አንድ የጀርመን ፓርላማ አባል በኢትዮጵያ ያለዉ የሰብአዊ መብት አያያዝ እጂግ አሳሳቢ ሆኑአል አሉ
የሀገሪቱን ሠላምና ፀጥታ ለማደፍረስና ሕገ-መንግሥታዊዉን ሥርዓት ለማፍረስ አሲረዋል በማለት የዘረኞች ቁንጮ መለስ ዜናዊ አገዛዝ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ጋዜጠኞችን በሽብርተኝነት ስም በማሰር የጀመረዉ ዘመቻ እጅግ እንዳሳሰባቸዉ የጀርመን ፓርላማ አባል ቲሎ ሆፕ ገለፁ።
እንደ ፓርላማ አባሉ መግለጫ የአረመኔው መለስ አገዛዝ በመዉሰድ ላይ ያለዉ እርምጃ በወያኔ አገዛዝ ላይ የሰላ ሂስ የሚሰነዝሩ ሃይሎችን ስልታዊ በሆነ መንገድ ለማጥፋት ሊሆን ይችላል ብለው እንደሚያምኑ ተናግረዋል።
ካለፈዉ መጋቢት ጀምሮ ቁጥራቸዉ 370 የሚሆኑ የፖለቲካ ተቃዋሚዎች የታሰሩ ሲሆን ከነዚህም ዉስጥ 217 የሚሆኑት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ዲሞክራሲያዊ ንቅናቄ / ኦፍዴን/ አባላት እንደሆኑ ቲሎ ሆፕ ጠቅሰዋል። በቀለ ገርባ፤ ኦልባና ሌሊሳ፤ እንዲሁም አርቲስት ደበበ እሼቱን ተከትሎ የጋዜጠኛ እስክንድር ነጋና የአንድነት ለፍትህና ለዲሞክራሲ ዋና ፀሃፊና የህዝብ ግንኙነት ሃላፊ የሆኑት የአንዱአለም አራጌ እና ሌሎችም በተከታታይ በሽብርተኝነት እየተወነጀሉ እስር ቤት መጣላቸዉ አጅግ አሳሳቢ እንደሆነ ተናግረዋል።
የጀርመን መንግስት ድርጊቱን በጥብቅ በማዉገዝ ለኢትዮጵያ መንግሰት ባለስልጣኖች ጠንካራና ግልፅ አቋሙን ማሳወቅ እንደሚገባዉ የገለፁት የፓርላማ አባል መንግስታቸዉ እስረኞቹ እንዲፈቱ እንዲጠይቅና ይህን መሰሉ የሰብኣዊ መብት ጥሰት በሁለቱ አገሮች የልማት ትብብር ላይ ተጽእኖ እንደሚኖረዉ በግልፅ ማስታወቅ እንዳለበት አሳስበዋል።
ከዚህ ጋር በተያያዘ የወያኔው አገዛዝ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላትንና ጋዜጠኞችን በአሸባሪነት ጥርጣሬ ማሰሩን አለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች ድርጅት አምንስቲ ኢንተርናሽናል መቃወሙ ታዉቋል።
በድርጅቱ የኢትዮጵያና ምሥራቅ አፍሪካ ጉዳይ አጥኚ ክሌር በስተን በለንደን ከጀርመን ድምፅ ወኪል ጋር ባደረጉት ቃለ መጠይቅ የኢትዮጵያ መንግሥት ሰዎችን በአሸባሪነት ስም የሚያስረዉ የፖለቲካ ፓርቲዎች፥ የመብት ተቆርቋሪ ተቋማትና ጋዜጠኞች የሚያሰሙትን ቅሬታና ተቃዉሞ ለማፈን እንደሆነ የዶቼቬሌ ሬዲዮ የአማርኛዉ ገልጿል። ዘረኛው አገዛዝ የእስረኞቹን ሕጋዊ መብት እንዲያከብርም ክሌር በስተን ጠይቀዋል።
ይህ በዚህ እንዳለ በኢትዮጵያ ውስጥ እየከፋ በመጣው የሰብ አዊ መብት ጥሰት ምክንያት 15 አትሌቶች በሞዛምቢክ በመደረግ ላይ ባለው የአፍሪካ ጨዋታዎች ውድድር ላይ ሲሳተፉ ከቆዩ በሁዋላ መሰወራቸውን ቢቢሲ ዘግቦአል። አትሌቶቹ ስላሉበት ሁኔታ የአገሪቱ መንግስት እንደማያውቅ የገለጸ ቢሆንም የአትሌቶቹ አሰልጣኝ ወደ ደቡብ አፍሪቃ ሳይጉአዙ እንዳልቀረ መግለጹም ተዘግቡአል።