ጆሮ ያለው ይስማ
ጆሮ ያለው ይስማ
ከዝግጂት ክፍላችን
ህወሓት በቅርቡ ያደረገውን ምርጫ ተከትሎ በወያኔ ደጋፊዎች መካከል እየተስተዋለ ያለውን መከፋፈል በሚመለከት ሁለት ነጥቦችን ለማንሳት ወደናል። አንደኛ፦ ስብሃትም ነጋም ሆነ መለስ ዜናዊ መሰረታዊ በሆነው ጉዳይ ላይ ልዩነት የላቸውም። ሁለቱ የሚለያዩት እንዴት አድርገው የዘረኛውን አገዛዛቸውን እድሜ ማራዘም እንዳለባቸው መላ ሲመቱ ነው።
መለስ ዜናዊ ህወሓትን ኢትዮጵያዊነትን በሚያቀነቅን ብሔራዊ ድርጅት ካባ ስር ሸፍነን ለሚቀጥሉት አስርተ አመታት ተደብቆ የሚገዛበትን መንገድ እናመቻች ይላል። ዘረኛነትን በጦር ሰራዊቱ ዘንድ በግልጽ መስበኩ ምን ያህል ለሱም ለቡድኑም እንደጠቀመው የሚያውቀው ስብሃት ነጋ ደግሞ፥ “አይሆንም፤ ህወሃት እንዳለ መቀጠል አለበት፤ የምን ብሔራዊ ድርጅት?” ይላል።
ምክንያቱም፥ ስብሃት ደህና አድርጎ እንደሚያውቀው፤ እነ መለስ ለፖለቲካ ጥቅም ሲሉ ውሸታቸውን የኢትዮጵያዊነት አቀንቃኞች ቢሆኑ፤ ይህ አይነት ውስብስብ የፖለቲካ ሴራ ከታች ላሉት እና አገዛዙን ይዘው ለቆሙት የህወሃት ወታደሮች ግልጽ እንደማይሆንላቸው ያውቃል። “ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ” ሲባልና ባንዲራ ሲውለበለብ ያዩት ወታደሮች፤ ከጥንት ጀምሮ የፕሮፓጋንዳ ነፋስ ወደነፈሰበት ሲነፍሱ ስለኖሩ፤ ዘረኛነትን ረስተው ኢትዮጵያዊነትን ሊቀበሉ ይችላሉ። ትናንት ሲሰድቡት እና ሲተፉበት የነበረውን የኦሮሞ ጀነራል ማክበር ሊጀምሩ ነው። ከሌሎች ብሔረሰብ የመጡ ወታደሮችን እንደ ወንድሞቻቸው ማየት ሊጀምሩ ነው። በስህተት ማለት ነው።
ይህ ከተከሰተ ደግሞ፥ ድሮ ዘረኝነት ዘግቶት የነበረው ትልቅ ቀዳዳ ወከክ ብሎ መከፈቱ ነው። በእውነት ኢትዮጵያውያን የሆኑ ዜጎች እና ድርጅቶች በዚህ ቀዳዳ እየገቡ የትግራይ ተወላጁን ወታደር ልብ እውነት እየነገሩ ሊያሸፍቱት ይችላሉ። ይህ የወያኔ መቆሚያ መሰረት ከተሰረሰረ ደግሞ ምንም ያህል ቢደበቅ የአገዛዙ ማብቂያ ሊሆን ይችላል። ስብሃት ነጋ ይህንን ይረዳል።
መለስ ዜናዊ ግን በዘረኛነትም ተጠቅሞ ቢሆን በጦሩ ላይ እና በትግራይ ህዝብ ላይ ተማምኖ እንደ ኢትዮጵያ ገዢ መቆየት እንደማይችል ለረዥም ጊዜ ሲሰማው ቆይቷል። የትግራይ ህዝብ ሌላ ትግራዌ አግኝቶ ፍንክች ቢልበት መውደቂያ እንደሌለው ጠንቅቆ ያውቃል። ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የዜግነት ስሜትም እሱ ከሚያስበው በላይ ከፍተኛ እንደሆነ የ1997ቱ ምርጫ አስተምሮታል። ስለዚህም፥ እሱ የመረጠው መንገድ፦ ከዚህ ቀደም በታሪክ እንደታዩ አንዳንድ አምባገነኖች እራሱን እንደ አገር ወዳድ መሪ በመቅረጽ እና ምስሉን በየቦታው በማሰቀል መግዛትን ነው።
ለጊዜው መለስ ዜናዊ ብሔራዊ ፓርቲ በመፍጠር ሃሳቡ እንደተሸነፈ አስመስለው እና ኢህአዴግ የተባለው የወያኔ እና የተለጣፊ ድርጅቶቹ ስብስብ እንዳለ ለመቆየት መወሰኑን ማንም ሳይጠይቃቸው ወጥተው መግለጫ ሰጥጠዋል። ከዛ በፊት ውይይቱ እየተካሄደ እንደነበረ ነግረውንም አያውቁም ነበር።
ይሁን እንጂ፥ ይህ ማዘናጊያ እና ምናልባትም በህወሃት ውስጥ ያሉትን የሃሳቡን ተቃዋሚዎች የመጥረጊያ ጊዜ መግዣ እንደሆነ እናውቃለን። ምክንያቱም እውነታው የመለስ ዜናዊ ቡድን ከጊዜ ወደ ጊዜ እየገነነ ሲሄድ፤ የስብሃት ቡድን ደግሞ ከስራ ውጪ እየተደረገ መሆኑ ነው። ይህ ወደ ሁለተኛው ነጥባችን ይወስደናል።
ሁለተኛው ነጥባችን፥ በህወሃት ውስጥ አለ የሚባለው መከፋፈል እና እያመጣ ያለው ውጤት አንድ ፍንትው አድርጎ እያሳየን ያለው ነገር ቢኖር መለስ ዜናዊ በተለይም ከዘጠኝ አመታት በፊት ከተከሰተው የድርጅቱ መሰንጠቅ ጀምሮ እያደረገ የቆየው ስልጣንን ወደ እጁ የመሰብሰብ ስራ ከፍተኛ ደረጃ ላይ መድረሱን ነው። ያኔ እነ ስየ አብረሃን እና ገብሩ አስራትን ከድርጅቱ በመወርወር የረዳውን ስብሃት ነጋን ሳይቀር አረጀህ ብሎ ወርውሮታል። ባንፃሩ ደግሞ ያኔ ሰው መኖሯን እንኳ ያውቅላት ያልነበረችውን ባለቤቱን የስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ አስሹሟታል።
አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች፥ አዜብ መስፍን ምናልባት መለስ ዜናዊ ከስልጣን ወርዶ ከበስተጀርባ ለመግዛት ከወሰነ የሱን ስፍራ ልትረከብ ትችላለች በሚል ይተነብያሉ። ያንን በማድረግም መቀመጫውን ለመለስ ዜናዊ ልጅ ለሰምሃል መለስ ትጠብቃለች እስከማለት የሚደርሱም አሉ።
ይህ ሁሉ ትንበያ እውነት ይሁን አይሁን፥ አንድ ዛሬ በእርግጠኝነት የምናውቀው ነገር ቢኖር በስብሃት ሞግዚትነት እዚህ የደረሰው ልጅ የሞግዚቱን ጡት ነክሶና አባሮ የቤቱ አለቃ መሆኑን ማስታወቁን ነው። በአምባገነኖች ደንብ እንደሚደረገውም በዙሪያው ያሉትን የስልጣን መቀመጫዎች ከሚስቱ ጀምሮ በቅርብ ጓደኞቹ እና “እሺ-ባዮቹ” የመሙላቱን ስራ አጠናክሯል። እንዲህ ነው አምባገነን! እንዲህ ነው መለስ ዜናዊ!
ይብላን ለወያኔ ደጋፊዎች እንጂ እኛ እንደሆንን ከዘረኛው አምባገነን የተሻለ ነገር ጠብቀን አናውቅም። እንዳውም የሚደረገው የቤት ማጽዳት በስብሃት ነጋ እና እንደ አርከበ እቁባይ ባሉ የጉያው ሰዎች ያበቃል ብለን አንገምትም። ገና መች ተነካና! ደግሞም፥ የቤት ማጽዳቱ ስራ ከማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት እና ከስራ አስፈፃሚነት በመባረርም የሚያበቃ አይመስለንም። ገና መች ተጀመረና!
ውድ የወያኔ ደጋፊዎች እና የአገር ዘረፋ አጋፋሪዎች፥ ያቀጣጠላችኋት እሳት እስክትበላችሁ ድረስ አትቆምም። እሳቱን ባቀጣጠላችሁበት እጅ መልሳችሁ የማጥፋቱ ጥበብ ስላልተሰጣችሁ፤ እሳት ደግሞ ስትስፋፋ እና ስትንሰራፋ ስም፣ እድሜ፣ ዘር እና ማንነት ስለማትጠይቅ፤ ማን እንዳቀጣጠላት፣ ማንስ እንድትኖር ከመጀመሪያውኑ እንዳደረጋት ስለማታውቅ፤ የሷ ስራ ዝም ብሎ መብላት ስለሚመስላት፣ የያንዳንዳችሁን ቤት መጎብኘቷ የማይቀር ጉዳይ ነው። “ጆሮ ያለው ይስማ!” ብለናል።