የግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ የአዲስ ዓመት መልዕክት

የግንቦት7 ንቅናቄ ሊ/መንበር ዶ/ር ብርሃኑ ነጋ የ2004 አዲስ አመት አስመልክተው ለኢትዮጵያ ህዝብ ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል

ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ!

በቅድሚያ በግንቦት 7: የፍትህ፣ የነፃነትና የዲሞክራሲ ንቅናቄ እና በራሴ ስም “እንኳን ከዘመን ወደ ዘመን አሸጋገረን” እላለሁ።

ያሳለፍነው 2003 ዓመተ ምህረት በዓለም ላይ ብዙ አስደናቂና ተስፋ ሰጪ ኩነቶች የታዩበት ዓመት ነበር። እኛ በነፃነት ስንኖር በቅኝ ግዛት ባርነት ውስጥ ይኖሩ የነበሩ ብዙ ኣፍሪካዊ ወገኖቻችን እኛን ኣልፈው ሄደው ከራሳቸው ኣምባገነኖች ተላቀው የነፃነት ኣየር እየተነፈሱ ነው:: እንደኛው በአምባገነን አገዛዞች ሲረገጡ የነበሩ የሰሜን አፍሪቃና የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ህዝቦች አምባገነንነትን ተራ በተራ ከጫንቃቸው ሲያስወግዱ አይተናል፤ ቱኒዝያ፣ ግብጽና ሊቢያ የተቀጣጠለው የነፃነት ሰደድ ወላፈኑ እኛም አገር ደርሷል።

የመለስ ዜናዊ አገዛዝም ይህንኑ በቅጡ በመረዳቱ መወራጨቱ በዝቷል። አንዴ ከየት እንደመጣ ባልታወቀው በአባይ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት፤ በሌላ ጊዜ ደግሞ “በትራንስፎርሜሽን” ወሬ ሊያማልለን ቢሞክርም የህዝቡን ትኩረት ለመሳብ ግን አልቻለም። እሱ ግን እያስገደደ ከህዝቡ ገንዘብ መዝረፉን እንደቀጠለበት ነው::

በሃገራችን በደልና ምሬት በዝቷል። ድህነትና ጉስቁልና ከመቸውም በባሰ ተንሰራፍቷል። እስርና ሰቆቃ (ቶርቸር) ተራ ነገሮች ሆነዋል። በኣሸባሪዎች ስም በከተማችን የሚፈነዱት ቦምቦች የመለስ ደህንነቶች ሆን ብለው ያጠመዷቸው ቦምቦች መሆናቸውን ዓለም እየመሰከረም፤ ሰላማዊ ዜጎች በአሸባሪነት እየተፈረጁ ለስቃይ መዳረጋቸው የዘወትር የመለስ ዓይን ኣውጣ ትዕይንት ሆኗል። ዛሬ በሃገራችን አርሶ መኖር አይቻልም፤ ሰፋፊውና ለሙ መሬት ለባዕዳን ቱጃሮች ተሰጥቷል። ነግዶ፣ ቸርችሮ ማደርም አይቻልም። የባንክ ብድር እንደፈለጉና በርካሽ ከሚያገኙ፤ ግብርና መዋጮ ከማይከፍሉ የወያኔ የንግድ ድርጅቶች ጋር ተፎካክሮ፤ ለከት ያጣ ግብርና መዋጮ ከፍሎ ማትረፍ አይታሰብም።

ኑሮ እጅግ በመወደዱ ወያኔ በጠላትነት የፈረጀው ሰፊው የኢትዮጵያ ህዝብ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ጥቅማ ጥቅሞች የሚደልላቸው የገዛ አባላቱ እንኳን ሳይቀሩ ቤተሰቦቻቸውን ከረሃብ መታደግ አልቻሉም። አብዛኛው ዜጋ ልጆቹን በቀን አንድ ጊዜ እንኳን መመገብ ተስኖታል።

የወጣቶች ተስፋ የጨለመ በመሆኑ ተረጋግተው ትምህራቸውን መከታተል አልቻሉም። ትምህርቱ ራሱ አለ ማለትም አይቻልም።

በተገኘው መንገድ ሁሉ ከዚህ ስቃይ ለመሸሽ በርካታ ወገኖቻችን በጀልባዎች ወደ አረብ አገራት ለመሻገር ሲሞክሩ ሰጥመው የባህር አውሬዎች ቀለብ ሆነዋል። ሌሎች ደግሞ በእግር ጉዞ በረሃ ሲያቋርጡ በሃሩር ደርቀው ቀርተዋል። የጎረቤቶቻችን አገሮች እስር ቤቶች የሞሉት በኢትዮጵያዊያን ወጣት ወንዶችና ሴቶች ነው። ኢትዮጵያዊያን ወጣቶች በአገራቸው ያለውን ሰቆቃ ለማምለጥ ሲሞክሩ፤ በሊቢያ በፈላ ውሀ ስትለበለብ እንደከረመችው እህታችን ሸዋዬ ሙላ፤ በጎረቤት አገራት ሰቆቃ ውስጥ ገብተዋል።

በአንፃሩ ደግሞ የዘመኑን ባላባቶች የተንቀባረረ ኑሮ ማየት ያበግናል። እነሱ በዘረፉት ገንዘብ ፎቆችና ቪላዎችን እየገነቡ ይዝናናሉ። እነሱ ለቁጥር የሚያታክት ገንዘብ ወደ ዉጭ አገራት ያሸሻሉ። እነሱ ለድሃው የመጣውን እርዳታ ተከፋፍለው ብሉና ብላክ ሌብል፤ ውስኪና ሻምፖኝ ይራጩበታል። ጣእሙን በቅጡ የማያውቁትን ካቪያርን ውድ ስለሆነ ብቻ የውስኪ ማወራረጃቸው ኣድርገውታል::

አገራችንና ህዘቧ የረሃብ የስቃይና የውርደት አዙሪት ውስጥ ናቸው። የመለስ አገዛዝ ካልተወገደ በስተቀር አገራችንና ህዝባችን ከረሃብ፣ ከድህነትና ከውርደት መውጣት አይችሉም። የመለስ ዜናዊ እኩይ አገዛዝ ከዚህ በላይ እንዲቆይ ከፈቀድንለት ሁላችንም የጋሻጃግሬዎቹና የባዕዳን ሸሪኮቹ የቀን ሠራተኞች መሆናችን አይቀርም። የቅጥራችን እና የኑሯችን ሁኔታም ከባርነት የባሰ እንጂ የተሻለ እንደማይሆን እያየነው ነው።

ውድ የኢትዮጵያ ህዝብ ሆይ!

ነፃነት መኖሩን እያወቅን ባርነትን መቀበል አይቻለንም!!!

የመለስ ዜናዊን አገዛዝ ማስወገድ አሁን እየደረሰብን ካለው መከራ የከበደ ነገር አይደለም። ባህር በታንኳ ለመሻገር፤ በረሃን በእግር ለማቋረጥ የቆረጠ ወጣት ራሱን ነፃ አውጥቶ የስደትን ስቃይና ውርደት ማስቆም እንደሚችል ጥርጥር የለኝም። ከቅኝ ገዢዎች ወረራ ራሱን ለመከላከል ከፍተኛ መስዋእትነት በመክፈል ነፃነቱን አስከብሮ የኖረ ህዝብ በመለስ ዜናዊ ጋባዥነት ባዕዳን ሃገሩን እየተቀራመቱት ከርስቱና ከቀየው እየነቀሉ ክብር-አልባ ሃገር-አልባ እያደረጉ አንገዋለው ሲጥሉት “በቃ!” የማለት፤ “እምቢ!” የማለት ጀግነነት በደሙ አሁንም እንደሚፈስ ጥርጥር የለኝም። የመለስ ዜናዊ አገዛዝን እብሪት፣ ዘረኛነትና ዘረፋ ህሊናችን ፈጽሞ ሊቀበለው የሚገባ ጉዳይ አይደለም።

በደል በዝቷል። ምሬት በዝቷል። ሆኖም መፍትሄ መሻት እንጂ የደረሱብንን በደሎች መዘርዘር ፋይዳ የለውም።

ወገኖቼ !!!!

ከዚህ በላይ በዚህ ማጥ ውስጥ መቆየት አንችልም። የመለስ አገዛዝ መወገድ ይኖርበታል!!! ይህ ደግሞ በአስቸኳይ ሊፈፀም የሚገባው ተግባር ነው!!!

አዲሱን ዓመት የመለስ ዜናዊ ግፈኛና ዘረኛ አገዛዝ ተወግዶ የብሩህ ተስፋ መንገዳችንን የምንጀምርበት ዓመት ማድረግ ይገባናል። ይህ አዲስ ዓመት ይዞ የመጣልን መልካም እድሎች ሊያመልጡን በፍጹም አይገባም።

አዲሱን ዓመት እንደተቀበልን የምናመራው በድል መጠናቀቅ ወደሚኖርበት ሁለገብ ትግል ነው። ይህ ትግል ለነፃነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትህ፣ ለዴሞክራሲ፣ ለሰላምና ለአንድነት የሚደረግ ትግል ነው። ይህ ትግል ቸነፈረን በብልጽግና፤ ውርደትን በክብር ለመተካት የሚደረግ ትግል ነው።

ይህንን ትግል በአሸናፊነት መወጣት የህልውና ጉዳይ ነው። ወገባችን አስረን፤ ሃሞታችንን አስቆጥተን እንነሳ!!!

ብርሃኑ ነጋ ነኝ

ኣዲሱን ዓመት የነፃነት ዓመት ያድርግልን!!!!!