ፍኖት ጋዜጣ – የኢሕአዴግ የግፍ ቀንበር ያረፈባቸዉ አቶ አሳምነዉ ብርሃኑ ማን ናቸዉ ?
አሣምነው ብርሃኑ ተወልዶ ያደገው ከዚሁ አዲስ አበባ ነው፡፡ የትምህርት ደረጃው በፊዚክስ ቢ.ኤስ.ሲ ዲግሪ አለው፡፡ ባሁኑ ጊዜ በኢኮኖሚክስ በዲግሪ መርሃ ግብር አዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ እየተማረ ነበር፡፡ መደበኛ ሥራውም መምህር ነው፡፡
ቤተሰብ አሣምነው ብርሃኑ ገና ወጣት በመሆኑ ለሥራና ለትምህርት እንዲሁም ለነፃነት ተግቶ ከመሥራት ውጭ ትዳር ለመመሥረት አስቦ እንደማያውቅ ቤተሰቦቹ ገልፀውልናል፡፡
የፖለቲካ አቋምአሳምነው ብርሃኑ አንድነት ፓርቲን ከመቀላቀሉ በፊት የፖለቲካ እንቅስቃሴው ብዙም የጎላ አልነበረም፡፡ ገና ወጣት በመሆኑና ሁለንተናዊ ቀልቡን ከትምህርቱ ላይ ነበር የሚያተኩረው ይላሉ ቤተሰቦቹ፡፡ የመጀመሪያ ዲግሪውን ይዞ የአንድነት ፓርቲ አባል ከሆነ በኋላ ግን ባሰየው የነቃ ተሳትፎ ለብሔራዊ ም/ቤት አባል ለመሆን የበቃ ወጣት ታጋይ ነው፡፡
አሣምነው ብርሃኑ ጭምት፣ ለቁም ነገር ጉዳይ ካልሆነ በስተቀር ከመናገር ሲበዛ ቁጥብ ነው፡፡ ባጭሩ የተግባር ሰው ነው፡፡ ኢሕአዴግ ይህንን የረጋና የሰከነ ወጣት በሽብርተኝነት እጠረጥረዋለሁ ብሎ ማነቁ ሁሉንም አስገርሟል፡፡ እንዴት እንደያዙት ቤተሰቦቹ እንደሚከተለው ይገልፁታል፡፡
“መስከረም 3 ቀን 2004 ዓ.ም ከቀኑ 10 ሰዓት አካባቢ ከቤታችን የታጠቁ ኃይሎች መጡ፡፡ በዚህ ወቅት አሳምነው ከቤቱ ውስጥ ነበር፡፡ ወታደሮች ቤታችንን ሲከቡት የሠፈራችን ሰው የምን መዓት መጣብን በሚል በሽብር ተዋጠ፡፡ ወደ ቤት ውስጥ ገብተው እሱን ከያዙት በኋላ እጆቹን አጣምረው በካቴና አሠሯቸው፡፡ ያን ጊዜ እኛ ግድግዳ አስደግፈው የሚረሸኑት ሰለመሰለን የምንይዘውን የምንጨብጠውን አጥተን ተብረከረክን፡፡ ቁም ብድግ በል እያሉ በቪዲዮ ካሜራ ይቀርፁት ነበር፡፡ ይህን ካደረጉ በኋላ እሱን ወደ ጥግ አስቀምጠው ቤቱን መፈተሽ ጀመሩ፡፡ ሁኔታቸው ሁሉ እንደ ቀማኛ አይነት ነበር፡፡ ሥርዓት አልነበራቸውም፡፡ የቤቱን እቃ ግልብጥብጥ አድርገውታል፡፡ ሽንት ቤት ሳይቀር ፈትሸዋል፡፡ ላፕቶፕ ኮምፒዩተሩን፣ ሞባይሉን፣ ፍላሽ ላይቱን፣ ሲዲዎችን፣ የኛን 3 ሞባይሎች፣ የኤቲኤም ካርድ፣ አንዳንድ ጥናት ያጠናባቸው የነበሩ ጥራዝ ወረቀቶችን እነዚህን ሁሉ ሲወስዱ እሱን አብረው በፊልም አየቀረፁ ነው፡፡ እነዚህን ሁሉ መዝግበዋል፡፡ አይፓዱን እስከነ ኤርፎኑን ግን አልመዘገቡትም፡፡ ደንግጠን ስለነበር ምን ያህል እቃ ይዘው እንደሄዱ ዛሬም ቢሆን ገና ለይተን ማወቅ አልቻልንም፡፡ ይህንን ሁሉ አተራምሰው ወደየትም ስልክ እንዳንደውል አስጠንቅቀውን እስከነንብረቱ ይዘውት ሄዱ”
ሲሉ ቤተሰቦቹ ገልፀውልናል፡፡
ፍኖት ነጻነት ለስላምና ለዲሞክራሲ በቆሙ ዜጎች ገንዘብ እርዳታ የሚታተም ነዉ። ጋዜጣዉን በብዛት ለማተም፣ በስፋት በአገራቷ ክፍሎች ለማሰራጨት ትልቅ የገንዘብ አቅም ይጠይቃንልና የፍኖት ጋዜጣ አዘጋጆች ድጋፍዎትን በአክብሮት ይጠይቃል ።
ፍኖት እትም ስምንት በመሉ ለማንበብ ከዚህ ይጫኑ !