቸው ብቻ ናቸው፡፡ ገንዘብ የሌላቸው ወደ መጡበት ተመልሰው ይሄዳሉ” ነበር ያሉት፡፡ ለመመለስም እኮ የኔ የሚሉት ይዘታ ሲኖራቸው ነው፡፡ ወደ አዲስ አበባ የመጡትኮ ይዞታ አጥተው ፈልሰው ነው፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባ ከገጠር ፈልሰው በመጡ ዜጎች ተጨናነቀች እንጂ እስዎ እንደተመኙት ወደ መጡበት አልተመለሱም፡፡ ምክንያቱም የኔ የሚሉት ምንም ነገር የላቸውምና፡፡

ክቡር ጠ/ሚንስትር

በመጨረሻም እንደ ዜግነቴና እንደ የዕድሜ ባለጸጋነቴ ምክሬን ቢቀበሉኝም ባይቀበሉኝም አንድ ነገር ማለት እወዳለሁ፡፡ ከሕዝብ ጋር ተመካክሮ የሠሩት ሥራ አመርቂ ውጤትን ያስገኛል፡፡ ከበሬታንና ፍቅርንም ያጎናጽፋል፡፡ ለዜጎች መሠረታዊ ለውጥም መድህን ይሆናል፡፡ ከሕዝብ ርቆ፣ ከሕዝብ ተደብቆ፣ ከሕዝብ ጀርባ ተሁኖ፣ ሕዝብን ንቆ የሚሠራ ሥራ ግን መካን ነው፡፡ አድሮ ፈራሽ ነው፡፡ ሕዝብ አያውቀውም፤ ስላላወቀውም የኔነት ስሜት አይኖረውም፡፡ ስለዚህ ይህ መሬት ለኢንቬስተሮች እየተባለ የሚሸጠው መቆም አለበት፡፡

ድህነታችንን ማጥፋት የምንችለው በራሳችን ኃይል መንቀሳቀስ ስንችል ብቻ ነው፡፡ አለበለዚያ የምንሠራቸው ሥራዎች ሁሉ የእንኳይ ካብ ሆነው እንደሚፈርሱ ቅንጣት አይጠራጠሩ፡፡ በዘመንዎ ክፉ ነገር እንዳይፈፀም ደግመው ደግመው ያስቡበት፡፡ ባሁኑ ሰዓት ከአጎራባች አገራት መሪዎች ትምህርት ሊወስዱ ይገባዎታል፡፡ የሚመጣውን ጦስ በጦር ኃይል እመክተዋለሁ የሚሉ ከሆነም ውጤቱ ጥፋት ብቻ ሳይሆን ለትውልድ በተለይም ለትግሬኛ ተናጋሪው ወገናችን ጠንቅ ተክለው እንዳይሄዱ፣ ክፉን ነገር አያስቡ፤ አይመኙ፡፡ በመጨረሻም በምትከተለው የዲያስፖራዎች እንጉርጉሮ እሰናበተዎታለሁ፡-

እኔ በሰው አገር አገሬን ለሌላ
ከሰው የበለጠ እንጀራ ላልበላ
እኔ ስንከራተት ያገሬን ለም መሬት
መጥቶ ሠፈረበት የውጭ ደላላ

ፍኖት ነጻነት ለስላምና ለዲሞክራሲ በቆሙ ዜጎች ገንዘብ እርዳታ የሚታተም ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማተም፣ በስፋት በአገራቷ ክፍሎች ለማሰራጨት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃንልና የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆች ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል ።

ፍኖት እትም ስምንት በመሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !